ውክፔዲያ:እኛና የኛ ተራሮች ክፍል አራት

እኛና የኛ ተራሮች

ለማስተካከል

(ክፍል አራት)


ተራራ፤ የከፍታ፣ የበላይነት፣ የክብር … ምልክት ነው። ነገሥታት፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ ታላላቅ ሠዎች፣… በተራራ ይመሰላሉ። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ መሪዎቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ የፖለቲካ መሪዎቻችንና ራሳቸውን አንቱ ያሉ ምናምንቴዎቹንም እንቃኛለን።

የኛዎቹ እንደራሴዎች

አጀንዳ አሲዙልኝ

ትዝ ይላችሁ ይሆን? ለሸንጎ አባልነት ልትወዳደሩ ስትሉ የአንድ ሺህ ሰው ፊርማ ያስፈልጋችሁ ነበር። ፓርላማ ተቀምጣችሁ ጥቂት ሰዎች አጀንዳ አሲዘው ሲጨቃጨቁ እናንተ ከመሰላቸታችሁ የተነሳ አስሬ ስታዛጉ እነዛ የፈረሙላችሁና እንደራሴ ሁነኝ ብለው የመረጧችሁን ሰዎች እንድታስቧቸው ላስታውሳችሁ?

ድህነት ያደቀቀው፣ ለእርፍ ከደረሰበት ጀምሮ ኋላ ቀር የእርሻ መሳሪያ ጉልበቱን የመጠጠው፤ አዳፋ ጋቢውን ተከናንቦ፤ የሳር ጎጆው ታዛ ስር ቁጭ ባለበት መጥታችሁ ያስፈረማችሁት ደሀ ገበሬ ሲፈርምላችሁ ምን ልታደርጉለት እንደነበር ትዝ ይበላችሁ።

ሳሎኗም፣ መኝታዋም ፣ማጀቷም፣ በረቷም ከሆነው ጎጆዋ ገብታችሁ በጭስ እየተጨናበሰች ቤተሰቧን ልታበላ ደፋ ቀና የምትለዋን እናት ምድጃዋጋ አግኝታችሁ ፊርማዋን የተቀበላችኋት አድናቂዎቿ ስለሆናችሁ እንዳልሆነ አስታውሱ።

ለሰዓታት ተጉዛ ውኃ ለመቅዳት የምትመላለሰው ኢትዮጲያዊት ኮረዳ መደቧን በእበት እየለቀለቀች አግኝታችሁ ፈርሚ ስትሏት እጇን አለቅልቃ ቀሚሷ ላይ አደራርቃ መፈረሚያውን የተቀበለቻችሁ ፓርላማ ገብቶ እንዲተኛ ፍቀዱለት ብላ መፈረሟ አልነበረም። ኮበሌው እንደ ቅም አያቱ ያጨደውን በበሬ ሲያበራይ የፈረመላችሁ ቃል ገብታችሁለት ነው።

ከከተማ የተወከላችሁትስ የፈረሙላችሁን ሰዎች ላስታውሳችሁ?

የወፍ ቤት በምታክለው ቤቷ ደጃፍ ለሥራ የቆመችውን ሴተኛ አዳሪ የመፈረሚያ ወረቀቱን ያቀበላችኋት ለጋብቻ ፊርማ አልነበረም አይደል? በኖሩበት ስፍራ ለዘመን ዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በግንበኝነት አገልግለው እርጅና ያለ ጡረታ ከሥራ ያገለላቸውን ስታስፈርሟቸው ምን ነበር ቃላችሁ? እናንተ ልጅ ሆናችሁ ጀምሮ የምታውቋቸው ሶስቴ ስም የቀየሩት መጀመሪያ ኩሊ፣ ከዚያ ወዛደር፣ አሁን ደግሞ ላብ አደር የተባሉትን ሸክም ሲጠብቁ ሄዳችሁ ስታስፈርሟቸው ንግግራችሁ ተሸክመህ ፓርላማ አድርሰኝ ነበር?


እንሾሽላና ብርጉድ ነጋዴዋን ለማስፈረም ጣታቸውን የማሕተም ቀለም ስታስረግጧቸው የጥፍር ቀለም እንዲሆናቸው ነው? የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዋን ምን ብላችሁ ነው የሰበካችኋት? ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ጋቢ የሚሰራው ሸማኔን ስታስፈርሙትስ?

የቦታ ግብር፣ የሽያጭ ግብር፣ የንግድ ፈቃድ ግብር፣ የማዘጋጃ ቤት ግብር፣ የግዢ ግብር፣ የፀጥታ ግብር፣ የንግድ ቦታ ኪራይ፣ የንፅሕና መቀጮ፣ የግብር ጊዜ እላፊ መቀጮ፣… የቀበረውን ነጋዴ ስታስፈርሙት ከአንተ የበለጠ ኃብታም እንድሆን ብላችሁት ነበርንዴ?

