የኒካራጓ ምልክት ቋንቋ (ISN, Idioma de Señas de Nicaragua ወይም Idioma de Signos Nicaragüense) በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ በምዕራብ ኒካራጓ የመስማት መሳን ባለባቸው ተማሪዎች የተለማ የምልክት ቋንቋ ነው። የተለማው ከቆዩት እጅ ቋንቋዎች ሳይሆን በተማሪዎች እራሳቸው በድንገት ነበር። ስለዚህ ለቋንቋ ሊቃውንት "የመነጋገር ልደት" ወይም የመንስኤው ሁኔታ ለማጥናት ያስችላል።

ከ1969 ዓ.ም. በፊት በመስማት የተሳናቸው ሰዎች ኅብረተሠብ አልነበራቸውም። ከቤተሠቦቻቸው ጋራ ለመነጋገር ይቻሉ ቀላል በሆነ እጅ ንቅናቄ ብቻ ነበር።

በ1969 ዓ.ም. ግን ጆሯቸው ለማይስማ ተማሪዎች ልዩ ተምህርት ቤት በዋና ከተማ በማናጓ ስለ ተመሠረተላቸው 50 ተማሪዎች ወዲያው ትምህርታቸውን ጀመሩ። የሳንዲኒስታ አብዮት በሆነበት ወቅት (1971 ዓ.ም.) መቶ ተማሪዎች ነበሩ። በ1972 ሁለተኛ ልዩ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በ1975 ዓ.ም. የተማሪዎች ቁጥር 400 ደረሰ።

በመጀመርያ ትምህርት ቤቶቹ የከንፈር ማንበብየጣት ፊደል ብቻ ለማስተማር አስበው ይህ ዘዴ ግን አልተከናወንም። ዳሩ ግን ተማሪዎቹ በትርፍ ጊዜያቸው በቤተሠቦቻቸው የተጠቀሙትን እጅ ምልክቶች እርስ በርስ ስለተማማሩ በትንሽ ጊዜ የራሳቸውን ቋንቋ ፈጠሩ።

የትምህርት ቤት አስተማሪዎች ግን ስለዚህ ልማት አላወቁም ነበር። የእጅ ምልክቶቻቸው እንደ ጨዋታ ብቻ መስሏቸው እስፓንኛ መማር ስለማይችሉ ይሆናል በማሰብ ገመቱ። እንዲግባቡ ከቶ ስላልቻሉ በመጨረሻ በ1978 ዓ.ም. ከአሜሪካ አንዲት የአሜሪካ ምልክት ቋንቋ መምህር ጁዲ ኬግል አስመጥተው እሷ ምልክቶቻቸውን በድንብ ለማጥናት ወሰነች። ያልታወቀ አዲስ ቋንቋ መሆኑን የገለጠች እርሷ ሆነች።