ማናማልቴል (ማናባልቴል፣ ማናበልቴኤል፣ ማናባልቲኤል) የማርቱ (አሞራዊ) ንጉሥ ኪሱራ በሚባል ከተማ-አገር በመስጴጦምያ ሲኖር ምናልባት ከ1836 እስከ 1805 ዓክልበ. አካባቢ ነገሠ። ከሥነ ቅርስ ሰነዶች ጥቂት መረጃ ይታወቃል።

ማናማልቴል ለዘመናዊ መምህራን መጀመርያ የታወቀው በ1891 ዓ.ም. በታተመ የሥነ ቅርስ መጣጥፍ ነበር።[1]ባቢሎን መጀመርያ ነጻ ንጉሥ ከሱሙ-አቡም ዘመን አስቀድሞ በዙሪያው ግዛት እንደ ነበረው ታወቀ። ሊቃውንት በፊት ዋና ከተማው ሲፓራ እንደ ነበር ቢመስላቸውም ጽላቶች በየጥቂቱ ሲነበቡ አሁን የኪሱራ ንጉሥ መሆኑ ተረጋገጠ።

ለእርሱ ፲ ያህል ልዩ የዓመት ስሞች በሰነዶቹ መካከል ተገኝተዋል፤ ቅድም-ተከተላቸው ግን አይታወቀም። ከነዚህ አንዱ ትኩረት የሚስብ «ኡር-ኒኑርታ ያረፈበት ዓመት» (= 1806 ዓክልበ. ግድም) የሚባለው ነው። ሌላ ከተማ-አገር ኢሊፕ-አኩሱም ደግሞ በንጉሥ ሃሊዩም ሥር ሆኖ ይህን ዓመት ስም «ኡር-ኒኑርታ የተገደለበት ዓመት» አለው።

በዚያ ወቅት የካዛሉ ንጉሥ ሱሙ-ዲታና ዓርፎ ያምጺኤል በተከተለው ጊዜ ሱሙ-አቡም በባቢሎን ነጻነት ከካዛሉ አዋጀ። ሱሙ-አቡም ኢሊፕ በያዘበት ጊዜ (1805 ዓክልበ.) ሃሊዩም በአብዲ-ኤራ፣ ማናማልቴልም በሻራሥዩሩም እንደ ተተኩ ይመስላል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን የላርሳ ንጉሥ ሱሙኤል ካዛሉንና አኩሱምን ያዘ። በዚያን ጊዜ በኪሡራ ሻሩሥዩሩም በንጉሥ ኡባያ እንደ ተተካ ይመስላል። ያንጊዜ ደግሞ በኢሊፕ-አኩሱም አብዲ-ኤራ በንጉሥ ማናና እንደ ተተካ ይመስላል። ይህ ንጉሥ ማናና በኢሊፕ-አኩሱም መንግሥት ከ1803 እስከ 1791 ዓክልበ. ግ. ቆየ፤ ሱሙ-አቡምንም ከባቢሎን ወደ ደር እንዳባረረው ይባላል። የዚህም «ማናና» መታወቂያ ከ«ማናማልቴል» ጋር አንድላይ አይሆንም ለማለት አንችልም። የአሁን ሊቃውንት ይህን «ኢሊፕ-አኩሱም መንግሥት» ደግሞ «የማናና መንግሥት» በሚል መጠሪያ ይሉታል።

በዚህ ወቅት ብዙ ነገሥታት በመስጴጦምያም ሆነ በግብጽ ቶሎ እየሞቱ ነበር። በኩፋሌ በሚገኘው ዜና መዋዕል ይህ ከመምከሮን (ግሪክ፦ ማካማሮን) ዘመን ጋር ልክ ይስማማል፤ በቤሮሶስም አቆጣጠር ይህ ወቅት ከ«ማሜሉስ» (ወይም «ማሚጦስ») ጋር ይስማማል። ነገር ግን እነዚህ ምንጮች ስለ ኹኔታው ብዙ አያብራሩንም።

ቀዳሚው
ኢቱር-ሻማሽ
ኪሱራ ንጉሥ
1836-1805 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ሻራሥዩሩም

የውጭ መያያዣ

ለማስተካከል
  1. ^ Proceedings of the Society of Biblical Archaeology, Volume 21 1891 ዓ.ም. (እንግሊዝኛ)