ይድረስ ለወ/ሮ ሪታ ማርሊ


ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን የውድ ባለቤትዎን የሚስተር ማርሊን 60ኛ ዓመት የልደት በአል በቅድስቲቷ ሀገር ለማክበር አበቃዎ እላለሁ።

ከልደት በዓሉ 2 ሳምንታት አስቀድሞ የኢትዮጲያዊነት የክብር ዜግነት ከከንቲባው እጅ ሲቀበሉ እዛው አዲስ አበባ ነበርኩ። ልደቱንም እርስዎ እየጨፈሩ እኔ ታዳሚዎ ሆኜ አሳልፈነዋል።

ወ/ሮ ሪታ ኢትዮጵያ ማለት እንግዳ የሚከበርበት ሀገር ነው። ይህንን አስረጅ እየጠቀስኩ ልንገርዎ

የትኛውም ኢትዮጲያዊ ቤት እንግዳ ቢመጣ፣ የቤቱ የምግብ ታሪክ ይቀየራል። ዝንተ አለም ሽሮ የሚበላበት ቤት እንግዳ ሲመጣ ዶሮ ይታረዳል። ወይ ደሞ እንደ ቤቱ በጀት ከሉኳንዳ ስጋ ይገዛል። እንግዳ በፆም የማይጠራው ለክብሩ ተብሎ ነው። ሀበሽ ወገኔ ከቆሻሻ ጋር ከርሞ እንግዳ ሲጠራ የቤቱ ዕቃ ሁሉ ወጥቶ ቤቱ ይፀዳል። ቤቱን ቀለም የሚያስቀባም እንግዳ አይጠፋም።

ልጆች ያላዩትን ነገር የሚያዩበት ጊዜ ቢኖር እንግዳ ሲመጣ ነው። ወ/ሮ ሪታ፣ በኢትዮጲያ ዉስጥ የእንግዳ ቤት የሚባል ክፍል አለ። ሆቴል ቤት ውስጥ እንዳይመስልዎት እያንዳንዱ ከተሜ ነኝ የሚለው ኢትዮጲያዊ ቤት ውስጥ፣ ይህ ክፍል የግድ ይኖራል። ይህ ክፍል ከሌሎቹ ክፍሎች የተዋበና መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ነው።

ታሪክ ደግሞ አንዳንድ ነገር ልጨምርልዎት ድሮ ነው አሉ አያቴ ሲነግሩኝ፣ ፕሬዚደንት ኒክሰን ይመጣሉ ተብሎ የአዲስ ከተማ አጥሮች ሳይቀሩ ቀለም ተቀብተዋል።

ደርግ ጊዜማ እነ ኮንስታንቲቭ ቸርኔኮ፣ ሙአመር አልጋዳፊ ኤርክ ኮኔከር መጥተው፣ ይረግጡበታል የተባለው መንደር ሁሉ ይፀዳ ነበር።

1996ቱ የአፍሪካ ህብረት 2ኛ መደበኛ የመሪዎች ስብሰባ ሲደረግ ባይኔ ያየሁትን ትኩስ ዜና ላጫውትዎ አንድ የአፍሪካ መሪ ከቦሌ ይመጣል ተብሎ የአፍሪካ ጎዳና/ ከቦሌ አብዮት የሚወስደው መንገድ/ ለ2 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ከሁለቱም አቅጣጫ ተዘግቶ፣ በዛ ወቅት መንገዱ ውስጥ ገብተው የነበሩ መኪናዎች በየጥሻ ውስጥና በየሰዉ ግቢ ዉስጥ ተሰገሰጉ። የኔም መኪና ሜጋ ሕንፃጋ ገብታ ለሶስት ሰዓታት መንቀሳቀስ አልቻለችም።

ድንገት እንግዳው መጣ ሲባል ፖሊሶች እግረኞችን ባገኙት ክፍት ነገር ዉስጥ እየገፈተሩ አስገብተው ዘጉባቸው። በር በሌለበት ቦታ የነበሩ ደሞ ፊታቸዉን አዙረው እንዲቆሙ ተደረገ።

እዚህጋ አንድ አስቂኝ ነገር ተፈጠረ። አንድ ነጭ ከማኩሽ ሬስቶራንት ወጥቶ፣ እኛን አልፎ እንግዳዉን አስፋልት ዳር ቆሞ ይመለከት ነበር። እትዬ ሪታ አይግረምዎት ፈረንጁ እንግዳ ነው። እንግዳ ከቤተኛው ይልቅ እንደሚከበር ቅድም አጫውቼዎታለሁ።

አሁን ደሞ ኢትዮጲያዊ በእንግድነት በሚቆይበት ሀገር ያለዉን ክብር ላጫውትዎ

ከአስር አመታት በላይ ከሃገር ውጭ ኖሬአለሁ (በጀርመንና በካናዳ)። 6ሌሎች ሃገሮችን ተዘዋውሬ አይቻለሁ (ሩሲያዩክሬይንፖላንድሆላንድፈረንሳይግብጽዩናይትድ ስቴትስ) በየሄድኩባቸው ቦታዎች አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተዋርዶ አሊያም በፈቃዱ አንገቱን ደፍቶ ነው የሚኖረው።

