ሥነ-ፍጥረት

ሰው ከምን ተፈጠረ
(ከሥነ ፍጥረት የተዛወረ)
ይህ መጣጥፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። ስለ ፊዚክስ ለመረዳት የተፈጥሮ ሕግጋት ጥናትን ይዩ።
Lucas Cranach the Elder Adam and Eve

ሥነ-ፍጥረት በክርስትና

ሥነ-ፍጥረት ማለት ልዑል እግዚአብሔር በእውቀቱ ሰማይን፣ ምድርን፣ እንዲሁም በእነርሱ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ ከምንም ወይም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ብቁ ንቁ የሆኑ ሥነ-ፍጥረት የፈጠረበትን ሁኔታና ሥርዓት የምንማርበት ትምህርት ነው፡፡ ሥነ-ፍጥረት ማለት የፍጥረት መበጀት ማለት ነው፡፡ ይህ የሚታየው ዓለምና በውስጡ ያለው ሁሉ ከዚህ የሚታየው ዓለም ውጭም ያለው የማይታይ ዓለምና በውስጡ ያሉት ረቂቃን ፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጥረዋል፡፡ /ዘፍ.1፣1 መዝ.101፣25 ኢሳ.66፣1-2 ዕብ.11፣3/ እግዚአብሔር ግዙፉንና ረቂቁን ዓለም የፈጠረው ከምንም ተነስቶ የሚያግናኛቸውና የሚያዋህደው ነገር ሳይኖረው/እምኀበ አልቦ/ ነው፡፡ /መዝ.32፣9 2ኛ መቃ.14፣10 ጥበብ.11፣18 የሐ.ሥራ 17፣24 ዕብ.11፣3 መዝ.148፣5

 • እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረው ሰውንና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ሲሆን የተቀሩትን ፍጥረታት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ስጋ ለምግበ ነፍስ ነው። /መዝ.148፣1-3 ራዕ4፣11 የሐ.ሥራ14፣17 ሮሜ.1፣20/
 • እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ያከናወነው በስድስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ /ዘፍ2 እና ዘጸ.20፣9-11/ በእነዚሀ ቀናት የተፈጠሩት ፍጥረታት እያንዳንዳቸው ቢቆጠሩ ፍጡር ተናግሮ አይፈጽመውም ነበር፡፡ ነገር ግን በባሕርያቸው በአኗኗራቸው በ22 ይመደባሉ፡፡ ኩፋሌ 3፣9 የተፈጠሩትም በሦስት መንገድ ነው፡፡ ይኸውም፡-
 1. በዝምታ /በአርምሞ/
 2. በመናገር /በነቢብ/
 3. በመስራት /በገቢር/ ናቸው፡፡

ሥነ-ፍጥረት በኢስላም

ሥነ-ፍጥረት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

39፥62 *አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡ اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ ۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ

"ሥነ-ፍጥረት"creatinology" ማለት ስለ ፍጥረት የሚያጠና የዕውቀት ዘርፍ ነው፤ አምላካችን አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፤ "ሸይዕ" شَىْء ማለት "ነገር'thing" ማለት ሲሆን ሁሉንም ነገራት ሁሉ ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው፡- «ኹን ነው» ወዲያውም ይኾናል፦ 2፥117 ሰማያትንና ምድርን ያለብጤ ፈጣሪ ነው፤ *ነገርንም ማስገኘት በሻ ጊዜ ለእርሱ የሚለው፡- «ኹን ነው» ወዲያውም ይኾናል*፡፡ بَدِيعُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۖ وَإِذَا قَضَىٰ أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ

አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፤ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፦ 39፥62 *አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡ اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ ۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ 6፥102 ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ *ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው*፤ ስለዚህ ተገዙት፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ ۖ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ فَاعْبُدُوهُ ۚ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ 13፥16 *አላህ ሁሉንም ነገር ፈጣሪ ነው*፤ እርሱም አንዱ አሸናፊው ነው፤ በል፡፡ قُلِ اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ وَهُوَ الْوَاحِدُ الْقَهَّارُ 40፥62 ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ *የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው*፤ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ ከእምነት ወዴት ትመለሳላችሁ፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ فَأَنَّىٰ تُؤْفَكُون


