ራስ መኮንን

ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል
(ከራስ መኰንን የተዛወረ)

ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤልሸዋ ንጉሥ የነበሩት የሣህለ ሥላሴ ልጅ የልዕልት ተናኘወርቅ እና የደጃዝማች ወልደሚካኤል ልጅ ናቸው። ግንቦት ፩ ቀን ፲፰፻፵፬ ዓ.ም ጎላ ወረዳ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ እስከ ፲፬ ዓመት ዕድሜያቸው ከአባታቸው ጋር ከኖሩ በኋላ ያጐታቸው የንጉሥ ኃይለ መለኮት ልጅ ዳግማዊ ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉሥ እንደነበሩ፡ ወደርሳቸው ቤተ መንግሥት መጥተው፡ ባለሟል ሆኑ ።

ራስ መኮንን ወልደሚካኤል
ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል
የዓፄ ምኒሊክ አጎት ልጅ ፣ የሐረር አገረገዢ
የተወለዱት ግንቦት ፩ ቀን ሺ፰፻፵፬ ዓ.ም. 
የትውልድ ቦታ ጎላ ወረዳ ደረፎ ማርያም
የአባት ስም ወልደሚካኤል ወልደመለኮት
የእናት ስም ተናኘወርቅ ሣህለ ሥላሴ
መዐረግ ዳግማዊ ምኒሊክ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ
የትግራይ አገረ ገዢ
የሐረር አገረ ገዢ
ባለቤት ወይዘሮ የሺ እመቤት
እህት ባፈና ወልደሚካኤል
ልጆቻቸው ይልማና ተፈሪ መኮንን
በውትድርና መስክ
በአድዋ ጦርነት የደቡብ ጦር ጠቅላይ አዛዥ
ያረፉት መጋቢት ፲፫ ቀን ሺ፰፻፺፰ ዓ.ም.
ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያን


፲፰፻፷፰ ዓ.ም ዕድሜያቸው ሀያ አራት ዓመት ሲሆን ከወይዘሮ የሺ እመቤት ጋር ተጋብተው ሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም የወደፊቱን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ወለዱ። ልዑል ራስ መኮንን የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ምኒልክ ተወካይ ሆነው ሁለት ጊዜ የአውሮፓን አገሮች ጎብኝተዋል። በዚህ ጊዜ እሳቸው ኢጣሊያን ሲጎበኙ በነበረ ጊዜ የኢጣሊያ ጋዘጦች የውጫሌ ውልን በተመለከተ፤ «...በውጫሌ ውል ላይ ኢትዮጵያ የኢጣሊያን ጥገኝነት ተቀብላ ውል ከፈረመች በኋላ የጀርመን ንጉሠ ነገሥት ከኢትዮጵያ የሚላከውን ማንኛውንም ደብዳቤም ሆን ጉዳይ በኢጣሊያ መንግሥት በኩል መቀበል ሲገባቸው በቀጥታ ከምኒልክ የተጻፈውን ደብዳቤ ተቀብለዋል...» እያሉ የጻፉትን ራስ መኮንን ተቃውሞአቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የውሉን መበላሸት ለአጤ ምኒልክ አሳወቁ። ከኢጣሊያንም ጋር በተደረገውም ጦርነት ራስ መኮንን ፲፭ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ይዘው ከምኒልክ እና ታላላቅ ጦር አዛዦች ጋር ዘምተዋል።

፲፰፻፺፰ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በብርቱ ስለታመሙ ለኅክምና ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ጥር ፬ ቀን ከከተማቸው ከሐረር ተነሱ። ጥር ፱ቀን ቡርቃ ወንዝ አድረው የጥምቀትን በዓል አክብረው ከዋሉ በኋላ ሕመሙ ስለጸናባቸው ወደ ኋላ ተመልሰው ቁልቢ ገብተው በሐኪም ይታከሙ ጀመር። እዚሁም ሲታመሙ ከቆዩ በኋላ መጋቢት ፲፫ ቀን ፲፰፻፺፰ ዓ.ም ቁልቢ ላይ አርፈው ሐረር ላይ እሳቸው በተከሉት በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ። ዐፄ ምኒልክም የአርባቸው ለቅሶ የሚለቀሰው አዲስ አበባ እንዲሆን ባዘዙት መሠረት፤ ሰኞ ሚያዝያ ፳፪ ቀን በአዲስ አበባና በዙሪያው ያሉት የየገዳማቱና የየአድባራቱ ካህናት የክርስቲያን የፍታት ጸሎት ተድርጎ በማግስቱም ማክሰኞጊዮርጊስ ዕለት ሚያዝያ ፳፫ቀን ፲፰፻፺፰ ዓ.ም በሰኢ ሜዳ ላይ ድንኳን ተተክሎ፤ መኳንንቱና ሠራዊቱ ተሰብስቦ የራስ መኮንን የማዕረግ ልብሳቸውና የራስ ወርቃቸው፤ ኒሻኖቻቸውና የጦር መሳሪያቸው ተይዞ ፈረስና በቅሏቸው በወርቅ እቃ ተጭነው በሠራዊቱ መካከል እየተመላለሱ ታላቅ ልቅሶ ተለቀሰላቸው። ከአልቃሾቹም አንዱ ደግነታቸውን ለማስታወስ እንዲህ ብሎ አሟሸ፤-

«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፤
መኮንን አይደለም ድኃ ነው የሞተው»

ዋቢ መጻሕፍት ለማስተካከል