የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤዎች

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በየጊዜው ከጻፏቸው ታሪካዊ ደብዳቤዎች (በተቻለ መጠን በቀጥታ ከአማርኛው የተወሰዱ )እኒህ ንጉሠ ነገሥት ታላቅና ብልህ መሪ፣ አገር ወዳድ፣ ሃይማኖተ ጽኑዕ እና የዘመኑን የአውሮፓውያንን ተንኮለኝነት በጥልቅ የተረዱ ኢትዮጵያዊ ንጉሠ ነገሥት እንደነበሩ መገንዘብ እንችላለን።

ወደ ሮማ ሊቀ ጳጳስ ሌዎን ፲፫ ኛ ለማስተካከል

ይኼ ደብዳቤ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የአድዋ ጦርነት ባከተመ በወሩ የተጻፈ ሲሆን፣ በራሳቸው በንጉሠ ነገሥቱ ቃላት፣ የአውሮፓውያንን ተንኮለኝነት፣ የኢጣልያን ተንኳሽነት በአጭሩ የጦርነቱን መንስዔና የራሳቸውንም ቆራጥነትና ብልህነት በሦስት ገጽ ደብዳቤ እንማራለን። ለዚህ ምላሽ መነሻ የሆነው ምርኮኞች ኢጣልያውያንን ለማስፈታት ጳጳሱ የላኩላቸው የመጽንዖ ደብዳቤ መሆኑን መገመት ይቻላል። ወዲያውም የጳጳሱ መልክት በክርስቲያንነት መንፈስ ማስመሰያም የተሞላ እንደነበር ከዚህ ከምኒልክ ደብዳቤ እንገምታለን።

