የየጁ ሥርወ መንግሥት ከ18ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ተጠናክረው ኢትዮጵያን በእንደራሴነት ሲያገለግሉ የነበሩ ራሶችን የሚገልጽ ነው። በዚህ ዘመን የጎንደር ነገስታት ሃይል እጅግ ከማሽቆልቆሉ የተነሳ እኒ እንደራሴወች የፈለጉትን ከስልጣን የማንሳትና የፈለጉትን የመሾም ሃይሉ ነበራቸው። ስለዚህም የአገሪቱ መሪ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከየጁ ስርወ መንግስት እንደራሴወች፡ ራስ ዓሊ ትልቁ ራስ ዓሊጋዝ ራስ ጉግሣ ራስ ይማም ራስ ማርዬ ራስ ዶሪ ራስ ዓሊ ትንሹ

የየጁ መሪወች አብዛኛውን ጊዜ የየጁ ኦሮሞ ተብለው ቢታወቁም አነሳስቸው በበለጠ እጅግ የተወሳሰበ ነው። የጁወች በድሮ ዘመን ደቡብ ሴማዊ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች ነበሩ። የሚኖሩበትም አገር ቀወት ይባል ነበር፤ ይህም በይፋትሸዋ ነበር። የግራኝ አህመድ ሰራዊት እኒህን ህዝቦች በቀወት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳገኛቸው ሺሃብ አድ-ዲን የተሰኘው ዜና መዋዕል ጸሃፊው ዘግቧል። ከዚህ በኋል በ16ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ የጁወች ብዙ ኦሮሞወችን ተቀብለዋል። ስለዚህም በቀጣዩ ዘመናት የየጁ ኦሮሞወች ተባሉ።

ዶናልድ ክርሚ የተባለ የታሪክ ጸሃፊ ሲዘግብ

በግራኝ አህመድ ወረራ የተሳተፉት ሙስሊሞች ዘላኖች፣ ከብት አርቢወችና አራሾች ነበሩ። አራሾቹ ወደ ደጋው ክፍል ለቀው በመሄዳቸው ዘላኖችና ከብት አርቢወች በተለቀቀው ቦታ ላይ በስፋት ሊሰራጩ ቻሉ። የኤል-እጁ (العجو = al-`ijju) ጉዳይ ከዚህ አንጻር ሲመረመር ይህን ጉዳይ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ኢል-እጁ በይፋትቀወት የሚባል ቦታ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ነበሩ። አገራቼውም በጣም ለም ከመሆኑ የተነሳ ትንሹ ጎጃም ተብሎ ይታወቅ ነበር። በአህመድ ግራኝ ወረራ ዋዜማ ክርስቲያን ነበሩ ግን ከአጠገባችፈው ይኖሩ ከንበሩ አማራወችና ሙስሊሞች የተለየ ቋንቋ ነበራቸው። ከወረራው በኋላ አብዛኛው ክፍል እስልምናን ይቀበል እንጂ መሪወቻቸውና ትንሹ ክፍል ክርስቲያን እንደሆነ ቆይቷአል። አብዛኞቹም አህመድ ግራኝን በመከተል በጊዜው አማራ ተብሎ የሚታወቀውን ክፍል ለመውረር እረድተዋል።
እንዴት የቃዋቶቹ የጁወች ወደ አንጎት እንደፈለሱና በዚያም መኖር እንደጀመሩ አይታወቅም ነገር ግን የወሎ የጁወች አያቶች እንደነበሩ ጥርጥር የለም። የጁወች የግራኝ ወታደሮች ቢሆኑ ኖሮ ግራኝ ሲባረር የከባቢውን ክርስቲያን በቀል መቛቋም አይችሉም ነበር። ስለዚህም በብዛት ተነቅለው ወደ አንጎት ተሰደዋል ወደሚለው አስተሳሰብ ያመላክታል። ከአህመድ ውድቀት በኋላ ወደ አገራቸው ቀዋት ያልተመለሱበት ምክንያት ከአዋሽ ማዶ የመጡ ሙስሊሞች አገራቸው ላይ በመስፈራቸው መሆን አለበት። በአሁኑ ጊዜ የጁወች እራሳቸው የዘር ምንጫቸውን በአህመድ ግራኝ ዘመን አንጎት ከሰፈረው ከሼክ ኡማር የመዛሉ። ኦሮሞወች እኒህን የጁወች "ዋራ ሼክ" በማለት ይጠሩዋቸዋል። የጁወች በአሁኑ ዘመን አማርኛን ሲናገሩ ከጎረቤቶቻቸው መረዋውጫሌወሎ ኦሮሞወች ለየት ያለ ባህርይ ነው። [1]

