ቢዛንታይን መንግሥት
(ከምሥራቅ ሮሜ መንግሥት የተዛወረ)
የቢዛንታይን መንግሥት ወይም የሚሥራቃዊ ሮሜ መንግሥት ከ387 እስከ 1445 ዓ.ም. ድረስ የቆየ መንግሥት ነበር። በ387 ዓ.ም. የሮሜ መንግሥት ለመጨረሻው ጊዜ ተለይቶ ምሥራቁ ግማሽ ልዩ መንግሥት ሆነ፤ ዋና ከተማው ቁስጥንጥንያ (ወይም «አዲሱ ሮሜ») ነበር። ከዚሁ ትንሽ በፊት ክርስትና በሮሜ መንግሥት ውስጥ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ። በ468 ዓ.ም. ሮሜ እራሱና የምዕራባዊ ሮሜ መንግሥት ለኦዶዋከር ወገን ወደቁ። በቁስጥንጥንያ ግን የሮሜ መንግሥት በረታ። እስከ 612 ዓ.ም. ድረስ ይፋዊ ቋንቋ ሮማይስጥ ሆኖ ቀረ፤ በዚያ አመት ግን የሕዝቡ መነጋገሪያ ግሪክኛ ይፋዊ ሆነ።
ከ1196 እስከ 1252 ድረስ በመስቀል ጦርነት ምክንያት የቁስጥንጥንያ መንግሥት ለጊዜው ጠፋ። ከዚያ በኋላ ግዛቱ እየደከመ እስከ 1445 ዓ.ም. ድረስ ቀረ። በዚያው አመት የቱርክ ሰዎች ቁስጥንጥንያን ያዙ።
ቢዛንታይን የሚለው ስም ከቁስጥንጥንያ ጥንታዊ ስም «ቢዛንቲዮን» መጣ። ሆኖም ይህ ስም በታሪክ መጻሕፍት መጀመርያ በ1549 ታየ። በጊዜው የነበሩት ዜጋዎች ግን ራሳቸውን «ሮማዮይ» አገራቸውንም ሮሜ («ሩም») ይሉት ነበር።