የእስክንድርያ ማስተማርያ ቤት
የእስክንድርያ ማስተማርያ ቤት በእስክንድርያ፣ ግብጽ በጥንት (54-373 ዓም ያህል) የተገኘ የክርስትና ሥነ መለኮት ትምህርት ተቋም ነበረ።
ተቋሙን የመሠረተው የኢየሱስ ሐዋርያ እና መጀመርያው የእስክንድርያ ጳጳስ፣ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ በ54 ዓም እንደ ሆነ ተጽፏል። የተቋሙ መጀመርያው መሪ በኋላ የእስክንድያ ፮ኛው ጳጳስ የሆነው ዩስቱስ እንደ ተሾመ ይታመናል።
ተቋሙ ያስተማረው ከሥነ መለኮት፣ መጽሐፍ ቅዱስና ክርስትናን ጭምር፣ የግሪክኛና የሮማይስጥ ስነ ጽሁፍ፣ ሥነ ጥበብ፣ ስነ አመክንዮ፣ ሥነ ቁጥርና ስነ-ተፈጥሮ ጥናቶች ነበሩ። ለዕውሮችም ማስተማርያ አገልግሎት አቀረቡ።
በፓንታይኖስ መሪነት (173-182 ዓም) ተቋሙ ስለ ትምህርቱ ዝነኛ ሆነ። ፓንታይኖስ በክርስትና ከመጠመቁ በፊት፣ የግሪኮች «ስቶዊሲሲም» ፍልስፍና ተከታይ ሆኖ ነበር። ፓንታይኖስ የግሪክ ፍልስፍና ከክርስትና ርዕዮተ አለም ጋር እንዳዋሐደ ይታስባል።
ቅሌምንጦስ ዘእስክንድርያ ከ182-194 ዓም በተቋሙ መሪነት ተከተለው። ብዙ አረመኔዎች በዚያን ጊዜ ለትምህርት ስለመጡ ከፍልስፍና መሠረት ጀምሮ የክርስትናን ትምህርት ያሳውቃቸው ነበር። በ194 ዓም የሮሜ መንግሥት ቄሣር በክርስቲያኖች ላይ ስላዘረጋው ማሳደድ፣ ቅሌምንጦስ ለጊዜው ከእስክንድርያ ሸሸ። እሱም የጻፋቻው ትልቅ መጻሕፍት ተርፈውልናል።
የቅሌምንጦስ ተከታይ ኦሪገኔስ በመከራ ጊዜ ቢሆንም ተቋሙን በ195 ዓም ዳግመኛ አቆመ። ኦሪገኔስ ደግሞ ብሉይ ኪዳን በስድስት ትይዩ ዕብራይስጥና ግሪክኛ ትርጉሞች (ሄክሳፕላ) ያሳተመው እና ብዙ አንድምታ የጻፈው ዝነኛ መምህር ነው።
በ373 ዓም በተካሄደው በቁስጥንጥንያ ጉባኤ፣ የጵጵሳት ቅድምንትነት ለሮሜ ፓፓ፣ ከርሱም ቀጥሎ ለአንጾኪያ ጳጳስ እንዲሰጥ የሚል ብያኔ ወረደ። ስለሆነም፣ የእስክንድርያ ጳጳስ የቀድሞ ቅድምትነቱን በማጣቱ ፣ በእስክንድርያ ከተማ ውስጥ ትልቅ ሁከት ደረሰ። በዚያም ጊዜ በተደረገው ጉዳት የማስተማርያ ተቋሙ ጠፋ።
በ1885 ዓም በካይሮ የተመሠረተው የቅብጢ ስነ መለኮት መንፈሳዊ ተቋም ከጥንታዊው ተቋም ግንኙነት እንዳለው ይግባኝ ባይ ነው።
ሌሎች ታዋቂ ተማሮች / አስተማሮች
ለማስተካከል- ኦማኒዮስ - ፪ኛው የተቋሙ መሪና ፯ኛው እስክንድርያ ጳጳስ
- ማርቅያኖስ - ፫ኛው መሪና ፰ኛው ጳጳስ
- ዩሊአኑስ - ፲፩ኛው ጳጳስ
- አቴናጎራስ ዘአቴና - ለቄሳር ስለ ክርስትና አቤቱታ የጻፈው ነው።
- ሔራክላስ - ፯ኛው መሪና ፲፫ኛው ጳጳስ
- እስክንድሮስ ዘኢየሩሳሌም - የኢየሩሳሌም ቆሞስ
- ዲዮናሲዮስ - ፰ኛው መሪና ፲፬ኛው ጳጳስ
- ጤዎግኖስቶስ ዘእስክንድርያ - ፱ኛው መሪና የአንድምታ ጸሃፊ
- ፒየሪዮስ - ፲ኛው መሪና የአንድምታ ጸሐፊ
- አኪላስ - ፲፩ኛው መሪና ፲፰ኛው ጳጳስ
- ጴጥሮስ ተፍጻሜ ሰማዕት - ፲፪ኛው መሪና ፲፯ኛው ጳጳስ
- እለእስክንድሮስ 1ኛ - ፲፱ኛው ጳጳስ
- አትናቴዎስ ሐዋርያዊ - ፳ኛው ጳጳስ እና ጸሐፊ
- ጢሞቴዎስ 1ኛ - ፳፪ኛው ጳጳስ
- ቄርሎስ ዓምደ ሃይማኖት - ፳፬ኛው ጳጳስ እና ጸሐፊ
- ዲዮስቆሮስ 1ኛ - ፳፭ኛው ጳጳስ
- ግሬጎርዮስ ዘናዚያንዞስ - የቁስጥንጥንያ ጳጳስ
- ዲዲሞስ ዕውሩ - ፲፭ኛው መሪ እና ጸሐፊ