የዞራስተር ፍካሬ: ወደ ሁሉምና ወደ ማንም በፍሬድሪች ዊልሄልም ኒሺ የተደረሰ የፍልስፍና ልቦለድ* ነው። መጽሐፉ በ1883 እና 1885 (እ.ኤ.አ) መካከል በ4 ክፍል የተደረሰ ሲሆን በጊዜው ይሰራበት ከነበረው የአስተሳሰብ ዘዴ ለየት ባለ መልኩ የፍልስፍናን እና የግብረገብን ጥናቶች መርምሯል። የመጽሃፉ አትኩሮቶች፡- የዘላለማዊ ምልልስኃይልን መፍቀድ (*ፈቃድ እዚህ ላይ ጠንካራ ፍላጎት ማለት ነው)፣ የአምላክ በጊዜው በነበሩ አውሮጳውያን ልብ ውስጥ መሞት፣ ስለዚህም የአዳዲስ ዋጋ ወይም ህግጋት አስፈላጊነት፣የበላይ ሰው (*በኒሺ አስተሳሰብ የሰው ልጅ በጦጣዎችና በበላይ ሰው መካከል ያለ ፍጡር ነው) መምጣት ትምህርቶች ነበሩ። [1] ጽሁፉ የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ስልት ይከተል እንጂ የውስጡ ፍሬ ነገር ግን የክርስትናአይሁድ ሃይማኖቶችን መሰረታዊ እምነቶች የሚጻረር ነበር። ኒሺ ይህን መጽሐፍ " ከሰዎችና ከጊዜ 6000 ጫማ" እርቆ እንደጻፈ ይናገራል፣ ማለቱም የመጽሃፉን ሃሳቦች በተራራ ላይ እያለ እንዳገኛቸው ለማስገንዘብ ነበር።[2]

ፍካሬ ዞራስተር

ኒሺ "የዞራስተር ፍካሬ" ብሎ የሰየመውን መጽሃፍ "ስርዓት አልባ"(ጥራዝ ነጠቅ) በሆነ ዘዴ ስለጻፈው ለተመራማሪወች እጅግ አስቸጋሪ ሆነ። ይሁንና ተመራማሪወች አንድ አንድ ቋሚ የሆኑ የመጽሃፉን ይዘቶች ማስተዋላቸው አልቀረም፦

  • የበላይ ሰው፡ ለኒሺ የበላይ ሰው ማለት በራሱ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ያለው ግለሰብ፣ እምቅ ኃይሉን ወደ ስራ የተርጎመ ሰው ማለት ነው። አሁን ያለው የሰው ልጅ (በኒሺ አሰተያየት) በእንስሳ እና በዚህ በበላይ ሰው መካከል ያለ ፍጡር ነው።
  • የዘላለም ምልልስ፡ ማናቸውም የተከሰቱ ነገሮች እንደገና ይከሰታሉ፣ አሁን የሚከሰቱ ነገሮች ድሮም ተከስተው ነበር ለወደፊቱም እልፍ አዕላፍ ጊዜ ይከሰታሉ! ይህ አለም ልክ እንደምናየው ሆኖ እንደገና ይከሰታል፣ ሰውም ይሞታል ግን ልክ በነበረበት መልኩ በነበረበት አለም ተመልሶ ይመጣል።
  • ኅይል መፍቀድ፡ የሰው ተፈጥሮ መሰረታዊ ባህርይ ነው። ማናቸውም የምንሰራቸው ነገሮች፣ እንደ ኒሺ አስተያየት፣ የዚህ መሪ ሃሳብ መገለጫ ናቸው። ከመራባት፣ ደስታ፣ ሐሴት ጋር ሲነጻጸር የበለጠ መሰረታዊ ሲሆን የኅይል መፍቀድ ሁሉም ህይወት ያለው ነገር ሁሉ ከከባቢው አለም ጋር የሚያደርገውን ትግል ጠቅልሎ የሚይዝ ጽንሰ ሃሳብ ነው።
  • ኃጥያትና ጽድቅ ስራወች በተሰኙ ተቃራኒ የክርስትና ሃሳቦች ላይ ብዙ ትችት መመስረት። በኒሺ አስተያየት እኒህ ነገሮች የሰው ልጅ ፈጠራወች እንጂ በተፈጥሮ የሚገኙ አይደሉም። በሱ አስተያየት የሰው ልጅ ተግባር መለካት ያለበት አስቀድሞ በተቀመጡ የግብረ ገብ ዋጋወች/ህጎች (ጥሩና መጥፎ) ሳይሆን የተግባሩን መዘዝ በመለካት ነው።