ነጥብ አንድ "ፍጥረት" አላህ የፈጠራቸው ፍጥረታት ህልቆ-መሳፍርት ናቸው፤ ከአጽናፍ እስከ አድማስ ያሉትን ትልቅ እና ደቂቅ ፍጥረታት ቢዘረዘሩ አያልቁም፤ እነዚህን ፍጥረታት አላህ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ ነው፦ 50፥38 ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ድካምም ምንም አልነካንም፡፡ وَلَقَدْ خَلَقْنَا السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَمَا بَيْنَهُمَا فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ وَمَا مَسَّنَا مِن لُّغُوبٍ 25፥59 ያ ሰማያትና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ፣ ከዚያም በዐርሹ ላይ የተደላደለ አልረሕማን ነው፡፡ ከእርሱም ዐዋቂን ጠይቅ፡፡ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَمَا بَيْنَهُمَا فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ ثُمَّ اسْتَوَىٰ عَلَى الْعَرْشِ ۚ الرَّحْمَـٰنُ فَاسْأَلْ بِهِ خَبِيرًا

ይህ ጥቅላዊ ገለጻ ሲሆን በተናጥል አስፈላጊ የሆነው አፈጠጠሩ እንዲህ ይገልጻል፦ 42፥9 በላቸው «እናንተ በዚያ ምድርን በሁለት ቀኖች ውስጥ በፈጠረው አምላክ በእርግጥ ትክዳላችሁን? ለእርሱም ባለንጣዎችን ታደርጋላችሁን? ያ ይህንን የሠራው የዓለማት ጌታ ነው፡፡ قُلْ أَئِنَّكُمْ لَتَكْفُرُونَ بِٱلَّذِى خَلَقَ ٱلْأَرْضَ فِى يَوْمَيْنِ وَتَجْعَلُونَ لَهُۥٓ أَندَادًۭا ۚ ذَٰلِكَ رَبُّ ٱلْعَٰلَمِينَ

ከመጀመሪያው ቀን እስከ አራተኛው ቀናት ባሉት በአራት ቀናት ውስጥ በምድር ላይ የረጉ ጋራዎችን፣ በውስጧም ምግቦችዋን ለጠያቂዎች ትክክል ሲኾኑ ወሰነ፦ 42፥10 በእርሷም ከበላይዋ የረጉ ጋራዎችን አደረገ፡፡ በእርሷም በረከትን አደረገ፡፡ በውስጧም ምግቦችዋን በአራት ቀናት ውሰጥ ለጠያቂዎች ትክክል ሲኾኑ ወሰነ፡፡ وَجَعَلَ فِيهَا رَوَٰسِىَ مِن فَوْقِهَا وَبَٰرَكَ فِيهَا وَقَدَّرَ فِيهَآ أَقْوَٰتَهَا فِىٓ أَرْبَعَةِ أَيَّامٍۢ سَوَآءًۭ لِّلسَّآئِلِينَ

"ጭስ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ዱኻን" دُخَانٌۭ ሲሆን "ጋዝ" ማለት ነው፤ ሰማይ በጋዝ ደረጃ እያለች አላህ ለእርሷም ለምድርም «ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ» አላቸው፡፡ «ታዛዦች ኾነን መጣን» አሉ፦

42፥11 ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ፡፡ ለእርሷም ለምድርም «ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ» አላቸው፡፡ «ታዛዦች ኾነን መጣን» አሉ፡፡ ثُمَّ ٱسْتَوَىٰٓ إِلَى ٱلسَّمَآءِ وَهِىَ دُخَانٌۭ فَقَالَ لَهَا وَلِلْأَرْضِ ٱئْتِيَا طَوْعًا أَوْ كَرْهًۭا قَالَتَآ أَتَيْنَا طَآئِعِينَ

"ሱመ" ثُمَّ ማለት አያያዥ መስተጻምር ሲሆን "ከዚያም" ወይም "እንዲሁ" ማለት ነው፤ አያያዥነቱ "ተርቲቢያህ" ማለትም "ቅድመ-ተከተል" ነው፤ ይህም ቅድመ-ተከተል በሁለት ይከፈላል፦ አንዱ "ተርቲበቱል ከላም" ማለት "የንግግር ቅድመ-ተከተል" ሲሆን ሁለተኛው "ተርቲበቱል ዘመን" ማለት የጊዜ ቅድመ-ተከተል ናቸው፣ እዚህ አንቀጽ ላይ ግን ዓውዱ የንግግር ቅድመ-ተከተል ታሳቢና ዋቢ ያደረገ ነው፤ አላህ ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ፤ ጭስ የነበረችውን ሰማይ በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደረጋቸው፦

41፥12 በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደረጋቸው፡፡ فَقَضَىٰهُنَّ سَبْعَ سَمَٰوَاتٍۢ فِى يَوْمَيْنِ

2፥29 እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ *ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ هُوَ ٱلَّذِى خَلَقَ لَكُم مَّا فِى ٱلْأَرْضِ جَمِيعًۭا ثُمَّ ٱسْتَوَىٰٓ إِلَى ٱلسَّمَآءِ فَسَوَّىٰهُنَّ سَبْعَ سَمَٰوَٰتٍۢ ۚ وَهُوَ بِكُلِّ شَىْءٍ عَلِيمٌۭ


