ዩፒቴር ኬልቴስፈረንሣይ አፈ ታሪክ የኬልቶች (በጋሊያ፣ አሁንም ፈረንሳይ አገር) ፱ተኛ ንጉሥ ነበረ። ስለርሱ አገሩ ወይም የአገር ክፍል ስሙን «ኬልቲካ» አገኘ፤ ሕዝቡም ከእርሱ «ኬልቶች» ተባሉ። ኬልቴስ የሉኩስ ተከታይ ሲሆን በአብዛኛው ምንጭ የሉኩስ ልጅ ይባላል፤ አንዳንድ መጽሐፍ ግን ኬልቴስ የ2 ባርዱስ ሕፃን ልጅ ስለ ሆነ ሉኩስ በእንደራሴነት ብቻ ገዛ ይላል ።

በኬልቴስ ዘመን በእረኞች ቸልተኝነት ታላቅ እሳት ፒሬኔ ተራሮችን እንዳቃጠለ ይፃፋል። ስማቸው «ፒሬኔ» ለኚህ ተራሮች የሆነላቸው ከዚያ እሳት መሆኑ ይባላል። በአንዳንድ ምንጭ ኬልቴስ ጎረቤቶቹን ወርሮ ወደ ኢቤሪያ (እስፓንያ) የላኩት ሠፈረኞች ኬልቲቤራውያን ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ወደ እስኩቴስ ተልከው እነዚህ «ኬልትስኩቴሳውያን» ተባሉ። ኬልቴስ ወንድ ልጅ ባይኖረውም አንዲት ሴት ልጅ ጋላጠያን ወልዶ ነበር። ሄርኩሌስ ሊቢኩስእስፓንያ ወደ ጣልያን በኬልቴስ ግዛት በኩል ሲመልስ ልዕልት ጋላጠያን አግብቶ እርሷ ልጁን ጋላጤስ ወልዳለት ነበር። ኬልቴስ ባረፈበት ጊዜ የልጁ ልጅ የሄርኩሌስ ልጅ ጋላጤስ ተከተለው።

በአንድ ታሪክ ስለ ግዛቱ ተጨማሪ ዝርዝር ይሰጣል። ቋንቋቸው ከእርሱ «ኬልቲክ» ተባለ፤ ጽሕፈትም ከግራ ወደ ቀኝ እንዲሄድ አሻሸለው። ሕብረተሠቡን በአራት መደቦች እነርሱም ቄሳውንት፣ ጦረኞች፣ ነጋዴዎችና ሠፈረኞች መደባቸው። እያንዳንዱ መንደር በየዓመቱ ተሰብስቦ አለቃቸውን ይመርጡ ነበር፤ አለቃውም መሬቱን ማካፈል ነበረበት። አለቃውም የያንዳንዱ ቤተሠብ መኖርያ ከጎረቤቱ ሦስት ጫማ እንዲሆንና በየዓመቱ ወደ አዲስ ቦታ እንዲዛወር ማረጋገጥ ነበረበት። ሁለት ጉባኤዎች አቆመ፦ አንዱ የቤተሠብ አለቆች ብቻ፣ አንዱም አካለ መጠን ወንድ ሁሉ ነበር። ለዚያው ጉባኤ ሥነ ሥርዓቱ እንዲህ ነበር፦ ወንዶቹ ሁሉ በሜዳ በክብ ነገር ይሰብስቡ፤ አለቆች በመካከላቸው ይሁኑ፤ የመናገር መብት በማዕረግ ቅድምትነት ነው፤ ስዎቹ ቃሉን ባይቀበሉስ በጩሀታቸው ተናጋሪው ዝም ይበል፤ አለዚያ ግን ቃሉን ከወደዱት ማሣርያዎቻችውን በጋሻዎቹ ላይ በመጋጭ ድምጽ ያሰሙ። በዚህ ሂደት ንጉሡ «የሕዝቤ ሥልጣን በኔ ላይ ካለኝባቸው ሥልጣን አያንስም» ብሎ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ዘንድ ንጉሥ ኬልቴስ ሲያርፍ ዕድሜው 107 ዓመት ነበር። [1]

ቀዳሚው
ሉኩስ
ኬልቲካ (ጋሊያ) ንጉሥ
1986-1952 ዓክልበ. ግድም (አፈታሪክ)
ተከታይ
ጋላጤስ
  1. ^ የፈረንሳይኛ ታሪክ 1798 ዓ.ም.