ኢትዮጲያዊነት ክብር ነው ይባል በነበረበት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጲያውያንና ኢትዮጲያውያት ለክብራቸው ህይወታችዉን ይሰጡ ነበር። ዛሬ ኢትዮጲያዊነት የሚባል ክብር የለም። በኢትዮጲያዊነት መኩራት የመድረክ ወሬ ሆኗል። ጥቂት ከተመክሮዬ ላጫውትዎ።

ዲሴምበር 03 2001 በዩናይትድ ኤር ዌይስ በበረራ ቁጥር US 3193 16፡45 ላይ የአሜሪካ ግዛት ወደሆነችው ወደ ፊላደልፊያ በረራ ነበረኝ። አውሮፕላኑ 66 መቀመጫዎች ያሉት ነው። የመቀመጫ ቁጥር 22`ሲ ተሰጥቶኝ ወደፍተሻው ሳመራ ከፊት ለፊቴ የነበሩት በሙሉ ነጮች (ካኩዢያንስ) ነበሩ። ሁሉም እንደነገሩ ተፈትሸው አለፉ። እኔግን ፓስፖርቴን የተቀበለው ሰው ገልጦንኳን ሳያየው ከነጓዜ ወደ ጥብቅ ፍተሻ ተወሰድኩ። ራቁቴን ሆኜ ተበረበርኩ። ጫማዬን አውልቄ የተፈተሽኩት ያየታመነው ካኩዢያን ከፈረንሳይ በጫማው ቦንብ ይዞ ከመግባቱ 19 ቀናት ቀደም ብሎ ነው። በፍተሻው ወቅት የያዝኳቸው ወረቀቶች ሁሉ ተነበቡ። ብዙ መስቀለኛ ጥያቄዎች ቀረቡልኝ። ከሁለት ሰአታት ምርመራ በሁዋላ ይቅርታ ተጠይቄ የመቀመጫ ቁጥሬ ወደ 66 ተቀይሮ ወደ አውሮፕላኑ ተላኩ። መቼም ብዙ ጊዜ በአነስተኛ አውሮፕላን ተጉዘዋልና 66 ቁጥር የትጋ እንደሆነ ያውቃሉ።

እዚህጋ አመጽኩ። 65ቱም ሰዎች ወርደው ካልተፈተሹ ለህይወቴ አስጊ ነውና አልሳፈርም አልኩ።

እኔ በደንብ ስለተፈተሽኩ 65ቱም መንገደኞች በኔ ሰላማዊነት እርግጠኞች ናቸው። እኔ ግን በነሱ ሰላማዊነት እርግጠኛ አይደለሁም አልኩ። በዚህ ቀን በጥበቃዎቹ ላይ ብዙ ችግር ተፈጥሮ በመጨረሻ እንዲያዉም በአሜሪካ አውሮፕላን አልሄድም ብዬ በኤይር ካናዳ በበረራ ቁጥር AC 872 ተሳፈርኩ።

በወቅቱ በዌብሳይት ከኢትዮጲያውያን ጋር ብዙ ተነጋግሬበት። ሁሉም በሰው ሃገር ተዋርዶ ለመኖር እንደመጣ ነው የመሰከረልኝ። ይሄን ሁሉ መረጃ የላኩልዎ እርስዎንኳን ለኢትዮጲያዊነት ቢከራከሩ ብዬ ነው

እርስዎም እትዬ ሪታ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ብዙ መከራ ያያሉና ያስቡበት። ካናዳ ነዋሪ ሆኜ ግብጽ ለመሄድ ቪዛ ለማግኘት መከራ አለብኝ። ከካናዳ ኩባ ለመሄድ ቪዛ የሚጠይቀው ኢትዮጲያዊ ብቻ ነው። የካናዳ መኖሪያ ፈቃድ ኖሮን አሜሪካ ቪዛ የምንጠይቅ እኛ ብቻ ነን። ባንግላዴሽና ስሪላንካ እንኳን ቪዛ አያስፈልጋቸዉም።

እርስዎ የተከበሩ ሰው ስለሆኑ የተለየ መስተንግዶ የሚጠብቅዎ እንዳይመስልዎ ዋናው የያዙት ፓስፖርት ነው። ለዚህ ምሳሌ ልስጥዎ ፌብሩዋሪ 15 2005 አንድ በኦሎምፒክ ሜዳ አንበሳ የተባለ ኢትዮጲያዊን፣ የጀርመን የድንበር ፖሊስ ፓስፖርቱን ይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስደው ባይኔ ለማየት በቦታው የነበርኩ ሰው ነኝ። እትዬ ሪታ፣ በሮም አደባባይ በይሁዳ አንበሳ ሲያላግጡ የነበሩትን ኢጣሊያውያን በሻሞላ የቀላውን የዘርዓይ ደረስን ታሪክ አንብበው ይሆን? በዚህ ትውልድ ያለሁት እኔ፣ ህያዉ አንበሳ በፖሊስ ሲሄድ አንዲትም ቃል አልወጣኝም። ለዚህ ቂም አይያዙብኝ ለ12 አመታት ዜግነቴን ባለመቀየሬ መንገላታት በዝቶብኝ ዜግነቴን ለመቀየር ፕሮሰስ ላይ ነኝ።