የቤንዚን ዋጋ አናቱ ላይ ያናጠረበትን ታክሲ ነጂ ስታስፈርሙት “ታክሲ አንድ ሰው ፓርላማ” ያላችሁት ነው የሚመስለው

ለመሆኑ ፊርማ ከሰበሰባችሁ በኋላ ያንን ኢትዮጲያዊ ደግማችሁ ያያችሁት መቼ ነው? የምርጫው ሰሞን? በተናጠል ያታለላችሁትን ሰብስባችሁ ዋሻችሁት። ለመሆኑ ሽማግሌ ስታታልሉ ትንሽ አታፍሩም? በዕድሜ አያት የሚሆናችሁን ሠው እንደራሴ እንሁንህ ብላችሁ ፈርሞላችሁ ስታሞኙት አይከብዳችሁም?

ፓርላማ የገባችሁትኮ ለማዳመጥ አይደለም። ለማዳመጥማ ያ በበሬ ሲያበራይ ያስፈረማችሁት ኮበሌም በብርቄ ሬዲዮ ያዳምጣል። የከተማውም ሠው በቲቪ እያየ ያዳምጣል የፈረመላችሁኮ እንደራሴ፣ እንደኔ፣ ሆናችሁ ተናገሩልኝ ብሎ ነው። በእንደራሴነት ያገኛችሁት ምቹ ኑሮ ምክንያቱ ያ እንወክልህ ያላችሁት ኢትዮጲያዊ ፊርማ ነው። የዛን ኢትዮጲያዊ አጀንዳ ማስያዝ በጎ ፈቃዳችሁ ሳይሆን ግዴታችሁ ነው። በያንዳንዷ በምትጠጧት ውስኪ ውስጥ የዛች መደቧን በእበት የምትለቀልቀው ኢትዮጲያዊት ዕንባ አለበት። በምትበሉት ጥሬ ስጋ ውስጥ የዛች ሴተኛ አዳሪ የተሸጠው ስጋዋ አለበት። የምትነዱት መኪና ነዳጁ የዛ የግንበኛ ደም፣ የምትተኙበትን አልጋ የተሸከመው ያየፈረመላችሁ ኩሊ ነውና የታለ ታዲያ የዛ ኢትዮጲያዊ ድምፅ ?

በዛ ኢትዮጲያዊ ተጠቅማችሁ ሸንጎ ገብታችሁ ቱባ ደሞዝ ታገኛላችሁ። ያ ኢትዮጲያዊ በናንተ የተጠቀመው ምንድነው? አሁን በወረዳ፣ በክልል፣ በብሔራዊ ሸንጎ መቀመጫ ተሰጥቷችሁ ዳሩ ምንም ነገር ስትናገሩ አንሰማም። ተመችቷችኋል። እጅግ ጥቂት ሠዎች ስለ ወከላቸው ሕዝብ እያነሱ ሲያወሩ አትባንኑም? ያ ታዛው ስር ተቀምጦ የነበረው አረጋዊ አጀንዳው ምን ነበር? ያቺ ምድጃ ጋ ያገኛችኋት እናት በቃ ከዛ የተሻለ ኑሮ አይገባትም? ጥያቄዋ ምን ነበር? ዝምታ? የምትናገሩት ካጣችሁ አጀንዳ አሲዙልኝ።

የወከላችሁ ደሀ ገበሬ ጨቅላ ልጁ የከብት ጭራ ተከትሎ ወጥቶ ገና የእናት ፍቅር ባልጠገበበት ዕድሜ ሜዳ አቋርጦ፣ ሸጥ ተሻግሮ፣ አቀበት ወጥቶ ከብት ሲያሰማራ ዶፍ ዝናብ ወርዶበት ገሣ ውስጥ ቁጭ በሚልበት ቅፅበት እናንተ የት ናችሁ?

ይህ ሕፃን ማታ ከብት ሲመልስ አንድ በግ ጠፍቶበት በየጥሻው ሲፈልግ የጅብ ድምፅ ሲያስለቅሰውና በዛ በጨለማ የዕውር ድንብሩን በባዶ እግሩ ሲሮጥ እንቅፋት ጥፍሩን ሲነቅለው በዛች ወቅት የትኛው ቡና ቤት የየት ሀገር ውስኪ እየጠጣችሁ ነው?

እናንተ እንደራሲዎች ያ ምስኪን እረኛ እንቅፋት የነቀለውን ጣቱን በቅጠል አሥሮ እሳት ዳር ሲቀመጥ እናንተ ምን አይነት ሶፋ ላይ ቁጭ ብላችሁ ቪዲዮ እየተመለከታችሁ ነው?

