አለቃ ገብረ ሐና
ከህይወት ታሪካቸው ስንጀምር አንዳንዶች የአባታቸው ስም ደስታ ተገኝ ነው ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ገብረ ማርያም ነው ይላሉ። ምናልባት አንዱ የአለም ሌላው ደግሞ የክርስትና ስማቸው ሊሆን ይችላል። የተወለዱት በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በድሮው የደብረታቦር አውራጃ ፎገራ ወረዳ፤ ናብጋ ጊዮርጊስ በተባለው ቦታ በ1814 ዓ.ም. ነው። የመጀመርያ ትምህርታቸውን በአካባቢው ከቀሰሙ በኋላ ወደ ጎጃም ተሻግረው ቅኔን ተቀኙ። ከዚያም ወደ ጎንደር ከተማ ተመልሰው ከመምሕር ወደ አብ ወልደ ማርያም ጽዋትወ ዜማ፤ ከባሕታዊ ገብረ አምላክ አቋቋም፤ ከዐቃቤ ስብሃት ገብረ መድሕን ትርጓሜ መጽሐፍትን እንዲሁም ድጓን ተምረዋል። በእዚህ የሰፋ እውቀታቸው የተነሣ በ26 ዓመታቸው ጎንደር ሊቀካህናትነት ተሾመው ነበር። በዚህም ሹመት ለሰባት ዓመት ማገልገላቸው ይነገራል። በፍትሐ ነገሥት ሊቅነታቸው ደግሞ በዳኝነት እየተሰየሙ አገልግለዋል። አለቃ ገብረ ሐና ጨዋታ አዋቂነታቸው እየታወቀ የመጣው በዚህ ወቅት ነበር። በዚህም እውቀታቸው የትንሹ ዓሊ አጫዋች ሆኑ። አጼ ቴዎድሮስ ሥልጣኑን ሲይዙ አለቃን በቤተ መንግሥት አገኟቸው። አለቃ የቤተ መንግሥቱን ሰዎች በቀልዳቸው ሸንቆጥ ስለሚያደርጉ መስማማት አልቻሉም ነበር። እንዲያውም ዐጼ ቴዎድሮስ «ገብረ ሐና ፍትሐ ነገስቱን ጻፍ፤ ፍርድ ስጥ .. ገንዘብ ያውልህ፤ ቀልድህን ግን ተወኝ።» ሲሉ ተናግረዋቸው ነበር ይባላል። አለቃ ግን አላቆሙም።
ገብረ ሃና | |
ሀይማኖት | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና |
---|
በተለይም ደግሞ በንጉሡ ባለሟል በብላታ አድጎ ላይ «አድግ / በግእዝ አህያ ማለት ነው /» እያሉ በሚሰነዝሩት ትችት በተደጋጋሚ ተከሰው ዐጼ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀርበዋል። በመጨረሻ ቴዎድሮስ ክስ ሲሰለቻቸው ምላስ ቀርቶ ታገሉና ተሸናነፉ ብለው ፈረዱ። በዚህም ትግል ምሁሩ አለቃ ተሸነፉ። ንጉሡም እንግዲህ ምን ይበጅህ? ሲሉ ጠየቋቸው አለቃም «ድሮስ ትግል የአህያ ሥራ አይደል» ብለው በመመለሣቸው ከአካባቢያቸው ለማራቅ ሲሉ ንጉሡ ገብረ ሐናን ለትግራይ ጨለቆት ሥላሴ አለቃ አድርገው በመሾም ወደ ትግራይ ላኳቸው። ወደካቶሊክነት የተቀየረውና ከአንቷን ዳባዲ ጋር በዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን ስለሆነው ሁሉ ደብዳቤ ይለዋወጥ የነበረው የዋድላው ሰው ደብተራ አሰጋኽኝ ጥር 1858 ዓ.ም. ለአንቷን ዳባዲ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ በማለት ይህን ሁኔታ ገልጦት ነበር «አለቃ ገብረ ሐናን ንጉሥ መቱዋቸው። ወደ ትግሬ ወደ ላስታ ተሰደዱ። እጅግ ተዋረዱ እኔም በዋድላ አገኘኋቸው ወደ ቆራጣም ሄዱ» ሲል ጽፏል።
