ፋይጦን
ፋይጦን (ግሪክኛ፦ Φαέθων) በግሪክ አፈ ታሪክ የሚታወቅ ሰው ነው።
በትውፊት ዘንድ የፀሐይ አምላክ ሄሊዮስ እና የክሊመኔ ልጅ ነበረ። ክሊመኔ የኢትዮጵያ ንጉሥ «ሜሮፕስ» ንግሥት ትባላለች። ፋይጦን ግን አድጎ አባቱ በዕውኑ ሄሊዮስ እንደ ነበር ማስረጃ ፈለገ። ስለዚህ አባቱ ሄሊዮስ የፀሐይቱን ሠረገላ እንዲነዳ ፈቀደው። ፋይጦን ሠረገላውንም ሲነዳ፥ አልቻለበትምና ፀሐይቱ ወደ ምድር ከመጠን እንድትቀርብ አመጣት። ስለዚህ ነው የአይቲዮፒያ (አፍሪቃ) ስዎች ቆዳ የተቃጠለ እንዲሁም ሳህራ በረሃ የተፈጠረ የሚል ትውፊት ነበር። የአማልክት አለቃ ዜውስ ግን ፋይጦንን በመብራቅ ገደለውና ከሠረገላው በኤሪዳኑስ ወንዝ ወደቀ። የዚህ ወንዝ መታወቂያ ፖ ወንዝ በጣልያን አገር መሆኑ ባብዘኛው ይታመን ነበር። እህቶቹ ሲያልቅሱለት ልብን ዛፎች ሆኑ እምባዎቻቸውም ወርቃማ የዛፍ ሙጫ (አምኒት ወይም በግሪክ «ኤሌክትሮን») ሆኑ። ይህ ትውፊት በተለይ በአረመኔው ጸሐፊው ኦቪድ ጽሑፍ ይታወቃል።
ከዚህ ባሻገር አኒዩስ ዳ ቪቴርቦ እና ዮሐንስ አቨንቲኑስ ባሳተሙት መረጃዎች ዘንድ፣ ፋይጦን እንደ ታሪካዊ ግለሰብና የሕዝቡ አለቃ ይታያል። ሚሪና ከአማዞኖቹ ሠራዊት ጋር በከነዓን ባለፈችው ወቅት ካባረረቻቸው ነገዶች መካከል ነበሩ። የፋይጦን ወገን ከከነዓን በመርከብ ወጥተው ለብዙ ዓመታት መኖሪያ ሲፈልጉ በሜድቴራኔያን ባህር ተንቀዋለሉ። በመጨረሻ በ2108 ዓክልበ. ግድም ወደ ጣልያን አገር መጥተው የራዜና ንጉሥ ማሎት ታገስ ከፖ ወንዝ ስሜን እንዲኖሩ ፈቀደላቸው። በኋላ በ2079 ዓክልበ. ግድም ፋይጦን ልጁን ሊጉር በዚያች አገር («ሊጉርያ») ትቶ ግማሽ ሕዝቡን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እንደ ፈለሱ ደግሞ ይጻፋል። ለመሆኑ በዚያው ዘመን ወደ ኩሽ መንግሥት የገባ የከነዓን ትውልድ «ዋቶ» የተመዘገበ ነው። ዋቶና ሕዝቡ በግብጽና በሱዳን ረሃብ አገኝተው እስከ ደጋ ድረስ መንገዳቸውን ቀጠሉና በዚያ ሠፍረው የወይጦ ሕዝቦች ወላጆች ሆኑ ይባላል።