ነጥብ ሁለት "ማስተንተን"

በሰማያትና በምድር ያሉትን ከአጽናፍ እስከ አድማስ ያሉትን ትልቅ እና ደቂቅ ህልቆ-መሳፍርት ፍጥረታት እኛ ቀስ በቀስ በማስተንተን ማወቅ እንችላለን፤ በአላህ አፈጣጠር ውስጥ ምንም መዛነፍን አታይም፤ ዓይንህንም ወደ ፍጥረታት እይ ከስንጥቆች አንዳችን ታያለህን? በፍጹም አታይም፦
3፥191 እነርሱም እነዚያ ቆመው፣ ተቀምጠውም፣ በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወሱ *በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ*፡- «ጌታችን ሆይ! *ይህን በከንቱ አልፈጠርከውም*፤ ጥራት ይገባህ፤ ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን» የሚሉ ናቸው፡፡ الَّذِينَ يَذْكُرُونَ اللَّهَ قِيَامًا وَقُعُودًا وَعَلَىٰ جُنُوبِهِمْ وَيَتَفَكَّرُونَ فِي خَلْقِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ رَبَّنَا مَا خَلَقْتَ هَـٰذَا بَاطِلًا سُبْحَانَكَ فَقِنَا عَذَابَ النَّارِ 

67፥3 ያ ሰባትን ሰማያት የተነባበሩ ኾነው የፈጠረ ነው፡፡ *በአልረሕማን አፈጣጠር ውስጥ ምንም መዛነፍን አታይም*፡፡ ዓይንህንም መልስ፡፡ «ከስንጥቆች አንዳችን ታያለህን?» الَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ طِبَاقًا ۖ مَّا تَرَىٰ فِي خَلْقِ الرَّحْمَـٰنِ مِن تَفَاوُتٍ ۖ فَارْجِعِ الْبَصَرَ هَلْ تَرَىٰ مِن فُطُورٍ

ለእኛም በሰማያት ያለውን እና በምድርም ያለውን ሁሉ በሙሉ ከአላህ ሲኾን የገራልን ነው፤ በዚህ አፈጣጥር ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ተዓምራት አልለበት፦ 45፥13 ለእናንተም በሰማያት ያለውን እና በምድርም ያለውን ሁሉ በሙሉ ከእርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፡፡ በዚህ *ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች* ተዓምራት አልለበት፡፡ وَسَخَّرَ لَكُم مَّا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا مِّنْهُ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ 13፥3 እርሱም ያ ምድርን የዘረጋ በእሷም ተራራዎችንና ወንዞችን ያደረገ በውስጧም ከፍሬዎች ሁሉ ሁለት ሁለት ዓይነቶችን ያደረገ ነው፡፡ ሌሊትን በቀን ይሸፍናል፡፡ በዚህም ውስጥ *ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች* ምልክቶች አሉ፡፡ وَهُوَ الَّذِي مَدَّ الْأَرْضَ وَجَعَلَ فِيهَا رَوَاسِيَ وَأَنْهَارًا ۖ وَمِن كُلِّ الثَّمَرَاتِ جَعَلَ فِيهَا زَوْجَيْنِ اثْنَيْنِ ۖ يُغْشِي اللَّيْلَ النَّهَارَ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ

ሰማያትና ምድር ከጌታችንም ጸጋዎች ናቸው፦ 55፥7 *ሰማይንም አጓናት*፡፡ ትክክለኛነትንም ደነገገ፡፡ وَٱلسَّمَآءَ رَفَعَهَا وَوَضَعَ ٱلْمِيزَانَ 55፥10 *ምድርንም ለፍጡሩ አደላደላት*፡፡ وَٱلْأَرْضَ وَضَعَهَا لِلْأَنَامِ 55፥13 *ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?* فَبِأَىِّ ءَالَآءِ رَبِّكُمَا تُكَذِّبَانِ

በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ ለእኛ ያገራልን ግልጽም ድብቅም ሲኾኑ የሞላላልን ጸጋዎቹንም ናቸው፦ 31፥20 አላህ *በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ ለእናንተ ያገራላችሁ ጸጋዎቹንም ግልጽም ድብቅም ሲኾኑ የሞላላችሁ መኾኑን አታዩምን?* أَلَمْ تَرَوْا أَنَّ اللَّهَ سَخَّرَ لَكُم مَّا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ وَأَسْبَغَ عَلَيْكُمْ نِعَمَهُ ظَاهِرَةً وَبَاطِنَةً ۗ