እናንተ የሸንጎ አባላት በተቋጠረለት አሹቅ የዋለው ያ እረኛ የሳማ ወጥ ሲበላ እናንተ ለዕራት ጠረጴዛ ላይ ያቀረባችሁት ቁርጥ ሥጋ የፍየል ነው የበሬ? ያ እረኛ ከእንሥራ የምንጭ ዉኃ ሲጠጣ እናንተ ከፍሪጅ ያወጣችሁት ሀይላንደር ነው አቢሲኒያ?

የዚህ ተስፋ የለሽ ሕፃን እናትና አባት ፊርማ ሸንጎ አድርሰዋችሁ ለዚህ አብቅቷችሁ እንዴት ዝም ብላችሁ ትቀመጣላችሁ? የቤት ሰራተኛችሁ ሳትሰራ ዝም ብላ ተኝታ ትከፍሏታላችሁ? ሰራተኛችሁ ስራዋን ጠረጴዛ ላይ ማሳየት እንዳለባት ከእናንተም አጀንዳችሁን መስማት አለብን። አጀንዳ ካጣችሁይህንን እረኛ አጀንዳ አስይዙልኝ። ሕፃኑ ሊሠራ አይገባም በሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ውስጥ የተፃፈ ሕግ አለ። ሕፃናት መጫወት፣ መማር፣ ፍቅር ማግኘት እንጂ ፍየል እያባረሩና ከቀበሮ ጋር እየተፋጠጡ ማደግ የለባቸውም።

በሰለጠነው ዓለም እረኝነት የሕፃናት ሥራ አይደለም!!!!!። በብዙ ሀገሮች ምን እንደሚደረግ ላሥረዳ።

ከብቶች ለግጦሽ እንዳይለቀቁ ሕግ ያስገድዳል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከብቶች ከአመት አመት ተመሳሳይ ቦታ ስለሚሰማሩ መሬቱ ላይ ያለውን ሣር ከነሥሩ ስለሚነጩት ቦታው ሳር የማያበቅል ይሆንና አንደኛ ከብቶች ዳግም አይሠማሩበትም፣ ሁለተኛ አፈሩ በነፋስና በጎርፍ ይሸረሸርና ወደ በረሀማነት ይቀየራል።

ይህንን በረሀነት ለመከላከል የግጦሽ ስፍራ ተከልሎ ሳር እንዲያድግበት ይደረግና ሳሩ ታጭዶ ወደ መከማቻ ይገባል። ያው መሬት በዓመት ሶስት ጊዜ ሳር ሊታጨድበት ይችላል። ይህ በማያመችበት ሁኔታ ለግጦሽ የሚውለውን መሬት ለሦስት ከፍሎ አጥሮ በየሦስት ወር ፈረቃ ከብቶች እንዲግጡት ማድረግ ይቻላል። በሦሥተኛ ደረጃ የመሬት ችግር ባለበት አካባቢ ለእርሻ የሚጠቀሙበትን መሬት በማይታረስበት ወቅት በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሳር ወይንም የጓሮ አትክልት ዘርቶ ለከብቶች ማዘጋጀት ይቻላል። እርሻውን አለስልሶና አፅድቶ ታጥሮ ቢተውም በራሱ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ሳር ማብቀል ይችላል።

ይህ አሰራር የመሬቱን አፈር ከመሸርሸር ያድነዋል፣ ከብቶች ከዓመት እስከ ዓመት ሳር ያገኛሉ፣ ዋናው ደግሞ ሕፃናት ከእረኝነት ወደ ትምህርት ገበታ ይሔዳሉ። እኔ ቀና ቀናውን መንገድ አስቀመጥኩት እንጂ አፈፃፀሙ ቀላል አይሆንም። ግን ሊሆን የሚችል ነው። ዝርዝር አሠራሩን ማቅረብ ካለብኝ አፈፃፀሙ ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን እና ችግሮቹን እንዴት መወጣት እንደሚቻል የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በዝርዝር ላቀርብ እችላለሁ።

እናንተ ብቻ አጀንዳ አስይዙት እንጂ ከኔ ይየተሻሉ ስራውን የሚያውቁ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች አሉና አትቸገሩም። ያእረኛም እንደ ታላቅ ወንድሙ በበሬ ማበራየት የለበትም። እንደ አያቱ ሞፈር በበሬ ማስጎተት የለበትም። ዘመናዊ አስተራረስን እንዲማር እረኝነቱን ትቶ ትምህርት ቤት አስገቡት። ለመሆኑ ልጆቻችሁ ይማራሉ ወይንስ ይሠራሉ? እንግዲያውስ በፊርማው ተደላድላችኋልና ከናንተ ልጆች ይልቅ ቅድሚያ ሊሠጠው የሚገባው የዛ ገበሬ ልጅ ነውና አጀንዳ አሲዙልኝ።


temenew@yahoo.ca

ጠመኔ ነኝ

ከቶሮንቶ ካናዳ