አሌክሳንድር ሄሊዮስ (ግሪክ፦ Αλέξανδρος Ήλιος) የግብጽ ንግሥት 7 ክሌዎፓትራና የሮማ መሪ ማርክ አንቶኒ ልጅ ነበረ። በ47 ዓክልበ. በእስክንድሪያ ተወለደ። መንታ እኅቱ 2 ክሌዎፓትራ ሰሌኔ ነበረች፣ የስሞቻቸውም ትርጉም በግሪክ «ፀሐይ» (ሄሊዮስ) እና «ጨረቃ» (ሰሌኔ) ነበሩ።

በ41 ዓክልበ. የሄሊዮስ ዕድሜ 5 አመት እየሆነ፣ ወላጆቻቸው አንቶኒና ክሌዎፓትራ በአንድ ታላቅ ሥነ ሥርዓት መንግሥታት ለልጆቻቸው ሰጡ። በዚህ አደራረግ በኩል ልዑል ሄሊዮስ የአርሜኒያ፣ የሜዶን እና የጳርቴ ንጉሥነት ማዕረግ ተሰጠ። ሆኖም እነዚህ አገራት ያንጊዜ የሮማ ግዛቶች ገና አልነበሩም፤ የራሳቸውም ነገስታት ነበሯቸው። በተጨማሪ የሮማ ሴናት እነዚህን ስጦታዎች አላጸደቀምና ደስ አላለም። ሌላ የሮማ መሪ ኦክታውያኑስ (አውግሥጦስ ቄሣር) ማርክ አንቶኒን ለመዋጋት ግብጽን ወረረና፣ አንቶኒና ክሌዎፓትራ ከተሸነፉ በኋላ ራሳቸውን ገደሉ (37 ዓክልበ.)። ልጁ ሄሊዮስና እህቱ ሰሌኔ 10 አመት ሆነው ኦክታውያን ወደ ሮማ አመጣቸውና በሠልፍ አሠለፋቸው።

ሰሌኔ በ27 ዓክልበ. የማውሬታኒያ ንጉሥ 2 ዩባ ንግሥት ሆነች። በዚህ ሰዓት ወንድሟ ሄሊዮስ በሕይወት እንዲኖር በአውግስጦስ ሞገስ እንደ ተፈቀደ ተጻፈ። ከዚያ በኋላ ልዑል ሄሊዮስ ወዴት እንደ ሄደ፣ መቼ ወይም የት እንደ ሞተ አይዘገብም። ደብዛው ከታሪክ ገጾች በሙሉ ጠፋ።

የውጭ መያያዣዎች ለማስተካከል