ሰማያትና ምድር፣ በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ እኛ የደረስንበት ግልጽም ያልደረስንበት ድብቅም ለእኛ ያገራልን የአላህንም ጸጋ ናቸው፤ የአላህንም ጸጋ ብትቆጥረው አንዘልቀውም፦ 16፥18 *የአላህንም ጸጋ ብትቆጥሩ አትዘልቋትም*፡፡ አላህ በእርግጥ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡ وَإِن تَعُدُّوا نِعْمَةَ اللَّهِ لَا تُحْصُوهَا ۗ إِنَّ اللَّهَ لَغَفُورٌ رَّحِيمٌ


መደምደሚያ በተረፈ ዘፍጥረት 1፥1-31 የፈጣሪን ፍጥረት በከፊት እንጂ በሙሉ አይዘረዝርም። ለምሳሌ ሰባት ሰማያት፣ መላእክት፣ ውኃ፣ ፈንገስ፣ ባክቴሪያ፣ ጀርም ወዘተ መቼ እንደተፈጠሩ፣ ከምን እንደተፈጠሩ እና እንዴት እንደተፈጠሩ አይናገርም። አላህ የዓለማት ጌታ ነው፤ “ዓለሚን” عَٰلَمِين ማለት “ዓለማት” ማለት ሲሆን የዘመናችን የሥነ-ፈለክ አስተንታኞች “መልቲ-ቨርስ”multi-verse” ይሉታል፤ ይህም ህልቆ-መሳፍት የሆነውን አድማስና አፅናፍ ለማመልከት ይጠቀሙበታል፤ “አዕለም” أَعْلَم የዐለሚን ነጠላ ሲሆን ‘ዐልለመ” عَلَّمَ “አሳወቀ” ከሚለው ግስ የመጣ ሲሆን “ዓለም” ወይም “የታወቀ” ማለት ነው፤ አላህ በእኛ ዘመን ባሉት ያሳወቀው እኛ ያለንባት አንድ ዓለም “ዩኒ-ቨርስ”uni-verse” ነው፤ የእኛ ዓለም ከ 170 billion እስከ 200 billion “ረጨት”galaxy” ይዟል፤ “ረጨት” ማለት የከዋክብት ስብስብ ሲሆን የእኛ ረጨት “ፍኖተ-ሃሊብ”Milky Way” ረጨት ይባላል፤ ይህ ረጨት ውፍረቱ 1000 የብርሃን አመት ይገመታል፤ ከአንዱ ጫፍ እስከሌላኛው ጫፍ ያለው ርቀት በዲያሜትር ሲለካ ደግሞ 100,000 የብርሃን ዓመት ይሆናል፤ በውስጡ ከ100 እስከ 400 ቢልዮን ከዋክብቶች እንደያዘ ይገመታል። ይህንን የከዋክብት ረጨት”constellation” አምላካችን አላህ የዛሬ 1407 ዓመት በቁርአን “ቡሩጅ” بُرُوج ይለዋል፦ 85:1 #የቡርጆች الْبُرُوجِ ባለቤት በሆነችው ሰማይ እምላለሁ፤ 25:61 ያ በሰማይ #ቡርጆችን بُرُوجًا ያደረገና በርሷም አንጸባራቂን ፀሐይ አብሪ ጨረቃንም ያደረገ ጌታ ክብሩ በጣም ላቀ። 15:16 በሰማይም ላይ #ቡርጆችን بُرُوجًا በእርግጥ አድርገናል፡፤ ለተመልካቾችም አጊጠናታል፡፡

አላህ የዛሬ 1400 ዓመት በተከበረው ቃሉ በቁርአን “በአጽናፎቹ ውስጥ ያሉትን ታምራቶቻችንን በእርግጥ እናሳያቸዋለን” ብሎ ቃል ገብቶ ነበር፦ 41፥53 እርሱም ቁርአን እውነት መሆኑ ለነርሱ እስከሚገለጽላቸው ድረስ፣ #በአጽናፎቹ #ውስጥ እና በራሶቻቸውም ውስጥ #ያሉትን #ታምራቶቻችንን በእርግጥ #እናሳያቸዋለን፤ ጌታህም እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ አዋቂ መሆኑ አይበቃቸውምን?