መጽሐፉ ባጭሩ

ለማስተካከል

በመጽሃፉ መግቢያ ላይ ዞራስተር 30 አመት ሲሞላው ወደ ተራራ እንደወጣና በዚያ ከሰወች ተለይቶ ብዙ ጥበቦችን እንደሰበሰብ እናነባለን። 40 አመት ሲሞላው ያከማቸውን ጥበብ ለማካፈል ከተራራው ወረደ። የመውረዱ ዋና አላማ "የበላይ ሰው"ን መምጣት ለመስበክ ነበር። የበላይ ሰው፣ በዞራስተር አስተሳሰብ፣ ከሰው በላይ የሆነ ፍጡር ማለት ነው፡ ልክ የሰው ልጅ ከጦጣወች በላይ የሆነ ፍጡር እንደሆነ።

በዞራስተር ግምት ዘመናዊው ሰው የወኔ ግሽበት፣ ባዶነትና አጠቃላይ የህይወት ውዥንብር ስለገጠመው አዲስ ትምህርት ያስፈልገዋል። በዞራስተር አስተሳሰብ የዘመናዊው ሰው መንፈሳዊ ግሽበት ምክንያት የአምላክ መሞት ነው። በርግጥ አምላክ ለመሞት አይቻለውም ሆኖም ግን በዞራስቶር አስተሳሰብ አምላክ ሞተ ማለቱ ዘመናዊው ሰው በአምላክ ላይ ያለው እምነቱ ሞተ ማለት ነው። ስለሆነም የድሮወቹ ሰወች ብዙ አስደናቂ ስራወችን ለአምላክ ሲሉ ቢሰሩም የዘመናዊው ሰው ግን ይህን እመንቱን በማጣቱ አጠቃላይ ዘመናዊ ህብረተሰብ መሪ ሃሳብ የማጣት፣ የመበስበስና ተስፋ የማጣት ምልክቶች አሳየ። ህግን የሚሰጥ በሰው አምሳያ ያለ አምላክ ለአዲሱ ሳይንሳዊና ዘምናዊ ህብረተሰብ እጅግ ኋላ ቀር መስሎ ታየ። ስለሆነም በተለይ በተማሩ ሰወች ዘንድ የአለም የህይወት ትርጉምና የግብረገብ ስርዓት እጅግ ዝብርቅርቅ ያለ ሆነ። ዘመናዊ ሰው ባዶነት "ኒሂልዝም"( የህይወት ትርጉም ማጣት) የሚባል ችግር ተጋረጠው፣ "የዞራስተር ፍካሬ" ዋና አላማ ይህን ባዶነት መታገል ነበር። በኒሺ አስተሳሰብ አዲሱ የ"በላይ ሰው" ትምህርት ለዚህ ዘመናዊ ኒሂሊዝም (ባዶነት) ፍቱን መድሃኒት መሆን ነበር።

ዞራስተር ከተራራው ወርዶ በሰወች መካከል እንዲህ ሲል ሰበከ፡ የሰው ልጅ በአሁኑ ሰዓት ያለበትን መናኛነት (ተራነት)ና የከሰረ ስልጣኔ በማሸነፍ የ"በላይ ሰው"ን መፍጠር አለበት፡ «የሰው ልጅ ሊሸነፍ የሚገባ ነው። ለማሸነፍ እያንዳንዳችሁ ምን አድርጋችኋል?» ሆኖም ግን ይህ ሰበካው ተቀባይነት አጣ። ህዝቡም መልሶ «የበላይ ሰውህን እዚያው ለራስህ» ብለውም ተሳለቁበት። የተመቻቸና ጥሩ ኑሮ ከመፈለግ ውጭ የበላይ ሰውን እንደማይፈልጉ ነገሩት። ህይወት የበለጠ ትርጉም ካልተሰጠው በርግጥም ከደስታ ውጭ ምንስ ያስፈልጋል? በዚህ ምክንያት የስልጣኔ ዋና ዓላማ ተራ መናኛ ሆነ፣ እርሱም፡- "ከፍተኛ ደስታ ለከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው" ሆነ።

ይህ ተራነት ዞራስተር ለህዝቡ ያለው ጥላቻና ንቀት እንዲያድግ አደርገ ( ምንም እንኳ ከጊዜ ወደጊዜ ሊያዝንላቸውና ሊረዳቸው ህሊናው ቢግደረደርም)። ተማሪውም ሆነ ያልተማረው፣ ፖለቲከኛውም ሆነ ፈላስፋው፣ ሰዓሊውም ሆነ ፕሮፌሰሩ፣ ሁሉም የተደላደለ ህይወት ከመሻት ውጭ ውስጣቸው ያለውን እምቅ ስብዕና ለማሳደግ የማይጥሩ ሆኖ አገኛቸው። ካደረበት ንቀት የተነሳ ዞራስተር ብዙ ተከታይ ከማፍራት ይልቅ ሊግባባቸው የሚችሉ ጥቂት ፈርጥ የሆኑ ሰወችን ፍለጋ ጀመረ፡ ተራ(መናኛ) ነገሮችን ከህይወት ለማግኘት የሚሞክሩን ሳይሆን፣ ከፍተኛ ነገርን ለማግኘት የሚሞክሩትን። ፍለጋው ጥቂት ሰወችን ስላስገኘለት ለኒህ ለተመረጡት "ማስተማር" በጥብቅ ጀመረ።

