ኩንታል
ኩንታል ማለት አሁን በተለምዶ የአንድ መቶ ኪሎግራም ክብደት መለኪያ ነው። በተለይ የእህል ምርት መለኪያ ነው።
የስሙ «ኩንታል» ታሪክ በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቷል።
- ሮማይስጥ፦ centenarius /ኬንቴናሪዩስ/ «የመቶ»
- የቢዛንታይን ግሪክኛ፦ κεντηνάριον /ከንቴናሪዮን/
- አረብኛ፦ قنطار /ቂንጣር/
- እንደገና ከአረብኛ ወደ ኋለኛ ሮማይስጥ፦ quintale /ኲንታሌ/
- ጥንታዊ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፦ quintal /ኲንታል/
- አማርኛ፦ ኩንታል
በአብዛኞቹ አገራት ዛሬ «ኩንታል» ለመቶ ኪሎ ክብደት ይጠቀማል፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ሕንድ፣ አልባኒያ፣ ፈረንሳይ፣ እስፓንያ፣ ዩክራይን፣ ቸኪያ፣ ኢንዶኔዥያ።
የፖርቱጋል ኩንታል ግን እንዲሁም የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ኩንታል 58 ኪሎ ያህል ነው።
ብዙ ሌሎች አገራት ከሮማይስጥ centenarius በሌላ መንገድ የመጣ ቃል centner /ሰንትነር/ ይጠቅማሉ። በፖልኛ፣ ስዊድኛ፣ በኦስትሪያ፣ ስዊስ አገር እና በቀድሞ ሶቭየት ኅብረት አገራት፣ ይህ ቃል (ጸንትነር / ሰንትነር) ለመቶ ኪሎ ይጠቀማል። በእስፓንያ centena /ሴንቴና/ በድሮው ትርጉሙ መቶ ፓውንድ ወይም 46 ኪሎ ማለት ነው፤ በጀርመን አገር Zentner /ጸንትነር/ ለ50 ኪሎ መደበኛ ሆኖአል፤ የመቶ ኪሎ መለኪያ በጀርመን አገር አሁን Doppelzentner /ዶፐልጸንትነር/ ይባላል።