ኤሰልዋልኽ
ኤሰልዋልኽ (Æðelwealh) የደቡብ ሳክሶናውያን መንግሥት (ሱስ ሴየክስ ወይም ሳሰክስ በአሁኑ እንግላንድ) መጀመርያው ክርስቲያን ንጉሥ ነበረ።
የደቡብ ሳክሶናውያን ንጉሥ የሆነው ምናልባት 637 ዓ.ም. ነበር። ከዚያ በፊት ሳሰክስ የጎረቤቱ የዌሰክስ ግዛት ሆኖ ነበር። የዌሰክስ ንጉሥ ከንዋልኽ ሚስት የሜርቸ ንጉሥ ፐንዳ እኅት ስትሆን፣ እርስዋን በፈታት ጊዜ ፐንዳ በቊጣው የሳሰክስ ግዛት ከዌሰክስ ይዞ ያንጊዜ እሰልዋልኽን የነጻ ሳሰክስ ንጉሥ እንዳደረገው ይታስባል።
በ653 ዓ.ም. አሰልዋልኽ ወደ ሜርቸ ሄዶ የፔንዳ ተከታይ ዉልፍሄረ በክርስትና አስጠመቀው፤ ተጨማሪ ግዛቶች ሜዮንዋራ እና ዋይት ደሴት ለአሰልዋልኽ ተሰጡት፣ አሰልዋልኽም የክርስቲያን ኊቸ ነገድ አለቃ የኤንፍሪስን ሴት ልጅ ኤቫን አገባት። ሕዝቡ ደቡብ ሳክሶናውያን ግን (፯ ሺህ ቤተሠቦች) እስከዚያ ድረስ ገና አረመኔዎች ነበሩ።
በ670 ዓ.ም. ዝናቡ ለ፫ አመታት ተቋርጦ ታላቅ ረሃብ በአገሩ ጀመረ። የእንግሊዝ ታሪክ ጸሐፊ ቤድ እንዳለው፣ ብዙ ጊዜ 40 ወይም 50 ወጣቶች በረሃብ ተድክመው ከገደል አብረው ወደ መሞታቸው ይዘልሉ ነበር። ከሳሰክስ በቀር የተረፉት እንግሊዛውያን መንግሥታት ክርስትናን በይፋ ተቀብለው ነበር፤ የሳሰክስም ሰዎች ብቻ የአረመኔነት ወዳጆች ሆነው ቀሩ። በ673 ዓ.ም. ኤጲስ ቆጶሱ ውልፍሪድ ደርሶ ሕዝቡ የአሣ አጥማጅ ዕውቀት ስላልነበረው ውልፍሪድ ዓሣን በመርበብ ለማጥመድ አስተማራቸውና በታላቅ ደስታ ተጠመቁ፣ ወዲያውም ሰማይ ከፍቶ ዝናቡ እንደ ተመለሠ ተብሏል። አሰልዋልኽም ርስት ለገዳም ለውልፍሪድ ሰጠው።
በ678 ዓም. ግን የየዊሠ ነገድ መስፍን (በኋላም የዌሰክስ ንጉሥ) ካድዋላ ወርሮ አሰልዋልኽን ገደለው፤ ከዚያም የአሰልዋልኽ አለቆች ቤርኽትሁንና አንድሁን ካድዋላን አባረሩትና ሳሰክስን ለጊዜ ገዙ።