ኅልዮት
ኅልዮት በብዙ ተሞክሮዎች ተፈትነው ሃሰት አለመሆናቸው የተረጋገጡ አመክንዮአዊና ስርአታዊ የሆኑ የትንተናና አንድን ኩነት ወይም ነገር ለመግለጽ/ለማብራራት የሚያገለግሉ ሃሳቦች ስብስብ ነው። ለምሳሌ የቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ኅልዮት ሰዎች እና ጦጣዎች ከአንድ የዘር ግንድ በዝግመተ ለውጥ እንደመጡ ያስረዳል። ይህ የዳርዊን የሃሳብ ስርዓት ኅልዮት ሊባል የቻለው ከሁሉ በፊት ተረችነት ስላለውና እንዲሁም ሃሰት መሆኑ ሲፈተን ሃሰት እንዳልሆነ እስካሁን ስለተረጋገጠ ነው።
አንድ ኅልዮት እውነተኛ ኅልዮት ለመባል ተረችነት ያስፈልገዋል። በተረፈ ያ ኅልዮት አንድን ነገር ለማብራራት/ለመግለጽ የሚረዱ የተያያዙ ሃሳቦችን መያዝ ያስፈልገዋል። እነዚህ ሃሳቦች ሊጠረጠሩ ከማይችሉ መሰረታዊ ሃሳቦች የተሰሩ መሆን ይገባቸዋል። ሆኖም ከሚብራርው ሃቅ የተለዩ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ ወርቅ ለምን ቢጫ ቀለም እንዳለው ለማብራራት/ለመግለጽ የሚረዳ ጥሩ ኅልዮት "ሁሉም ሰው ወርቅ ቢጫ እንደሆነ ማየት ይችላል" ከሚል ሃሳብ መነሳት የለበትም። እሚብራራው ሃቅን እንደ ኅልዮቱ መነሻ መውሰድ አይፈቀድም።