ሄርኩሌስ አለማኑስ (በጀርመንኛ Alman አልማን) በጀርመን አፈ ታሪክ ዘንድ በጥንት የጀርመን ፲፩ኛው ንጉሥ ነበረ። ከቴውታኔስ ቀጥሎ ለ64 ዓመታት (ምናልባት 1855-1791 ዓክልበ. ግድም) ነገሠ።

አቬንቲኑስ እንደ ጻፈው ንጉሥ አልማን ጀግና፣ ታላቅ ጦረኛ ሲሆን የባየርን ሰዎች አባት ነበር። አርማው በጋሻው ላይ የአንበሣ ምልክት ነበር፤ ይህም እስካሁን በባየርን አርማ ሊታይ ይችላል። አምባ በአሁኑ ኑረምበርግ እንደ ሠራ ይለናል። በተጨማሪ እስከ እስያ ድረስ ሄዶ ረጅሙን «ቲጭ» ገደለው። አለማኑስ ደግሞ «አለማኒ» የተባለው ጀርመናዊ ብሔር ሞክሼ ይባላል፤ አሁንም ይህ ስም በአንዳንድ ቋንቋ፣ እንደ ፈረንሳይኛ «አለማኝ»፣ የጀርመን አገር ስያሜ ነው።

የአልማን ወንድ ልጆች ኖሪኩስ (ኖራይን)፣ ሁኑስ (ሃውን)፣ ሄልቬቲዩስ (ሄልፎስ)፣ መዶ (ሚድ)፣ ማጣያስ (ማጥ)፣ ታውሩስ (ጦይር)፣ ገሎኑስ (ግላን)፣ ስኪቴስ (ስኪጠር)፣ አቢዩስ (አብ)፣ እና ቦዩስ (ባየር) ናቸው። ከአልማን መሞት በኋላ ለትንሽ ጊዜ ከወንድማማች መካከል ሁከት ነበረ፤ ያንጊዜ በሬምስሉክሳምቡርግ የነገሠው ዘመዳቸው ራሙስ ዐርቆ የአልማን ግዛት አከፋፈላቸው ይላል። ከነዚህ ታናሹ ልጅ ቦዩስ ባየርንንና የጀርመን ከፍተኛ ንጉሥነቱን ተቀበለ።

ኖሪኩስ በኖሪኩም፣ ሄልቬቲዩስም በአሁኑስዊስ ገዛ፤ ሁኑስም ከቪስቱላ ወንዝ ምዕራብ ሳርማትያን ተቀበለና አቬንቲኑስ የሁኖች አባት ያደርገዋል። ገሎኑስና ስኪቴስ ከሁኑስ ጋር ሄዱ፤ በእስኩቴስ ሠፈሩ፤ (ሆኖም «እስኩቴስ» የሚባለው አገር ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ነበር)፤ ገሎኑስ የገሎኒ ነገድ ወለደ። መዶና ማጣያስ የሜዲዮማትሪኬስን ነገድ መሰረቱ፣ በመትዝ ዙሪያ ሠፈሩ። ከአልማንም ዘመን በኋላ ታውሩስና አቢዩስ ከብዙ ሕዝብ ጋር (ኪምብሪ ወይም ኪሜራውያን ተብለው) ከባየርን ወጥተው በኢሉዋርያና በጥቁር ባሕር ላይ ያሉትን አገራት እስከ ቦስፎሮስ ድረስ ገዙ። የጦይርም ሚስት ሃክስ ደግሞ ታላቅ አለቃና መድኃኒተኛ ነበረች፤ የርሷ ሴቶች ሥራዊት («አማዞኖች») መሬት በትንሹ እስያ እስከ አርሜኒያ ድረስ አሸነፉ ይላል።

ቀዳሚው
ቴውታኔስ
የቴውቶኔስ (ጀርመን) ንጉሥ ተከታይ
ቦዩስ