ለመሆኑ ኢትዮጲያዊነት ሁለት መሆኑን ያውቁ ኖሯል? አንዱ በወረቀትም በልብም ሲሆን ሌላኛው በልብ ብቻ ነው። እነ አብዲሳ አጋ ዜግነታችሁን ወደ እንግሊዛዊነት ካልቀየራችሁ ተብለው እንዳልታሰሩ ያህል፤ እኔ ግን ዜግነቴን ለመቀየር ማመልከቻ አስገብቼ፣ ገንዘብ ከፍዬ 15 ወር ወረፋ የምጠብቅ ዜጋ ሆኛለሁ። ለምን አይበሉኝ በሰው ሀገር ብበደልም ይሁን ብዬ ወደ ሀገሬ ልመጣ ፓስፖርቴን ለማሳደስ ኢትዮጲያ ኤምባሲ ስሄድ የካናዳ መንግስት ኢትዮጲያዊ መሆንህን ይመስክርልህ የተባልኩ ሰው ነኝ።

አዲሳባም መጥቼ ነሐሴ 14 ከቀኑ 8 ሰአት 22 ማዞሪያ የሚገኘው ከቀረጥ ነጻ የሆነ አንድ የቱሪዝም መደብር እኔና አንድ ፈረንጅ ስንገባ ፈረንጁ ካለፍተሻ አልፎ እኔ መፈተሽ ነበረብኝ። ዘበኛው የሰጠኝ መልስ ፈረንጅ አይፈተሽም ነው።

ነሐሴ 18 1996 10 ሰአት አካባቢ ወደ ሂልተን ሆቴል ስገባ አንዱ ፈረንጅ አልፈተሽም ብሎ ገባ። ጥበቃዉም ብዙ አላሳሰበዉም ለቀቀው። እኔም እሱ ካልተፈተሸ አልገባም አልኩ። ሌላው ጥበቃ አይ እሱን ስለማውቀው ነው አለ። የፍተሻውን አስፈላጊነት ሳስረዳው የጥበቃው ሃላፊ ምንድነው ብሎ ነገሩን ባጭሩ እንደሰማ ዲፕሎማት ነው። አለ

ጥበቃዎቹ ራሳቸዉን እየተከላከሉ ነበር። እውነታው ግን ኢትዮጲያዊነት ክብር ማጣቱ ነው። እዛው ሒልተን ሆቴል ከሚሰሩ ጋርና ካንዳንድ ሰዎች ጋር ስለጉዳዩ ስንወያይ ብዙዎቹ እርስ በርስ ስለምንናናቅ ነው። አንዳንዶቹማ አዲስ ነህንዴ በየቢሮው ቅድሚያ የሚሰጠው ለፈረንጅነው ብለውኛል።

እትዬ ሪታ አንድ ሁለት ቀልድ ልጨምርልዎትና ላብቃ ጀርመን ሀገር ያለው የኢትዮጲያ ኤምባሲ ቅድሚያ የሚሰጠው ለጀርመናዊያን ነው። አዩት የኛን ነገር? በእንግድነትም ሄደን ባለሀገሩን እናስተናግዳለን። በአዲስ አበባ የሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ለካናዳዊ ነው።

በአንፃሩ ደሞ የዉጭ ሀገር ፓስፖርት የያዙ ኢትዮጲያውያን በክብር ይስተናገዳሉ። ታዲያ ክብር ያጣው ዜግነቱ አይመስልዎትም? ይህንን የተዋረደ ዜግነት በመምረጥዎ እንደ ባለቤትዎ ልወድዎ፣ በዚህ ኢትዮጲያዊ መሆን በዘቀጠበት ወቅት ኢትዮጲያዊነትን በመምረጥዎ እጅ ልነሳዎት ይገባል። እባክዎን እርስዎ በክብር የተቀበሉትን ዜግነት ላዋረደው ዜጋ ምክርዎን ይለግሱት።

እትዬ ማርሊ ጊዜ ቢኖረንና እርስዎ ሬጌ ቢጫወቱልኝ፣ እኔ ደግሞ በአለም ዙሪያ ያስናቀንን በጊነሥ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ ላይ ለ22 አመታት ክብረ ወሰን ስለ ሰበርንባቸው 8 ሬከርዶቻችን ባጫወትኩዎ ደስ ባለኝ ነበር። ለማንኛዉም እስቲ እድሜ ይስጠንና ቀጠሮ እንይዝበት ይሆናል። ለዛሬ በዚሁ ልለይዎት ።


ጠመኔ ነኝ ከቶሮንቶ ካናዳ

temenew@yahoo.ca