ደስታ እንዳለ ሁሉ መከራም ያለ ስለሆነ ሁለቱንም በጸጋ መቀበል የሰው ልጅ ሁሉ ግዴታ ነው። ካህናት በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ባመጹ ጊዜ በአድማው ካሉበት ካህናት መካከል አንዱ ገብረ ሐና መሆናቸው ስለታወቀ ዐጼ ቴዎድሮስ በአለቃ ገብረ ሐና ላይ አምርረው ሊቀጧቸው ዛቱ። አለቃም ሸሽተው ጣና ሐይቅ ሬማ መድኃኔዓለም ገዳም ገቡ። በዚያም ባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ የተባሉ የአቋቋም ሊቅ አገኙ። ሁለቱም ተወያይተው በጎንደር አቋቋም ስልት የመቋሚያውን የአካል እንቅስቃሴ ጨምረው ዝማሜውን አዘጋጁት (በኋላ ተክሌ አቋቋም እየተባለ የሚታወቀው ነው)። ባህታዊ ጸዐዳ «ከእንግዲህ እኔ ወደ ዓለም አልመለስም፤ አንተ ይህንን ስልት አስተምር» ብለው አለቃ ገብረሐናን አደራ አሏቸው። ከዐጼ ቴዎድሮስ ሞት በዃላ በ1864 ዓ.ም. ዐጼ ዮሐንስ ሲነግሡ ከገዳም ወጥተው ወደ ትግራይ አቀኑ። በመቀጠልም በቴዎድሮስ ቤተመንግሥት ሳሉ የሚያውቋቸው ምኒልክ በሸዋ መንገሣቸውን ተከትለው ሸዋ መጡ።
ዓፄ ምኒልክ በዓፄ ቴዎድሮስ ቤተመንግሥት ሳሉ አለቃ ገብረ ሐናን ስለሚያውቋቸው በደቡብ ጎንደር የሚገኘውን የአቡነ ሐራን ገዳም ሾሟቸው። በዚያም ጊዜ በአካባቢው ከባድ ርሃብ በመከሠቱ አለቃ ከገዳሙ ብር አንድ ሺ አውጥተው ለገበሬዎች አከፋፈሏቸው። በዚህም ተግባራቸው ተከስሰው ወደ አዲስ አበባ መጡ። የፍርድ ሚኒስቴር የነበሩት አፈ ንጉሥ ነሲቡ ስሕተት ነው ብለው ፈርደውባቸው ነበር። ነገር ግን ጉዳዩ በምኒልክ ዘንድ ስለተሰማ ወደ ዙፋኑ ችሎት ተሻገረ። ዐጼ ምኒልክም ይህ ተግባር ያሸልማል እንጂ አያስቀጣም ብለው በመፍረዳቸው አለቃ ነጻ ወጡ። ንጉሥ ምኒልክ አለቃን የእንጦጦ ራጉኤል አለቃ አድርገው ሾሟቸው። እርሳቸውም ትርጓሜ መጻሕፍትን ያስተምሩ ነበር። ጥቂት ጊዜ በአዲስ አበባ እንደ ተቀመጡ እንደገና ወደ ጎንደር ተመልሰው፤ ድንግልናቸውን አፍርሰው ወይዘሮ ማዘንጊያን አገቡና ተክሌ የተባለ አንድ ወንድ ልጅና በፍታ የተባለች ሴት ልጅ ወለዱ። አንዳንድ ሊቃውንት አለቃ ገብረ ሐና ሊቅ፤ መልከመልካምና የነገሥታቱ ወዳጅ በመሆናቸው በዚያ ዘመን የነበሩ ሴቶች ወዳጅነት ለማበጀት ይሻሙባቸው ነበር ይላሉ። አለቃ ድንግልናቸውን ያፈረሱት ሆን ብለው ሳይሆን እኔ አስፈርሰዋለሁ በሚል የወይዛዝርት ውድድር