 
ገጽ ፩
 
ገጽ ፪
 
ገጽ ፫

ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥትኢትዮጵያ

ይድረስ ከሮም ሊቀ ጳጳሳት ሌዎን ፲፫ ኛ፤ ሰላም ለርስዎ ይሁን

ክቡር ሊቀ ጳጳሳት ሆይ።

በዚህ ደብዳቤ ቀጥሎ የሚጻፈውን ግፌን አስታውቅዎታለሁ። የኢትዮጵያ ነጻነቷና ራሷን የቻለች መንግሥት ባጠገቧም ጎረቤት የሌላት መሆኗ አስቀድሞ በዮሮፓ መንግሥታት ሁሉ የታወቀ ነው። ከግራኝ ዠምሮ እስካሁን በአሕዛብ እጅ ተከባ ዘወትር በጦርነት ድካም ነው ኑሯችን። ከዮሮፓ የጦር መሳሪያ አስመጥቼ ሠራዊቴን ዘወትር ከጦርነት ድካም አሳርፋለሁ ስል ከንጉስ ዑምበርቶ አባት (ዳግማዊ ቪክቶር ኢማኑኤል ጋራ የፍቅርን ነገር ዠመርኩ። ንጉሥ ዑምበርቶም መንግሥት በያዙ ጊዜ እኔም እንደአባቴ ፍቅርን እወዳለሁ ብለው ቢልኩብኝ እኔም እንደአባትዎ ታፈቀሩኝ እሺ ብዬ ፍቅርን ተቀበልሁ። ኮንት አንቶኔሊ የሚባል የኢጣልያ ሰው በገንዘብዎ ጠበንጃ ልግዛልዎ ቢለኝ ብዙ የዝሆን ጥርስና ወርቅ ሰጥቼው ይዞ ሄዶ ከንጉሥ ዑምበርቶ አስፈቅዶ ገዝቶልኝ ቢመጣ ከመንግሥት ፈቃድ በማግኘቱ እጅግ ደስ አለኝ። ሁለተኛም ንጉሥ ዑምበርቶ ኮንት አንቶኔሊን የመንግሥት መልክተኛ አድርገው ወደኔ ሰደዱት። ተልኮ ያመጣውም ቃል ይህ ነው። ነጋዴም እንዲነግድ የጦር መሳርያ እንዳይከለከል ይፈቀድልዋል። እርስዎም ባሪያ እንዳይሸጥ ይከለክላሉ በሌላ መንግሥት ያለ መሳርያ ሁሉ ብትፈልጉ በኛ በር ይወጣላችኋል አይከለከልም። እንደ ዮሮፓ ነገሥታት የተጠላው ውል(የውጫሌ ውል) በአምስት ዓመት ይለወጣል የተወደደው ይረጋል። ምጥዋ ሐሩር ሆኖብናል ለሰዋችን ማሳረፊያ ጥቂት ነፋስ ያለበት ሥፍራ እንዲሰጡን የፍቅርን ውል ይህን እናድርግ ብለዋል አለኝ። እሺ ይሁን ብዬ እኔም ለመንግሥቴና ለኔ የሚስማማና የሚጠቅም ቃል በአማርኛ በትክክል አድርጌ አስጥፌ ብሰጠው አስራ ሰባተኛው ክፍል ላይ ቃሉን በኢጣልያ ቋንቋ ለውጠው ከጥንት ዠምሮ ነፃ የነበረውን መንግሥቴን የሚያዋርድ የማይስማማኝ ቃል ቢሆንብኝ እኔ ባስጣፍኩት በአማርኛው ቃል ይርጋ ኢጣልያው ቋንቋ ከኔ ከአማርኛው ጋር ያልተካከለ ነው አሁንም በትክክል እናድርገው ብዬ ወደ ንጉሥ ዑምበርቶ ብልክባቸው ምላሽ ሳይሰጡኝ ቀሩ። እኔም ነገሩ ለተንኮል እንደሆነ አውቄ የክርስቲያን ደም በከንቱ እንዳይፈስ አስቀድሜ ለዮሮፓ ነገሥታት ሁሉ ከንጉሥ ዑምበርቶ በውሉ እንዳልተስማማን አስታወቅሁ፤ የእውነት ፍርድ አገኛለሁ ስል። ሁለተኛም አምስት ዓመቱ ሲደርስ የጠላነው እንዲቀር የወደድነው እንዲረጋ ሰው ይላኩልኝ ብዬ ብልክ እስከምላሹም አስቀሩት። ከዚህ ወዲህ ይልቅ ክፉ ነገር እየበረታ ሄደ። አሽከሬን ደጃች መሸሻን አለፍርድ አሰሩት። ልክ አበጅቼ የሰጠኋቸውን አገር አልፈው የሾምኩትን ሹም ራስ መንገሻን ወግተው አባረው አገሬን ትግሬን በሙሉ ያዙት። ከዚያ አልፈው ላስታ መሬት እስከ አሸንጌ ድረስ ወጡ። ከዚህ ወዲያ አገር የሚጠብቁ መኳንንቶች ከኔ ብሰድ አምባላጌ ላይ በር ይዘው ቆይተው ተዋጉዋቸው የእግዚአብሔር ኃይል በኔ ሰዎች አድሮ ድል አደረጉዋቸው። እኔም ወደዚያው ተከትዬ ብሄድ መቀሌ እርድ ገብተው አገኘሁ። ጦርነት ተሆነ ከትልቁ ጋር እዋጋለሁ እናንተ ክርስቲያኖች በወሀ ጥም አትለቁ ብዬ እስከ መሳሪያቸው ከእርድ አሰጥቼ ለጀነራል ባራቲዬሪ ሰደድኩለት። እኔም ከዚያ ተጉዤ አድዋ እከተማዬ ሰፍሬ ጀነራል ባራቲዬሪ እውነት የመሰለ የእርቅ ቃል ላከብኝ። እኔም እርቅ ከፈለጉ ብዬ ሠራዊቴን ቀለብ ሰድጄ ሣለ እንደ ዮሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቁኝ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሠግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ዠመረ። ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችንን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግኋቸው። ከዚያ ሄጄ አስመራንም የኔን አገር ሁሉ አስለቅቃለሁ ብዬ ተጉዠ ሣለሁ ጀነራል ባልዲሤራ በኢጣልያ ሠራዊት ሁሉ ላይ ተሹሜ መጥቻለሁ ንጉሥ ዑምበርቶም ሲለዩኝ እርቅ ነውና እምፈልግ እርቅ አድርግ ብለውኛል ብሎ በማጆር ሣልሳ እጅ ወረቀት ቢልክብኝ እኔ በወደድሁት ከታረቃችሁ የሚስማማኝ ቃል ከሆነ እውነተኛ ሰው አዲስ አበባ እከተማዬ ድረስ ይምጣና ይጨርስ ብዬ እኔም ወደከተማዬ ተመልስኩ። እስካሁን በትግሬ አለሥራት ያለቀው መኳንንትና ባላገር የውሮፓ ነገሥታትና መኳንንት ሁሉ የተደረገውን ግፍ አመለክታለሁ። የኢጣልያ ገንዘብ በላያችን ላይ የለብን፣ ካገራቸውም ድንበራቸን የራቀ ነው። ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ ነፃነቱና ራሱን የቻለ መንግሥት የሆነውን በተንኮል ሊወስዱት እንዴት ይቻላቸዋል፡ ይህን የግፍ ፍርድ በሙሉ ልቦናዎ በውል እንዲመለከቱት ተስፋ አለኝ። ኢጣልያኖች ግን ይኸን ሁሉ ግፍ ሲያደርጉብኝ እነሆ እኔ የማደርገው የነበረ እነሱን ማክበር ሲመጡ በሥራት መቀበል ሲመለሱ በሥራት መሸኘት። ደግሞ በተሰጠኝ ሥልጣን ሁሉ የባሪያን ንግድ መከልከል በኔ መንግሥት እንፈዲ መሐመድ ብቻ የባሪያ ንግድ አልተው ቢለኝ ስለዚህ አውሳ ጦር ሰድጄ አስወጋሁት። ይህ ፈቃድ የኔ ብቻ አይደለም የመላ ዮሮፓም እንደሆነ አውቃለሁ። በመጋቢት፳፫ ቀን በመቀሌ ሰፈር በ ፲፰፻፹፰ ዓመተ ምሕረት ተጻፈ ማኅተም

