የፕላቶ አካዳሚ (ግሪክኛ፦ አካዴሚያ፣ ሄካዴሚያ) በአቴናግሪክ አገርፕላቶ የተመሠረተ ጥንታዊ የከፍተኛ ትምህርት ቤት ተቋም ነበር። ከ395 እስከ 94 ዓክልበ. እና እንደገና ከ402-521 ዓም ቆየ።

«የአቴና ትምህርት ቤት» በራፋኤሎ በ1502 ዓም እንደ ተሳለ።

ቦታው በአቴና ከተማ በቅዱስ የወይራ ደን አጠገብ ነበረ። ግሪካዊ ፈላስፎች በፕላቶ መኖሪያ ይሰብስቡ ጀመር። እንደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት አስተማሪና ተማሮች ተለይተው ሳይሆን፣ ከፍተኛ እና ታቸኛ አባላት ነበሩ። ሴቶች አባላትም ነበሩ። ትምህርቱ በጥያቄና መልስ ይካሄድ ነበር።

በተቋሙ ውስጥ ከተማሩት ጥናቶች መካከል በተለይ ፍልስፍናሥነ ቁጥርሥነ ፈለክ ነበሩ። በመግቢያ ላይ «ከጂዎሜትሪ ተመራማሪዎች በቀር ማንም አይግባ» የሚል መፈክር እንደ ተለጠፈ ተብሏል።

አሪስጣጣሊስ ከ375 እስከ 355 ዓክልበ. በዚያ አባል ነበረ፣ ከዚያ የራሱን ትምህርት ቤት ፔሪፓቶስን በሊሲየም ጀመረ። ፕላቶ በ355 አክልበ. አረፈና እስከ 274 ዓክልበ. ድረስ የነበሩት አስተዳዳሪዎች ከፕላቶ ፍልስፍና በላይ ምንም ይፋዊ ርዕዮተ አለም አላስተማሩም።

በ274 ዓክልበ. አርቄሲላዎስ ዋና አስተዳዳሪ ሆነና ተቋሙ ያስተማረው ርዕዮተ አለም «ትምህርታዊ ተጠራጣሪነት» ሆነ። በዚህ ፍልስፍና ዘንድ፣ ፍፁም እውነትን ማወቅ አይቻልም።

በ94 ዓክልበ. የሮሜ መንግሥት አለቃ ሱላ ከተማውን በሠራዊት ይዞ ተቋሙንና የወይራ ደኑን አጠፋ።

አዲስ የፕላቶ አካዳሚ በ402 ዓ.ም. ተመሰረተ። ርዕዮተ አለሙ የፕሎቲኖስ (197-262 ዓም የኖረ) ትምህርት አሁን «አዲስ ፕላቶኒስት» የተባለው ፍልስፍና ነበር። ይህ የፕሎቲኖስ ፍልስፍና ዘዴ ወደፊት ለማንኛውም ሃይማኖት ፈላስፎች መሠረታዊ ሆነ፤ ማለትም ለአረመኔነት (ቅሬታ)፣ ለኖስቲሲስም፣ ለክርስትናም፣ ለእስልምናም ሁሉ፣ «አዲስ ፕላቶኒስም» የፍልስፍና ትምህርት መሠረት ሆነ። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ እራሱ የአረመኔነት ቅሬታ ስለ ነበር፣ የቢዛንታይን ንጉሰ ነገሥት ዩስጢኒያኖስ521 ዓም. ተቋሙ እንዲዘጋ አዘዙ።