ተክለጻድቅ መኩርያ
ከ ብርሃነ መስቀል ደጀኔ እና ጌታሁን ሽብሩ “ያሠርቱ ምእት፥ የብርዕ ምርት” የተወሰደ
ተክለጻድቅ መኩርያ በ፲፱፻፮ ዓ.ም. በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ አሳግርት ልዩ ስሙ ሳር አምባ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምሕርት ሲደርስ መጀመሪያ ከአባታቸውና ቀጥሎም በአጥቢያቸው ባህላዊውን ትምሕርት እስከቅኔ ያለውን ቀስመዋል። ከዚያም አዲስ አበባ መጥተው አሊያንስ ፍራንሴዝና ተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ገብተው የጊዜውን የትምሕርት ደረጃ አጠናቀዋል።
ኢጣልያ አገራችንን የወረረች ጊዜም በየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ፍጅት ተይዘው ወደ ሶማሌ ደናኔ ተግዘው ለሦስት ዓመታት ታስረዋል። ከነጻነትም መልስ አገራቸውን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል።
መጀመሪያ ተቀጥረው ያገለገሉት በትምሕርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር ነበር። እዚያም ሳሉ በአገራችን ሰው የተጻፈ የአገራችን ታሪክ አንድም ባለመኖሩ በቁጭትና በመቆርቆር ነበር ‘መጻፍ አለብኝ’ ብለው በደንብ ከሚታወቀው ከቅርቡ ጊዜ በቅጡ ወደማይታወቀው የሩቁ ዘመን መጻፍ የጀመሩት። የመጀመሪያውን መጽሐፍ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” የሚለውን በ ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. አሳተሙ። ከጫፍ እስከ ጫፍ ጽፈው የመጨረቻውን መጽሐፍ፣ የታሪካችን መጀመሪያ የሚሆነውን “የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ-አክሱም-ዛጉዬ እስከ ዓፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት” የሚለውን በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. አቅርበዋል። እኒህኑ መጻሕፍት ትምሕርት ሚኒስቴር ታሪክ ለማስተማሪያ በትምሕርት ቤት ተጠቅሞባቸዋል።
ተክለጻድቅ ከታሪክ ውጭ የጻፏቸው “የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ” እና በሚዮቶሎዢያ (mythology አፈ ታሪክ) ላይ ያተኮረ “ከጣዖት አምልኮ እስከ ክርስትና” የሚሉም መጽሐፎች አሏቸው።
ተክለጻድቅ በምድር ባቡር በዋና ጸሐፊነት፥ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ዋና ሥራ አስኪያጅነት፥ እንዲሁም በፈረንሳይ፥ በእስራኤል፥ በዩጎዝላቪያ በዲፕሎማሲ ሥራ በመጨረሻም የትምሕርትና የባህል ሚኒስቴር ሆነው አግልግለዋል። በፈቃዳቸው ጡረታም ከወጡ በኋላ በምርምር የታገዙ ሦስት ታላላቅ የታሪክ ሥራዎችን አቅርበዋል።
ተክለጻድቅ ከረጅም የአገልግሎት ዘመን በኋላ በተወለዱ በ ሰማንያ ስድስት ዓመታቸው ሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. አርፈዋል።
የተክለጻድቅን ሥራዎች ዋጋ የምንሰጣቸው ለሚከተሉት ምክንያቶች ነው፦
- ታሪክን ከተተበተበበት ልማዳዊ አጻጻፍ ነጻ አውጥተው በሰገላዊ መንገድ መጻፍ በመጀመራቸው
- አገራዊውን መረጃም ሳይተው በውጭ ቋንቋ በጣልያንኛ፥ በፈረንሳይኛ፥ በእንግሊዝኛ ጭምር ያለውን ሁሉ ተጠቅመው ከስር እስከጫፍ የአገሪቱን ታሪክ በመጻፋቸው
- እኒህን ሁሉ መጻሕፍት የጻፉት በመደበኛ የቀለም ትምሕርት ቤት ሳይሰለጥኑ፥ በከፍተኛ የመንግሥት ሥራና ኀላፊነት ተጠምደው፥ ያላቸውን የምዝናኛ ጊዜ ሁሉ ሰውተው ቁም ነገር በመሥራታቸው
- በተለይም ከአሥራ አምሥት ዓመታት በላይ የደከሙበት “የግራኝ አሕመድ ወረራ” የተሰኘው መጽሐፋቸው በመቶ አምሳ አምሥት ምዕራፎችና ስምንት መቶ አርባ ገጾች በጽሑፍ፥ በካርታ፥ በሠንጠረዥ፥ በፎቶግራፍ መረጃዎች ተሞልቶ ሥርዓት ባለው መልክ ታሪኩ ትንትን ተደርጎ የተሠራ ግዙፍ ሥራ በመሆኑ
ዋቢ መጻሕፍት
ለማስተካከልብርሃነ መስቀል ደጀኔ እና ጌታሁን ሽብሩ፣ “ያሠርቱ ምእት፥ የብርዕ ምርት ክፍል ፩” ፣ ጳጉሜን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.