ሉሉቢ ወይም ሉሉቡም በ2400-1900 ዓክልበ. ግድም በዛግሮስ ተራሮች በዛሬው ኩርዲስታን (ኢራቅኢራን) የነበረ ጥንታዊ አገር ነበረ። ከተማቸው ሉሉባን ወይም ሉሉቡና በዘመናዊው ሐለብጄ ሥፍራ እንደ ነበር ይታስባል።

የአካድ ንጉሥ ናራም-ሲን በሉሉቡም ላይ ድል ሲያደርግ።

ሉጋልባንዳና የአንዙድ ወፍ በተባለው የቀድሞ ሱመርኛ ተውፊት ዘንድ፣ በኡሩክ መጀመርያው ንጉሥ በኤንመርካር ዘመን ሉጋልባንዳ የተባለ አለቃ በ«ሉሉቢ ተራሮች» የአንዙድን ወፍ አገኘ። ይህም የኤንመርካር ሠራዊት አራታን ለመክበብ ሲሔድ የሉጋልባንዳ ደብዛ ጠፍቶ ነው።

ከዚህ በኋላ በአካድ መንግሥት ዘመን፣ ሉሉቡም ከታላቁ ሳርጐን ተገዥ አገሮች መካከል አንድ ሆኖ ይታያል። ከሉሉቢ ወደ ደቡብ ከሆነው ከጉቲዩም ጋር ይገዛ ነበር። የሳርጐን ልጅ-ልጅ ናራም-ሲን ደግሞ ሉሉባውያንን ከነንጉሳቸው ሳቱኒ አሸንፎአቸው (2034 ዓክልበ. ግ.)፣ ድል ማድረጉን ለማስታወስ የታወቀ ጽላት አስቀረጸ። የአካድም መንግሥት ለጉታውያን ከወደቀ በኋላ (2010 ግ.) ፣ ሉሉባውያን በጉታውያን ንጉሥ በኤሪዱፒዚር ላይ አመጹ።

ከጉታውያን ዘመን ቀጥሎ፣ የኡር መንግሥት ንጉሥ ሹልጊ በሉሉቢ በ1923-1922 ዓክልበ. እና ብዙ ጊዜ ይዘምት ነበር። በተከታዩ በአማር-ሲን ጊዜ (1918-1909 ዓክልበ.) በኡር ሠራዊት ውስጥ አንዱ ክፍል ሉሉባዊ ሆኖ፣ አገራቸው በኡር መንግሥት ሥልጣን እንደ ተቆጠረ ይመስላል።

የሉሉቢ ንጉሥ አኑባኒኒ ያስቀረጸው ትርዒት

ሌላ በገደል ድንጋይ የተቀረጸ ትርዒት የሉሉቢ ንጉሥ አኑባኒኒ ከጣኦቷ ኢሽታር (አስታሮት) እና ከምርከኞች ጋራ ያሳያል። ይህ አኑባኒኒ በኡር መንግሥት ዘመን እንደ ኖረ አሁን ይታስባል፤ ሆኖም በአንድ የባቢሎን ትውፊት ዘንድ፣ አኑባኒኒ የታላቁ ሳርጐን ተቃዋሚ ይባላል።

በሚከተለው ዘመን «ሉሉቢ» ወይም «ሉሉ» የሚል ቅጽል ስም ለተራራማ አገር ሰዎች ሁሉ የጠቀለለ ይመስላል። ይህም ሲሆን፣ የሉሉባውያን አገር ደግሞ ዛሙዋ በመባል ይታወቅ ነበር። በ1740 ዓክልበ. «ሉሉ» አሦርን ድል እንዳደረገ ይዘገባል። የሉሉቢ አገር እንደገና በመዝገቦች ሲታይ፣ በባቢሎን ንጉሥ 1 ናቡከደነጾር (በ1130 ዓክልበ. ግድም) እና በአሦር ንጉሥ 1 ቴልጌልቴልፌልሶር (በ1122 ዓክልበ.) ሲሸነፍ ነው። እንዲሁም ሌሎች የአሦር መንግሥት ነገሥትታ በሉሉቡም / ዛሙዋ አውራጃ ዘመቱ። በተለይም 2 አሹር-ናሲር-ፓል የሉሉባውያን / ዛሙዋውያን አለቆች አመጽ በ890 ዓክልበ. ሰበረ። በዚህ አመጽ የሸፈቱት አለቆች አሶራዊውን ለመከልከል ታላቅ ግድግዳ በተራሮች መሃል ባለው መተላለፊያ ውስጥ ሠርተው ነበር። ከዚህ በላይ 19 ባለ ቅጥር ከተሞች ነበራቸውና ብዙ ከብት፣ ፈረሶች፣ ብረታብረት፣ ጨርቃጨርቅና ወይን ከአገራቸው ተበዘበዘ። እስከ አሦር ንጉስ አስራዶንም ዘመን መጨረሻ (678 ዓክልበ.) ድረስ፣ የዛሙዋ አውራጃ አለቆች ወይም አገረ ገዦች ይጠቀሱ ነበር።

ተጨማሪ መረጃ

ለማስተካከል