ሽብ አድ ዲን የተሰኘው የግራኝ አህመድ ዜና መዋዕል ጸሃፊ በቀወት የአህመድና የየጁ ሰወችን ቃለ ምልልስ እንዲህ ሲል መዝግቧል፦

የጁወቹ የክርስቲያን ልብስ ልብሰዋል። ኢማሙም አላቸው "በአላህ! ከየጁ ቋንቋ በቀር በሌላ ቋንቋ እንዳትናገሩ!" [2]
ተራኪው ( አላህ ይባርከው) እንዲህ ሲል ተናገረ <<በመንገድ ላይ ሳለን አንዲት ክርስቲያን ሴት ዴጋላን የተባለው መስፍን መስሏት እየጮኸች ወደ ኢማሙ መጣች። በቀረበችውም ጊዜ በየጁ ቋንቋ ሊያወራት ሞከረ። በመስሊም ቋንቋ መልሶ ተናገረ፣ ንብረቷም እንዲወሰን አዘዘ። ቋንቋውን ስለተረዳች ወደኋላ ሄዳ ተቀመጠች አለችም <<እኒህ ሙስልም ናቸው>> ነገር ግን ማንም ትኩረት አልሰጣትም ። [3]
ወደ እስልምና የተቀየሩት የየጁ ክፍል የሆኑት የቀወት ሰወች አሉ <<እኛ እስላም ነን፣ አካባቢያችንንም ስለዚህ ስንጠብቅ ነበር። አንተ እስክትመጣ በጥበቃ ላይ እያለን አንድስ እንኳ ክርስቲያን ወደኛ ቢመጣ እንገለዋለን። >> ኢማሙም በጣም ተደስቶ መሪያቸውን የክብር ካባ አለበሰው። በዚህ ዘመን የቀወት አካባቢ በካሊድ አል ዋረዲ ይመራ ነበር። ኢማሙም ይህን ሰው በነሱ ላይ የሾመው አካባቢውን ሙስሊም ያደረገው እርሱ ስለነበር ነበር። ሆኖም ግን ይህ መሪ በበሽታ ስለሞተ በሻራ በሱ ቦታ ተሾመ።ቀወት በጣም ደስ የሚል አገርና አበሾቹም ስለለምነቱ <<ትንሹ ጎጃም>> ብለው ይጠሩታል። በሻራም ከየጁ ወታደሮች በመሆን ወደ ነሱ አገር ዘምቶ በዚያ ተቀመጠ።[4]

ከላይ ቀወት የሚለው ቃል ለቦታና ለነዋሪው ህዝብ አንድ ላይ ለመግለጽ ጸሃፊው ተጠቅሞታል። የየጁ ክፍልና የዚሁ አገር ይመስላል። የጁ እንግዲህ ከሙስሊሞቹ የተለየና እንደ አርጎባይፋትአማርኛሃራሪ ከደቡብ ወሎ እስከ ሃረር ድረስ የደቡብ ሴም ቋንቋ ኮሪደር የፈጠረ ነበር። የጁወች ግማሽ እስላም ግማሽ ክርስቲያን መሆናቸው በርግጥም ከላይ ለቀረበው ጽሁፍ የበለጠ ድጋፍ ይሰጣል፡ ይሄውም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት እኒህ ነገዶች በአብዛኛው ክርስቲያን ነበሩ።

ታሪክ አጥኝው ዶናልድ ክርሚ እንዲህ ይላል፦

ከ1800 በኋላ ዋናወቹ በዜና መዋዕሎች ሰፍረው የምናገኛቸው ኦሮሞወች ከየጁ የተገኙት ዋራሼክ ቤተሰቦች ናቸው። ትልቁ ራስ አሊ ይህን ስርወ መንግስት የመሰረተው በ1780ወቹ ሲሆን እስከ 1850ወቹ ድረስ ቤ/ሰቦቹ የክርስቲያኑን ደጋ ክፍል ሊቆጣጠሩ ችለዋል። መርዕድ ወልደ አረጋይ በሚገባ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት እኒህ ህዝቦች ደቡብ ሴማዊ ቋንቋ እንደሚናገሩ አሳይቷል። ምንም እንኳ ከዚህ ዘመን በኋላ ከኦሮሞወች ጋር በብዛት ቢጋቡም እና ከነበሩበት አገር ተነቅለው ቢጠፉም ክርስትናን የመያዝና ሴሜቲክ ቋንቋን የመናገር አዝማሚያ እስከ አሁን ድረስ ይታይባቸዋል። [5]


ማጣቀሻወች

ለማስተካከል
  1. ^ merid wolde aregay
  2. ^ Futuh al-habesh (552)
  3. ^ Futuh al-Habesh (553)
  4. ^ Futuh al-Habesh (665)
  5. ^ Donald Crummey