ፑርሽፐጊሪ ቪሃረ
ፑርሽፐጊሪ ቪሃረ በአሁኑ ኦዲሻ፣ ሕንድ ምናልባት ከ250 ዓክልበ. እስከ 1200 ዓም ግድም ድረስ የቆየ ቪሃረ ወይም የቡዲስም ገዳም፣ መቅደስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነበር። ዛሬ የሚታወቀው በተለይ ከሥነ ቅርስ ፍርስራሽ ነው።
የ«ፑርሽፐ-ጊሪ» ትርጉም ከሳንስክሪት «ፑርሽፐ» (አበባ) እና «ጊሪ» (ተራራ፣ ኮረብታ) ወይም «አበባማ ኮረብታ» ነው። በፑርሽፐጊሪ አጠገብ ባሉት ኮረብቶች ደግሞ ሦስት ሌሎች የተዛመዱ የጥንት ንዑስ ቪሃራዎች ፍርስራሶች በውስጡ አሉ፣ እነርሱም ላሊትጊሪ፣ ኡደየጊሪ፣ ረትናጊሪ ናቸው።
ከሥነ ቅርስ የተነሣ ቪሃረው መጀመርያው የመሠረተው ንጉሥ አሾካ (277-240 ዓክልበ.) እንደ ነበር ይታስባል። ለሕንድ የቡዲስም ጥናት ማእከል እስከ 1200 ዓም ያህል እንደ ቆየ ከቅርሶቹ ይመስላል፤ ልክ መቼ ወይም በማን ዕጅ እንደ ጠፋ ግን አይታወቅም።
በታሪካዊ መዝገቦች ዘንድ ስለ ፑርሽፐጊሪ የሚጠቅሱ ሰነዶች ጥቂትና እርግጠኛ ያልሆኑ ናቸው። በተለይ በ630 ዓም ግድም የጎበኘው የቻይና ተጓዥ ሧንዛንግ አንድ «ፑሴጶቂሊ» የተባለ ተቋም እዚያ መኖሩን ጠቀሰ።