የሎውናይፍ (ዶግሪብኛ፦ ሶምባኬ) በካናዳ ስሜን-ምዕራብ ግዛቶች ውስጥ ዋና ከተማ፣ እንዲሁም አንድያ ከተማ ነው። ከስሜናዊ ክበብ 400 ኪ.ሜ (250 ማይል) በስተደቡብ፣ በታላቅ ስለይቭ ሐይቅ ስሜን ዳርቻ ላይ፣ በየሎውናይፍ ስላጤ ምዕራብ ላይ፣ በየሎውናይፍ ወንዝ አፍ አጠገብ ይገኛል።

የ«የሎው ናይፍ» ትርጉም ከእንግሊዝኛ «ቢጫ ቢላዋ» ሲሆን ይሄው ስያሜ በዙሪያው ከሚገኙት ዴኔ ኗሪዎች ደረሰ፣ እነሱም የ«ቢጫ ቢላዎች» ወይም የ«መዳብ» (የሎውናይቭዝ ወይም ኮፐር) ዴኔ ጥንታዊ ሕዝብ ተብለዋል። እነዚህ በአርክቲክ ውቅያኖስ አካባቢ ከተገኘው መዳብ ማዕድን ወስደው ዕቃዎችንም ሰርተው ይነግዱበት ነበርና። የከተማው ሕዝብ ቁጥር ባለፈው 2008 ዓም ቆጠራ 19,569 ሰዎች ነበር። ከስሜን-ምዕራብ ግዛቶች አስራ አንድ ይፋዊ ቋንቋዎች መካከል፣ ፭ቱ በብዛት በየሎውናይፍ ሊሰሙ ይቻላል፤ እነሱም ቴኔ ሱጢኔኛ፣ ዶግሪብኛ፣ ስለይቪኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ናቸው። የከተማ ስም በዶግሪብኛ «ሶምባኬ» ማለት «ገንዘቡ ያለበት» ነው። አሁን የየሎውናይቭዝ ዴኔ ብሔር አባላት በአቅራቢያው ባሉት በዲሎ እና በደታህ ሠፈሮች ይገኛሉ።

ወርቅ በአቅራቢያው ከተገኘ በኋላ በ1926 ዓም የተቋቋመው ሲታመን፤ ሆኖም በውሃ ዳርቻ ዙሪያ የንግድ እንቅስቃሴ እስከ 1928 ዓም ድረስ አልተጀመረም። ከዚያ በቅርቡም የሎውናይፍ የግዛቶቹ የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል ሆነ፤ በ1959 ዓም ደግሞ የሰሜናዊ ምዕራብ ግዛቶች መቀመጫ ከተማ ሆኖ ተሰየመ። በ1980ዎቹ እ.ኤ.አ. ላይ የወርቅ ምርት እያለቀ፣ የሎውናይፍ የማዕድን ከተማ ከመሆኑ የመንግሥት አገልግሎት መኃል ወደ መሆን ተሸጋገረ። ሆኖም በ1983 ዓም አልማዝ ከከተማው ስሜን ከተገኘበት ጀምሮ፣ ይሄ ለውጥ ይመለስ ጀመር። ባለፉት ቅርብ ዓመታትም ላይ፣ ቱሪዝምመጓጓዣ፣ እና ኮሙኒኬሽን ዋና የየሎውናይፍ ኢንዱስትሪዎች ለመሆን ጀምረዋል።