ታዲያ በበረሃ ግመል ገፊ ነው ተብሎ በሚነገርላቸው ላይ ይህ ሁሉ እውቀት እንዴት ተዥጎደጎደ? ስንል፤ ይህንን እውቀት የዛሬ 1407 ዓመት ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው ይሆናል መልሱ፦ 25:6 ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፤ እርሱ መሐሪ አዛኝ ነውና፤ በላቸው።

✍ከወንድም ወሒድ ዑመር https://t.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም

ፍጥረታት የተገኙበት መንገድና ሁኔታEdit

ፍጥረታት የተገኙበት ሁኔታ በሁለት ሁኔታ ነው፡፡ እነርሱም እምኸኀበ አልቦ አልቦ ኀበቦ (ካለመኖር ወደመኖር) በማምጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ግብር እም ግብር ከተፈጠሩት ላይ በመፍጠር ነው፡፡

 • እምኀበ አልቦ ኀበቦ(ካለመኖር ወደ መኖር) በማምጣት የፈጠራቸው ፍጥረታት አራቱ ባሕርያት ማለትም ነፋስእሳትውሃመሬትጨለማመላእክት ናቸው፡፡
 • ግብር እም ግብር (ከተፈጠሩት ላይ በመፍጠር) የተፈጠሩት ደግሞ ሌሎቹ ፍጥረታት ናቸው፡፡ መገኛቸውም አራቱ ባሕርያተ ስጋ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እነሱን በማዋሐድ ፈጥሯቸዋል፡፡

ፍጥረታት የተገኙበት መንገድ ደግሞ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-

 1. በዝምታ /በአርምሞ/፡- አራቱ ባሕሪያተ ስጋ፣ ጨለማ፣ መላእክት፣ ሰማያት
 2. በመናገር /በነቢብ/፡- ብርሃን፣ የዕለተ ሰኞ፣ የዕለተ ማክሰኞ፣ የዕለተ ረቡእ እና ሐሙስ ሥነ-ፍጥረታት ናቸው፡፡
 3. በመስራት /በገቢር/ ፡-ሰውን ብቻ፡፡

የስድስት ቀናት ፍጥረታትEdit

የእለተ እሑድ ፍጥረታት፡- እሑድ ማለት አሐደ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን የመጀመሪያ አንደኛ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ቀን ስምንት ፍጥረታትን እምኀበ አልቦ ኀበቦ አምጥቶ እሳት፣ ነፋስ፣ ውሃ፣ አፈር/መሬት፣ ጨለማ፣ ሰማያት፣ መላእከት እና ብርሃን ናቸው፡፡ /ዘፍ.1፣1 እሳት፣ ነፋስ፣ ውሃና መሬት አራቱ ባሕርያተ ስጋ ይባላሉ፡፡ ሰማያት ሰባት ናቸው፡፡ /መዝ.18፣1 ማቴ.3፣17 2ኛ ቆሮ.123 ዮሐ.14፣2 ዕዝራ ሱቱኤል 4፣4/

 1. ጽርሐ አርያም፡- ከሰማያት ሁሉ በላይ ናት፡፡ ለመንበረ መንግስት እንደ ጠፈር የምታገለግል ናት፡፡
 2. መንበረ መንግስት /መንበረ ስብሐት/፡- እግዚአብሔር በወደደው ምሳሌ ለፍጡራን የሚታይበት ነው፡፡ ለኢሳይያስሕዝቅኤልወንጌላዊው ዮሐንስ በአምሳለ ንጉስ ታየቷቸዋል፡፡ ኢሳ.6፣1 ሕዝ.12፣6 ራዕ.4፣2 መዝ.10፣4 ሰማይ ውዱድን እንደ መሰረት አድርጎ ሰርቷታል፡፡
 3. ሰማይ ውዱድ፡- ከኪሩቤል ላይ ተዘርግቶ ለመንበረ መንግስት እንደ አዳራሽ ወለል ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡
 4. ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፡- በፊት ሳጥናኤል የተፈጠረበት ኋላ የወጣባት ናት፡፡ ራዕ.12፣9 ይሁ.1፣6 በእለት ምጽአት በጎ የሰሩ ሰዎች የሚወርሷት የክርስቲያኖች ርስት ናት፡፡ ገላ.4፣4-26 ዕብ.12፣22 ዮሐ.14፣2 አስራ ሁለት ደጅ አላት፡፡ የደጆቿም ብርሃን ለዓይን እጅግ የሚስቡ ናቸው፡፡ የብርሃን መጋረጃም አላት፡፡ የ12ቱ ሐዋርያቱም ስም በመሰረቶቿ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እግዚአብሔር የብርሃን ታቦትን ፈጥሮ አኑሮባታል፡፡የአምላክ ማደሪያ የሆነች ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ /ራዕ.11፣19/
 5. ኢዮር
 6. ራማ
 7. ኤረር፤ እነዚህ ሦስቱ ዓለመ መላእክት /የመላእክት መኖሪያ/ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በ3 ክፍል የምትሰራው በዚህ ምሳሌ ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክትEdit

መላእክት የተፈጠሩ በመጀመሪያ ቀን በእለተ እሑድ ነው፡፡ /ኩፋ.2፣6-8 በነገድ መቶ በከተማ አስር ነበሩ፡፡ መላእክት እምኀበ አልቦ ወይም ከአምላካዊ ብርሃን ተፈጥረዋል፡፡ አክሲማሮስ የተባለ መጽሐፍ መላእክት ከነፋስ ከእሳት ተፈጥረው ቢሆኑ እንደኛ ሞተው በፈረሱ በበሰበሱ ነበር ብሏል፡፡ በቅዱሳት መጽሐፍት በግብራቸው በእሳትና በነፋስ ተመስለዋል፡፡ መዝ.103፣4 ዕብ.1፣7 በእሳትና በነፋስ መመሰላቸው ነፋስ ፈጣን ነው መላእክትም ለተልእኮ ይፈጥናሉና፡፡ ነፋስ ረቂቅ ነው መላእክትም ረቂቃን ናቸው፡፡ እሳት ብሩህ ነው መላእክትም ብሩኀነ አእምሮ ናቸው፡፡ የመላእክት ባሕርይ ፦

 • መላእክት በፍጥረታቸው ረቂቃን ስለሆኑ ስጋና አጥንት የላቸውም፡፡ አይበሉም አይጠጡም /ሉቃ.24፣39/
 • መላእክት ጾታ የላቸውም፡፡ አያገቡም፡፡ /ማቴ.22፣30
 • አንድ ጊዜ የተፈጠሩ የማይባዙ የማይዋለዱ ናቸው፡፡ ህማም ሞትና ድካም የለባቸውም ሕያዋን ናቸው፡፡
 • ቁጥራቸው በአኃዝ አይወሰንም /ራዕ.5፣11/

የመላእክት ግብራቸው /ስራቸው/Edit

 • ስራቸው እግዚአብሔርን ያለ እረፍት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ሌትና ቀን ማመስገን ነው፡፡ /ኢሳ.6፣3 ራዕ.4፣8/
 • መላእክት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ለምህረትና ለብስራታ ለቁጣም ይላካሉ፡፡ /ሉቃ.1፣1-26 ዘፍ.19፣1-38፤ 2 ነገሥ.19፣35…/
 • ድኀነት የሚገባቸውን ሰዎች ይጠብቃሉ /መዝ.33፣7 90፣15/ ማቴ.18፣10 የሐ.ሥራ 12፣7/
 • ክፉዎችን ይቃወማሉ፡፡ የሐሰትና የዓመጸኛ የክህደት ምንጭና አባት የሆነውን ዲያብሎስን /ሄኖክ.12፣3 መቅ.ወንጌል ራእይ. 13፣5 ዮሐ. 8፣44/ በመጀመሪያ የተቃወሙት መላእክት ናቸው፡፡ /ራዕ.12፣7/
 • የቅዱሳንን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳረጋሉ፡፡ /ራዕ.8፣2-4 ጦቢ.12፣15/
 • መላእክት ሰውን ያማልደሉ፡፡ ሰው ከፈጣሪው ጋር እንዲታረቅ ይጸልያሉ፡፡ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ናቸውና ስለ ሰው ይለምናሉ፡፡ [1]
 • መላእክት ሰውን ይረዳሉ፡፡ /ዘፍ 16፣7 21፣17፤ 1 ነገሥ.19፣5-7/ ሰውን ይጠብቃሉ፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ጠባቂዎች አሉት፡፡ አንዱ መላእክ ቀን አንዱ ደግሞ ሌሊት ይጠብቁታል፡፡ /ማቴ.18፣10/
 • የእግዚአብሔር አገልጋዮችን በችግራቸው ጊዜ ይረዳሉ ያበረታሉ፡፡ /የሐዋ.5፣12-24 12፣1-17 27፣22-25/
 • መላእክት ንስሃ በሚገቡ ሰዎች ደስ ይሰኛሉ፡፡ /ሉቃ.15፣10/
 • መላእክት ይህን የመስላሉ ቁመታቸው ይህን ያህላል ማለት አይቻልም ፡ ረቂቃን ናቸውና ሊያድኑ ያሉትን ለመታደግ በወጣትና በሽማግሌ በተለያዩ አምሳላት ይታያሉ፡፡

የሰኞ /ሁለተኛው ቀን/ ስነ ፍጥረትEdit

ሰኞ ማለት ሰኑይ ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ሲሆን በሁለተኛው ቀን እግዚአብሔር ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ሞልቶ የነበረውን ውኃ ወደ ላይና ወደ ታች ከፈለ፡፡ በመካከሉም ጠፈርን አደረገ፡፡ ጠፈርንም ሰማይ ብሎ ጠራው፡፡ ከጠፈር በላይ የተቀረውም ውኃ ሐኖስ ይባላል፡፡ ዘፍ.1፣6-8 ኩፋ.2፣9 የጠፈር ጥቅም፦