የተነሣ ነው ይባላል። የአለቃ መንፈሳዊ ሕይወት የተናጋው ከዚያ በዃላ ነው ይባላል። ተክሌ ለትምህርት ሲደርስ ከሌላው የቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር እርሳቸው ከባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ ጋር ሆነው ያዘጋጁትን ዝማሜ አስተማሩት። አለቃ ገብረ ሐና ደርቡሽ ጎንደርን ሲወርር ልጃቸውን ወደ ወሎ ልከው እርሳቸው ጎጃም ውስጥ ዘጌ ገዳም ገቡ። በዃላም ዐጼ ምኒልክ ደርቡሽን ለመውጋት ወደ ፎገራ መምጣታቸውን ሲሰሙ፤ ከተደበቁበት ወጥተው ንጉሡን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ምኒልክም እንደገና የራጉኤል አለቃ አድርገው ሾሟቸው። ልጃቸው አለቃ ተክሌ ወሎ ንጉሥ ሚካኤል ዘንድ እያሉ የተንታ ሚካኤል በዓል ሲከበር ከአባታቸው የተማሩትን ዝማሜ በተመስጦ አቀረቡት። ንጉሥ ሚካኤልም በዚህ ተደንቀው በዚያው በተንታ እንዲያገለግሉ አደረጉ። የተክሌ ዝማሜ በይፋ የተጀመረው ያኔ ነው ይባላል። በዃላ ራስ ጉግሣ የአለቃ ተክሌን ዝና ሰምተው ንጉሥ ሚካኤልን በማስፈቀድ ወደ ደብረ ታቦር አምጥተው የኢየሱስ ቤተክርስቲያን ሾሟቸው። አለቃ በአዲስ አበባ እያሉ ከመኳንንቱ ከመሳፍንቱ ጋር ያላስማሟቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። የመጀመርያው ትንባሆ ይጠጣሉ ተብሎ የተነገረው ሐሜት አንድ ቀን በቅኔ ማኅሌት ፒፓቸው ወድቆ በመጋለጣቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአድዋ ጦርነት ታላቅ ጀብዱ ለፈጸሙት ለደጃዝማች ባልቻ ዐጼ ምኒልክ የሚወዷትን ጎራዴያቸውን ሲሸልሟቸው «ወይ ጎራዴ ወይ ጎራዴ ከቤቷ ገባች» በማለት በሽሙጥ በመናገራቸው ባልቻ እገላለሁ ብለው ተነሡ። ይህም አልበቃ ብሏቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በነገር ተኳረፉና መላ የቤተመንግሥቱ ሰው አደመባቸው። ዐጼ ምኒልክ አለቃን ምን ቢወዷቸው በተለይ ከደጃች ባልቻና እቴጌ ጣይቱ ጋር የፈጠሩትን ጠብ አልወደዱላቸውም። በዚህ ምክንያት አለቃ ገብረ ሐና ከአዲስ አበባ ለቅቀው እንዲወጡ ተወሰነባቸው። በጎንደርና በወሎ ጥቂት ጊዜ ከሰነበቱ በዃላ ልጃቸውን ገብረ ሐና ሞተ ብለህ ተናገር ብለው አዲስ አበባ ላኩት። አለቃ ተክሌ ይህንን መርዶ በቤተመንግሥቱ ሲያረዱ ምንም እንኳ ገብረ ሐና ከብዙዎቹ ጋር ቢኳረፉም ታላቅ ሐዘን ሆነ። ከተወሰኑ ቀናት በዃላ አለቃ ራሳቸው አዲስ አበባ ገቡና ጉድ አሰኙ። ምኒልክም አስጠርተው ሞቱ ከተባለው በዃላ ከየት መጡ ቢባሉ «በሰማይ ጣይቱ የለች፤ ምኒልክ የለ፤ ጠጅ የለ፤ ጮማ የለ፤ ባዶ ቤት ቢሆንብኝ ለጠባቂው ጉቦ ሰጥቼ መጣሁ።» ብለው ሁሉንም አሳቋቸው። ጣይቱም መኳንንቱም ይቅር አሏቸው። አለቃ ገብረ ሐና እድሜያቸው እየገፋ አደብም እየገዙ መጡ አዲስ አበባ ተቀምጠውም ትርጓሜ መጽሐፍት ማስተማር ቀጠሉ። ዐጼ ምኒልክ የአብያተ ክርስቲያናቱን የግብዝና መሬት ለመኳንንቱ በመስጠታቸው ካህናቱ ምንም ባለ ማግኘታቸው የተቆጡት አለቃ ገብረ ሐና ተቃውሟቸውን በቀልድ ለዐጼ ምኒልክ አቀረቡ። ይህም ከወይዛዝርቱና ከመኳንንቱ ጋር መልሶ አጋጫቸው። ከዚህ በዃላ አዲስ አበባ መቀመጥ ስላልቻሉ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ደብረ ታቦር ተመለሱ። ያኔ ልጃቸው አለቃ ተክሌ ደብረ ታቦር ኢየሱስን እልቅና ተሾመው ነበር። ለጥቂት ቀናት ደብረ ታቦር ከልጃቸው ጋር ሰንብተው ወደ ትውልድ ቦታቸው ናባጋ ጊዮርጊስ መጡ። በእድሜያቸው መጨረሻ ዝምተኛ ሆነው ነበር ቀድሞ በሠሩት ሥራ እየተጸጸቱ አንደበታቸውን ከነገር ዘርቅ ከለከሉ። ከጥሩ ምግብና ከጥሩ መጠጥ ተቆጠቡ። ቅዱሳን መጻሕፍትን ሰብስበው «መሳቂያና መሳለቂያ አደረግዃችሁ» እያሉ ይቅርታ ይጠይቁ ነበር ይባላል። በዚህ ሁኔታ ከሰነበቱ በዃላ በ84 ዓመታቸው የካቲት 1898 ዓ.ም. ዐረፉ። አለቃ ገብረ ሐና በብዙ ሰዎች ዘንድ በቀልደኝነታቸው ይታወቁ እንጂ በቤተክርስቲያን ታሪክ ወደር ከማይገኝላቸው ሊቃውንት አንዱ ነበሩ። አለቃ ለማ ኃይሉ (የደራሲ መንግስቱ ለማ አባት) ሰለ አለቃ ገብረ ሃና ሊቅነት ሲናገሩ « የሞያ መጨረሻ እርሳቸው አይደሉም ወይ ? የሐዲስ መምህር ናቸው። የፍትሐ ነገስት መምህር ናቸው። መርሐ እውሩን፤ አቡሻሩን የሚያውቁ ባለሙያ ናቸው። ለዚህ ለዝማሜ እሚባለው ለመቋሚያ እገሌ ይመስለዋል አይባልም። ከገብረ ሐና ፊት የሚዘም የለም።» ብለዋል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴም «አለቃ ገብረ ሐና እጅግ የተማሩ የጎንደር ሊቅ ነበሩ። በዚህም በላይ ኃይለ ቃልና ጨዋታ ያውቁ ነበር» በማለት ይገልጿቸዋል። (ምንጭ (ዚና ሰኔ 1999)) ።በ1998 ዚና እንዳጻፈው ደግሞ አለቃ ገብረ ሃና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቅ ሲሆኑ አቋቋምና ዜማ ቅኔ ከእነ አግባቡ የሚያውቁ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል። አለቃ ባልሳሳት የነበሩበት በአጼ ምንይልክ ዘመን ይመስለኛል። በቅርቡ የሳቸውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ የታተመ ስለኆነ ስለሳቸውም ኆነ ስለሌሎች ባለ ታሪኮች ጥሩ ግንዛቤ ይኖረናል እላለሁ።