ሄርኩሌስ ሊቢኩስ ወይም ሊብዩስ ጣልያናዊው መኖኩሴ አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ በ1490 ዓ.ም. ባሳተመው ዜና መዋዕል ዘንድ፣ በጣልያን ሀገር የነገሠ ንጉሥ ነበር። በሮሜ አፈ ታሪክ ደግሞ የሄራክሌስ ስም «ሄርኩሌስ» ነበረ።

የስማግሌው ሄርኩሌስ ምስል

በአኒዩስ ጽሑፍ መሠረት፣ ሄርኩሌስ የኦሲሪስ አፒስ ልጅ ነበር። አባቱ ኦሲሪስ የግብጽ ፈርዖን ሲሆን በ2003 ዓክልበ. ግድም በቲፎን ተገደለ። ልጁ ሄርኩሌስ ግን የአባቱን ቂም በቅሎ ቲፎንን ገደለውና ለአጭር ጊዜ ፈርዖን ሆነ። ቶሎ ግን ለግብጽ ተገዥ ወደ ሆኑት አገራት ሄዶ አመጸኛ አገረ ገዦቹን አስወጣቸው። ቡሲሪስን ከፊንቄ (ከነዓን)፣ ሌላውን ቲፎን ከፍርግያ (ማዮንያ)፣ ሚሊኑስን ከቀርጤስአንታዮስን ከሊብያ አስወጣቸው። ከዚያ ፫ቱን ሎምኒኒዎች ከእስፓንያ አስወጥቶ በፈንታቸው ሂስፓሉስን ንጉሥ ሆኖ ሾመው። ከዚያ በኬልቲካ (ፈረንሳይ) አለፈና የንጉሣቸውን ኬልቴስን ልጅ ጋላጠያን አግብቶ ጋላጤስን ወለደችለት። ከዚያ ሄርኩሌስ ለ፲ ዓመት ያህል በጣልያን ንጉሥ ሌስትሪጎን ላይ ጦርነት አድርጎ አሸነፈውና በ1992 ዓክልበ. ግድም ዘውዱን ተከተለው።

ለ፳ ዓመታት ጣልያንን በሰላም ገዝቶ ብዙ መንደሮች ሠራ። በ1973 ዓክልበ. ግድም ግን የጊጋንቴስ ወገን እንደገና ጦርነት ጀመሩ። በ1968 ዓክልበ. ግድም አጠፋቸውና እንደገና ሌላ 30 አመታት ገዛ። በ1938 ዓክልበ. ግድም ልጁን ቱስኩስዶን ወንዝ ጠርቶ የጣልያን ንጉሥ አድርጎ ወደ እስፓንያ ተመለሰና የልጁን ልጅ ሂስፓኑስን በዙፋን ተከተለው። በዚህ ወቅት ከሠሩት ከተሞች ባርሴሎና በሄርኩሌስ እንደ ተሠራ የሚል ልማድ አለ። በ1929 ዓክልበ. ግድም ሄርኩሌስ ዓረፈና በጋዲር እንደ ተቀበረ አኒዩስ ይለናል።

ዮሐንስ አቬንቲኑስ ባሳተማቸው መዝገቦች ውስጥ ስለ ሄርኩሌስ ሊቢኩስ ትንሽ ዝርዝሮች ይጨመራሉ። በፍርግያ በሌላው ቲፎን ፋንታ ኦምፋሌን አሾመ። ሄርኩሌስ ደግሞ በጀርመን ሲቆይ የጋምብሪቪዩስ ሴት ልጅ አራክሳን አግብቶ አራት አለቆች ወለደችለት፦ ቱስኩስ፣ ትንሹ ስኩቴስ፣ አጋጡርሲስ፣ ፔውኪንገር፣ ጉጦ ናቸው ይጽፋል።

በታራጎና እስፓንያ ከ«ሄርኩሌስ መቃብር» ከተገኙት «ግብጻዊ» ቅርሶች መካከል አንዳንዱን ያሳያል።

በ1842 ዓ.ም. አንድ መቃብር ቦታ በታራጎና እስፓንያ ተገኝቶ የሄርኩሌስ መቃብር እንደ ነበር የሚል ማስታወቂያ ታተመ። በዚሁ መቃብር ያለው ጽሑፍ በግብጽኛ እና በኢቤርኛ ሲሆን ሄርኩሌስና ወገኑ ከግብጽ ወደ እስፓንያ ስለ መድረሳቸው እንደ ነበር ተባለ። ሆኖም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የአውሮፓ ሊቃውንት ይህ ሃሣዊ ሥነ ቅርስ እንደ መሰላቸው አሳወቁ።

ቀዳሚው
ሌስትሪጎን
የራዜና (ጣልያን) ንጉሥ
1992-1938 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ቱስኩስ
ቀዳሚው
ሂስፓኑስ
ሂስፓኒያ ንጉሥ
1938-1929 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ሄስፔሩስ