 • ፀሐይ፣ ለከዋክብትና ለጨረቃ መመላለሻ ማኀደር ይሆን ዘንድ
 • ከፀሐይ ከጨረቃና ከክዋክብት የሚወጠው ብርሃን ጉብብ ባለ ቅርጽ ወደላይ ሳይነዛ ወስኖ ገትቶ እንዲይዝ
 • ወአየ ፀሐይን (ሙቀት ማፋጀት) እንዲያቀዘቅዝ
 • ሰው ጠፈርን ወይም ሰማይን እያየ ሰማያዊ ርስቱን ተሥፋ እንዲያደርግ
 • ለአይናችን ማረፊያ

ማክሰኞ /የሦስተኛው ቀን/Edit

ማክሰኞ የሚለው ቃል ሠሉስ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ሦሥትኛ ቀን ማለት ነው፡፡ ፍጥረታት ከተፈጠሩ ሦስተኛ ቀን ነውና ሌላው ደግሞ ማክሰኞ የሚለው ቃል ማግሰኞ (የሰኞ ማግስት) ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ ብሎ ውኃን ከመሬት ለይቶ ባህር ካለው በኋላ ሦስት ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ ዘፍ. 1፣9-13 ኩፋ.2፣10-12፡፡ እነርሱም ፡- እጽዋትአዝእርትአትክልት ናቸው፡፡

 • ምሳር የሚቆረጡ እጽዋት /ዛፎች/፡፡
 • ማጭድ ሚታጨዱ አዝርዕት፡፡
 • በእጁ የሚለቀሙ አትክልት ናቸው፡፡
 • ገነት ተክል

ዕፅዋት አዝርእትና አትክልት ከአራቱ ባሕርያት ከመሬት ከውኃ ከነፋስ እና ከእሳት ተፈጥረዋል ይኸውም በግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ የዚህ እለት ፍጥረታት ለምስጢረ ስጋዌ ምሳሌ እንጠቀምበታለን፡፡

የረቡዕ /የአራተኛው ቀን/Edit

ሥነ-ፍጥረት እለት ረቡእ ራብዕ ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ሲሆን አራተኛ ቀን ማለት ነው፡፡ ሥነ ፍጥረታት ከተፈጠሩ አራተኛ ቀን ማለት፡፡ በእለተ ረቡዕ ሦስት ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ እነዚህም፡- ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ናቸው። /ዘፍ.1፣14-16/ ከዋክብትና ጨረቃን በሌሊት ፀሐይን በቀን አሰለጠናቸው /መዝ.135፣8-9/። ፀሐይ ከእሳትና ከነፋስ በመፈጠሯ ትሞቃለች ትሄዳለች፡፡

ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩት ከነፋስና ከውኃ ነው፡፡ ከነፋስ በመፈጠራቸው ይሄዳሉ፣ ከውኃ እንደመፈጠራቸው ደግሞ ይቀዘቅዛሉ፡፡ እነዚህንም ለዕለታት ለሳምንታት ለወራት ለአመታትና ለክፍለ ዘመናት መታወቂያ መለያ እንዲሆኑ ፈጥሮአቸዋል /ኩፋ.2፣13-14/፡፡ የዚህ እለት ፍጥረታት ለምስጢረ ትንሳኤ ሙታን ምሳሌ እንጠቀምባቸዋለን፡፡

የሐሙስ /የአምሰተኛ ቀን/ ፍጥረትEdit

ሐሙስ የሚለው ቃል ሃምሳይ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አምሰተኛ ቀን ማለት ነው፡፡ አምስተኛ መባሉም ፍጥረታት ከተፈጠሩ አምስተኛ ቀን ሆኗልና፡፡ በእለተ ሐሙስ ሦስት ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ በልብ በሚሳቡ፣ በእግር የሚሽከረከሩ በክንፍ የሚበሩ በባህር ተወስነው የሚኖሩ በደመ ነፍስ ሕይወት ሕያዋን የሆነ ፍጥረታትን ፈጠረ። /ዘፍ.1፣20-23 ኩፋሌ.2፣15-16 እነዚህም ዘመደ እንስሳ፣ ዘመደ አራዊት፣ ዘመደ አእዋፋት ይባላሉ፡፡