ወደ ሮማ ሊቀ ጳጳስ ስለአድዋ ምርኮኞች ለማስተካከል

 

ማኅተም፡ ምኒልክ

ማኅተም፡ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ (ባለ አንበሳ)

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ

ይድረስ ወደተከበሩ የተቀደሱ የሮም ሊቀ ጳጳሳት ሌዎን ፲፫ ኛ

ሰላም ለርስዎ ይሁን።

የከበረው ያባትነትዎ ደብዳቤዎ ባቡነ መቃርዮስ እጅ ደረሰልኝ። በዚህም ደብዳቤዎ የቀድሞ መላላካችንን አሳምሮ የሚያስታውስ እግዚአብሔር ከኔ እጅ የጣላቸውን ስለኢጣልያ ምርኮኞች የቸርነት ሥራ እንድሰራ የሚያመለክት መሆኑን በጣም አየሁ። ደግሞም የከበረ ቅድስናዎ ከአቡነ መቃሮስ የበለጠ ነገሩን በጣም አስረድቶ አጣፍጦ ሀሳብዎን የሚናገር መላክ እንዳይቻልም አወቅን። የክርስቲያን ሁሉ አባት የላከው እጅግ የሚያስደንቅ ደብዳቤዎን ባነበብኩ ጊዜ ልቤን መታው። ዳግመኛም የከበረውን የመልክተኛዎን የቃል ንግግር በሰማሁ ጊዜ ልቤ ቅድስናዎ በማክበር ለለመኑኝ ጉዳይ ለመፈጸም ጨክኖ ነበር። እኔ ሣልፈልገው በዚህ በከፋ ጦር ደማቸው ለፈሰሰ በከንቱ ላለቁት ወታደሮች እጅግ አለቀስሁ። ነገር ግን ቅድስናዎ የተመኙትን ለፈጸም የኢጣልያ መንግሥት ያልታሰበው የዛሬ ሥራቸው የማያስፈጽመኝ ሆነ። ይህነንም ማለቴ የእርቅ ፈቃድና በደህና ለመላላክ ካሳዩኝ በኋላ ሥራቸው በጦርነት እንዳለኝ አድርገው ይሄዱ ዠመር። አሁንም የሚገባኝ ንጉሥነቴና የሕዝብ አባትነቴ ይህን አውቀ በእጀ ያለውን የእርቅ መያዣ መልቀቅ የማይቻለኝ ሆነ። ቅድስናዎ ያሰበውን ሀሳብ ደስ ለማሰኘት የኔንም መልካሙን ሀሳብ ለመፈጸም ከለከለኝ። በክርስቲያንነቴና በንጉሥነቴ ልብ አውጥቼ አውርጄ ሳበቃ የፍቅሬን ምልክትና ብዙ ማፍቀሬን ሌላ ቀን አደርገዋለሁ ማለት ስለሆነብኝ ዛሬ ሳይሆንልኝ መቅረቱ እጅግ ያሳዝነኛል። እግዚአብሔር አደራ የሰጠኝ መንግሥቱን የሕዝቤን ነፃነት የምፈልግ ስለሆንሁ በክርስቲያኖች ሁሉ በማክበር የሚሰማውን የቅድስናዎ ድምጽ ለኛ ብለው እንደሚያሰሙልኝ ተስፋ አለኝ። ይህ የሆነ እንደሆነ ከዘመዶቻቸውም ለተለዩ ምርኮኞች በቅርቡ ለመመለስ እንዲመቸን ማድረግዎ ነው። ነገር ግን ይህ ነገር እስኪጨረስ ድረስ ከኔ ዘንድ ያሉትን ምርኮኞች እንደ ክርስቲያን ሥራ ከዚህ ቀደም ጠብቄ በመልካም አድርጌ እንዳኖርኋቸው ይልቁንም ከእንግዴህ ወዲህ ስለርእዎ(ስለ እርስዎ) ፍቅር በጣሙን ጠብቄ በደህና አሣምሬ እንዳኖራቸው በዚህ አይጠርጥሩኝ። በመስከረም፳፪ ቀን ባዲስ፡ አበባ ከተማ ተጻፈ። በ፲፰፻፹፱ ዓመተ ምሕረት


 

ጥር 7፣ 1879 ዓ.ም. የተጻፈ። ስለ ሐረር ዘመቻ የሚያትት።