የመጨረሻው የመጽሃፉ እትም 4 ክፍሎች አሉት። እያንዳንዱ ክፍል ለማብራራት ብዙ ቦታ ስለሚይዝ ከዚህ በታች በየራሳቸው ገጽ ማብራሪያቸው ሰፍሯል። ይመልከቱ።

ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፩

ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፪

ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፫

ዋና መጣጥፍ፦ የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፬

ከፍካሬ ዞራስተር የተወሰዱ ጥቅሶች

ለማስተካከል
  • ህይወትን የምናፈቅር መኖር ስለምናወቅ ሳይሆን ማፍቀር ስለምናውቅ ነው።
  • በፍቅር ውስጥ ሁል ጊዜ ዕብደት አለ። በዕብደት ውስጥ ደግሞ ሁልጊዜ ምክንያት አለ።
  • አንቺ ታላቅ ኮከብ! ፍንትው ብለሽ የምታበሪላቸው ባይኖሩ ደስታሽ ምኑ ላይ ነበር?
  • መብረርን የሚማር መጀመሪያ መቆምን፣ ከዚያም መራመድን፣ ብሎም መሮጥንና ዛፍ መውጣትን እንዲሁም መደነስን መማር አለበት፣ ወደ መብረር መብረር አይቻልም!
  • እውነትን መናገር - በጣም ጥቂት ሰወች ይችላሉ! ከነዚህ ከሚችሉት ግን የሚፈፅሙት የሉም`!
  • ደፋርነት፣ ደንታ ቢስነት፣ አላጋጭነት፣ ጸበኛነት-- ጥበብ ከኛ እኒህን ትፈልጋለች፡ ሴት ናትና የምትወደውም ጦረኛን ብቻ ነው።
  • እራሱን የማያዝ መታዘዝ አለበት። ብዙወች እራሳቸውን ማዘዝ ይችላሉ፣ ነገር ግን ለራሳቸው ከመታዘዛቸው በፊት ብዙ ይጎላቸዋል!
  • ህብረተሰብ ተኩላውን አላምዶ ውሻ አደረገ። የሰው ልጅ ከሁሉም የሚበልጥ ለማዳ እንስሳ ነው!
  • አንድ ልምድ አጀማመሩ በሩቅ የዘመን ጭጋግ እየተሸፈነ ከሄደ፣ አመሰራረቱም እየተምታታ ከመጣ -- በክብር እያደገ ይሄዳል። ከትውልድ ወደ ትውልድም ክብሩ እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻ ልምዱ ቅዱስ ይሆንና በሰወች ዘንድ ድንቅ ይሆናል።
  • ሰው በንዴት አይገድልም፣ በሳቅ እንጂ።
  • በቁመና ለማደግ፣ ወደብርሃንም ለመጠጋት በተፈለገ ጊዜ፣ ስርን ወደ መሬት መላክ ያስፈልጋል፣ ወደ ድቅድቅ ጨለማው፣ ወደ ጥልቁ - ወደ መጥፎው።
  • እውነተኛ ወንድ ሁለት ነገር ይፈልጋል፡- አደጋና ጨዋታ። ለዚያ ሲልም ሴትን ይፈልጋል፣ ከሁሉ በላይ አደገኛ የሆነች መጫወቻ።
  • "የታላላቆቹ ተራሮች አመጣት ከየት ይሆን?" ብየ ጠይኩ። ከባህር እንደመጡ ደረስኩበት፣ ማስረጃውም በአለቶቻቸውና በከፍተኛ ገጽታቸው ተጽፎ ይገኛል። ታላላቅ ከፍታወች የሚመጡት ከታላላቅ ጥልቀቶች ነው።
  • ነጻ ከምን? ለዞራስተር ደንታ ይሰጠው ይመስል! ይልቁኑ ብሩህ አይኖችህ እንዲህ ይበሉ፡ ነጻ ምን ለማድረግ?
  • ሳንደንስበት ያለፈን ቀን እንደጠፋ ቀን መቁጥር ይገባል። እንዲሁ በሳቅ ያልታጀበን እውነት ውሸት ማለት ይገባል።
  • መተኛት ቀላል ጥበብ አይደለም፡ ለዚህ ተግባር ሲባል ቀኑን ሙሉ መንቃት ግድ ይላል።
 
የንጋት ጮራ ፡ የመጽሃፉ መጀመሪያና መጨረሻ የቅኔ ምስል
  1. ^ C. Guignon, D. Pereboom. Existentialism: Basic Writings, 2nd ed., Hackett, 2001. pp. 101-113 (እንግሊዝኛ)
  2. ^ Gutmann, James. "The "Tremendous Moment" of Nietzsche's Vision". The Journal of Philosophy, Vol. 51, No. 25. American Philosophical Association Eastern Division: Papers to be presented at the Fifty-First Annual Meeting, Goucher College, December 28-30, 1954. pp. 837-842. (እንግሊዝኛ)