 • ዘመደ እንስሳ፡-አሳዎች
 • ዘመደ አራዊት፡- አዞ
 • ዘመደ አእዋፋት፡- ዳክዬዎች

የእለተ ዓርብ ቀን ሥነ-ፍጥረትEdit

አርብ ማለት አርበ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አካተተ ፈጸመ ማለት ነው፡፡ በእለተ አርብ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን ፈጥሮ ጨርሷልና በዚህ ቀን እግዚአብሔር አራት ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ እነርሱም በእግር የሚሽከረከሩ በክንፍ የሚበሩና በልብ የሚሳቡ በየብስ የሚኖሩ በደመ ነፍስ ሕይወት ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታትን ፈጠሩ፡፡ በመጨረሻም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ሰውን በመልካችን እንፍጠር ብለው ዓርብ እለት በነግህ አራቱን ባሕርያተ ሥጋ አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን አዋህደው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርጎ በማዕከለ ምድር /መዝ.73፣12/ በቀራኒዮ አዳምን ፈጠሩት፡፡

 • እንስሳት፡- ሳር ነጭተው ውኃ ተጎንጭተው የሚኖሩ
 • አራዊት፡- ሥጋ በጭቀው ደም ተጎናጭተው ውኃ ጠትተው የሚኖሩ
 • አዕዋፋት፡- የዛፍእህልን ፍሬ ለቅመው ሥጋ በልተው ውኃ ጠጥተው የሚኖሩ ናቸው፡፡

አዳም ማለት ይህ ቀረው የማይባል ያማረ መልከ መልካም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ከመሬት መፈጠሩን ያመለክታል፡፡ ሰው አራት ባሕርያተ ስጋ አምስተኛ ግብራተ ነፍስ አሉት፡፡

 • የነፍስ ግብራት፡- ልባዊነት፣ ነባቢነት፣ ሕያውነት
 • ባሕርያተ ሥጋ፡- ውኃ፣ መሬት፣ ንፋስና እሳት

አዳም በተፈጠረ በሳምንቱ ጠዋት ሦስት ሰዓት ሲሆን «አዳም ብቻውን የሆን ዘንድ አይገባውም የምትመቸውን እረዳት እንፈጠርለት» ብሎ ወዲያውኑ በአዳም እንቅልፍ አመጣበት ከአዳም ጎን አንዲት አጥንት ወስዶ ለአዳም ምትረዳውን ሴት ፈጠረለት ዘፍ.2፣18-23 ኩፋ.4፣4። እግዚአብሔር ሔዋንን ከጎኑ ፈጥሮ ባሳየው ጊዜ አዳም «ይህች አጥንት ከአጥንቴ የተገኘች ናት ሥጋዋም ከስጋዬ የተገኘች ናትና ሴት ትባል» አለ (ዘፍ.2፣23)። ሕይዋን ማለት የሕያዋን ሁል እናት ማለት ነው፡፡ ዘፍ.3፣20 ሕይዋን ከጎኑ መፈጠሯ ወንድና ሴት (ባልና ሚስት) አንድ አካል መሆናቸውና የሰው ዘር ሁሉ ከአንድ ግንድ መገኘቱን ያመለክታል፡፡ ሔዋንን ስለ ሦስት ነገር ፈጥሮታል፦

 1. ረዳት እንድትሆን
 2. ዘር ለመተካት
 3. ከፍትወት ለመጠበቅ

ሰው ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ ነው፡፡ (መዝ.48 ፣12) ይኸውም የሚታወቀው፦

 1. ፍጥረታት ሁሉ ከተፈጠሩ በኋላ በመፈጠሩ
 2. በእግዚአብሔር አራያና አምሳል በመፈጠሩ
 3. በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ ገዥ አዛዥ ሆኖ በመፈጠሩ

22ቱ ሥነ-ፍጥረት የሚባሉት እነዚህ ከላይ ያየናቸው ናቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን ቅዳሜ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ከስራው አረፈ፡፡ ስለዚህ ይህች ዕለት ሰንበት ሆና እንድትከበር ሥጋዊ ስራዎች እነዳይሰሩባት የእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ሆነ፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ከስራው ሁሉ አርፎባታልና ነው /ዘፍ.2፣2/፡፡

ደግሞ ይዩEdit

referenceEdit

[2][3][4][5][6][7]

[8]

 1. ^ ዘካ.1፣9-13 ሉቃ.1፣19
 2. ^ ሰማኒያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ
 3. ^ ሥርወ ሃይማኖት
 4. ^ ፍሬ ሃይማኖት
 5. ^ መርሐ ጽድቅ ባሕለ ሃይማኖት
 6. ^ ኮክሃ ሃይማኖት
 7. ^ አምደ ሃይማኖት
 8. ^ መዝገበ ሃይማኖት