ኤንመርካርሱመር (ሳንጋር) ነገስታት ዝርዝር ዘንድ የኡሩክ (ኦሬክ) ከተማ መስራች ነበረ። በዚያ ዝርዝር ጽህፈት 420 (ወይም በሌላ ቅጂ 900) ዓመታት እንደ ነገሰ ይላል። ደግሞ አባቱ የኡቱ ልጅ መስኪያጝካሸር ወደ ባሕር ገብቶ ኤንመርካር መንግስቱን ከኤአና ከተማ እንዳመጣ ይጨምራል።

የኤንመርካር ስም በሌላ የሱመር ጽሑፍ ደግሞ ተገኝቷል። «ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ» በተባለው ተረት እሱ የኡቱ ልጅ ይባላል። (ኡቱ በሱመር እምነት የጸሓይ አምላክ ነበር።) ይህ ተረት የሰው ልጅ ልሳናት መደባለቁን ይናገራል። ኡሩክን ከመመስረቱ በላይ ታላቅ መስጊድ በኤሪዱም እንዳሰራ ይተረታል። ለመሆኑም፣ አራታ እንዲገዛለት የሚለው መልእክት በአፍ መናገር ስለሚከብድ፣ ኤንመርካር ጽሕፈት በሸክላ ጽላት ላይ መጻፍ እንደ ፈጠረ ይላል።

በተጨማሪ በዚሁ ጽሑፍ ኤንመርካር የዙሪያው አገሮች ልዩ ልዩ ልሳናት እንደገና አንድ እንዲሆኑ ይጸልያል። እነዚህ አገራት ሹቡርሐማዚሱመር፣ ኡሪ-ኪ (የአካድ ዙርያ) እና የማርቱ አገር ናቸው።

ከዚህ በላይ የኤንመርካርን መንግሥት የሚገልጹ ሦስት ተጨማሪ ጽሑፎች አሉ። «ኤንመርካርና ኤንሱሕጊርዓና» የሚባል ተረት የኤንመርካርና የአራታ መቀያየም ሲገልጽ፣ ሐማዚ ተሸንፎ እንደ ነበር ይጠቅሳል። በ«ሉጋልባንዳ በተራራ ዋሻ»፣ ኤንመርካር በአራታ ላይ ዘመቻ ሲመራ ይታያል። አራተኛውና መጨረሻውም ጽላት፣ «ሉጋልባንዳና የአንዙድ ወፍ» ኤንመርካርና ሠራዊቱ በአራታ ዙሪያ ለ1 አመት እንደ ከበቡት ይላል። ለመሆኑ ኤንመርካር 50 አመት ከነገሰ በኋላ፣ የማርቱ ሕዝብ (አሞራውያን) በሱመርና በአካድ ሁሉ ተነሥተው ኡሩክን ለመጠብቅ ግድግዳ በበረሃ መስራት እንደ ነበረበት ይጠቅሳል።

በነዚህ መጨረሻ 2 ጽላቶች፣ ከኤንመርካር ጦር አለቆች አንድ የሚሆን ሉጋልባንዳ የሚባል ሰው ይተረታል። በሱመር ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ፣ ይህ ሉጋልባንዳ «እረኛው» ኤንመርካርን ወደ ኡሩክ ዙፋን ተከተለው። ይህ ሉጋልባንዳ ደግሞ በጊልጋመሽ ትውፊት በተባለው ግጥም ዘንድ የኋለኛው ኡሩክ ንጉሥ የጊልጋመሽ አባት ነበረ።

ዴቪድ ሮኅል የሚባል አንድ የታሪክ ሊቅ የኤንመርካርና የናምሩድ ተመሳሳይነት አመልክቷል። «-ካር» የሚለው ክፍለ-ቃል በሱመር ቋንቋ ማለት «አዳኝ» ነው። ኡሩክ ከተማ የተመሠረተ በኤንመር-ካር ነበር ሲባል፣ ደግሞ ናምሩድ፣ አዳኝ፣ በኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 10 ዘንድ ኦሬክን ሰራ። በሌላ ትውፊቶች ዘንድ ይህ ናምሩድ የባቢሎን ግንብ መሪ የሆነ ነበር። በተጨማሪም አቶ ሮህል የኤሪዱ መጀመርያ ስም «ባቤል» እንደ ነበር ያምናል፤ እዚያም የሚገኘው የግንብ ፍረስራሽ የባቢሎን ግንብ ፍርስራሽ መሆኑን ገመተ።[1] «ባቢሎን» ማለት የኤሪዱ መጠሪያ እንደ ነበር የሚል ማስረጃ በሌሎችም ጥናቶች አለ።[2]

ሮማዊው ጸሐፊ ክላውዲዩስ አይሊያኑስ በጻፈ አንድ ትውፊት ዘንድ (200 ዓ.ም. ግድም)፣ የባቢሎን ንጉስ «ኤወኮሮስ» የተከታዩን «ጊልጋሞስ» አያት ይባላል። ይህ «ጊልጋሞስ» ማለት የኡሩክ ንጉስ ጊልጋመሽ መሆኑን የአሁኑ ሊቃውንት ስለ ገነዘቡ፣ እንዲሁም «ኤወኮሮስ» ማለት ኤንመርካር ሳይሆን አይቀርም የሚል አስተሳሰብ ያቀርባሉ። ከዚህ በላይ የከላውዴዎን ታሪክ ጸሐፊ ቤሮሶስ በጻፈው ዝርዝር መሰረት፣ ከማየ አይህ ቀጥሎ የከላውዴዎንና የአሦር መጀመርያው ንጉስ «ኤወኮዮስ» ይባላል፤ ስለዚህ የዚሁ «ኤወኮዮስ»ና የናምሩድ መታወቂያ አንድ ናቸው የሚለው አሳብ ለረጅም ዘመን የቆየ ነው።

  1. ^ Legends: The Genesis of Civilization (1998) and The Lost Testament (2002) by David Rohl
  2. ^ "Babylon as a Name for Other Cities..." Archived ጁላይ 30, 2012 at the Wayback Machine p. 25-33. (እንግሊዝኛ)
ቀዳሚው
መስኪያጝካሸር (የኤአና ንጉሥ)
ኡሩክኤሪዱ ንጉሥ (ሉጋል) ተከታይ
ሉጋልባንዳ