ናርመር
ናርመር ለሥነ ቅርስ የሚታወቅ የግብጽ የቀድሞ ዘመነ መንግሥት ፈርዖን ነበረ። ስሙ በግብጽ ሃይሮግሊፍ ሲጻፍ፣ የአምባዛ (አስቀያሚ የባሕር አሳ ወይም በግብጽኛ «ናር») ከመሮ (በግብጽኛ «መር») በላይ ነው። ከሔሩ (ወይም ሆሩስ፣ ሖር) ወገን በመሆኑ ስሙ በሙሉ «ሔሩ ናር-መር» (ወይም ምናልባት «ሔሩ መር-ናር») ነበረ።
የናርመር ዱላ የተባለው ቅርስ በዙፋን ሲቀመጥ የታችኛ (ስሜኑ) ግብጽ ዘውድ በራሱ ላይ ሲጫን ያሳያል። በሱም ዙሪያ የሚያገልግሉ ሰዎች አሉ። በላይኛው ተርታ አጫጭር ሰዎች ዓላማዎች ሲሸክሙ አንዱ «ሴት» ምልክት (አዋልደጌስ ወይም ቀበሮ)፣ አንዱም የጊንጥ ምልክት፣ ሁለቱም የሔሩ ምልክት (ጭላት) አለባቸው።
በ1890 ዓ.ም. በተገኘው የናርመር መኳያ ሠሌዳ በተባለው ቅርስ ላይ የናርመር መልክ በሁለቱ ገጾች ላይ ይታያል። በፊተኛው ገጽ ላይ የታችኛ ግብጽ ዘውድ (ቀዩ ዘውድ)፤ በጀርባውም ላይ የላይኛ ግብጽ ዘውድ (ነጩ ዘውድ) በራሱ ላይ ይታያል። ስለዚህ ሁለቱ ክፍሎች መጀመርያው ያዋሐደው ፈርዖን በተለመደው ታሪክ ሜኒስ ሲሆን፣ እርሱና ናርመር አንድ እንደ ነበሩ በሰፊ ይታመናል። ናርመር ታችኛ (ስሜን) እና ላይኛ (ደቡብ) ግብጽ ካዋሐደው አስቀድሞ የተለያዩ አለቆች እንደ «ንጉሥ ጊንጥ» ሸለቆውን በከፊል ይገዙ ነበር።
ቀዩ ዘውድ ባለበት ገጽ ላይ እንደ ተለመደው አጫጭር ሰዎች ያገልግሉታል። ባንዱ አገልጋይ አጠገብ ሁለት ሃይሮግሊፎች «ጨቲ» (ጸሐፈ ትእዛዝ ወይም አማካሪ) ይላሉ። በግብጽ ሥነ ቅርስ እስከሚታወቅ ድረስ የሃይሮግሊፍ አጠራር እንደ ድምጽ ፊደል (የግብጽኛ ተናባቢ ድምጽ ምልክቶች)
|
(ጭ፣ ት ) ሲጠቀም መጀመርያው ጊዜ ይህ ነው። ይህም የሚያሳየን፣ ሃይሮግሊፍ እንደ ፊደል መጠቀሙን በዚሁ ዘመነ መንግሥት አዲስ የተማረ ነገር መሆኑ ነው። ከዚህም በታች 2 ዘንዶ-ነብር በሠሌዳው ይታያሉ።
ከናርመር ዘመን በኋላ የነገሠው (የ1ኛ ሥርወ መንግሥት 2ኛው ፈሮዖን) በዛሬው የሥነ ቅርስ ሊቃውንት ዘንድ «አሃ» ወይም «ሆር-አሃ» ይባላል። በማኔጦን ዘንድ ከሜኒስ ቀጥሎ የነገሠው ፈርዖን «አጦጢስ» ሲሆን፣ በሌሎች ጥንታዊ የግብጽ ነገሥታት ዝርዝሮች መሠረት የ2ኛው ፈርዖንና የሜኒ ተከታይ ስም ቴቲ (ወይም ኢቴቲ) ተባለ። እያንዳንዱ ፈርዖን አያሌ ስሞች ስለነበሩት፣ በትክክል ለማለት ትንሽ ቢያስቸግርም በአብዛኛው አስተሳስብ በኩል ይህ ቴቲ እና አሃ አንድ ንጉሥ ነበሩ።
የውጭ መያያዣ
ለማስተካከልቀዳሚው (የለም) |
የግብፅ ሁሉ ፈርዖን 3101-3089 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ 1 ቴቲ |