ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ (፲፰፻፷፱ ዓ.ም. ተወለዱ) ሙዚቃቸው በሸክላ የተቀረፀው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ናቸው።

የሕይወት ታሪክ

ለማስተካከል

ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፥ካባታቸው፡ካቶ፡እሸቴ፡ጉቤ፡ከጐጃም፡በረንታና፡ከቦረና፡ጨከታ ፡ከናታቸው፡ከእማሆይ፡ወለተየስ፡ሀብቱ፡ከቡልጋ፡መስኖ፡ማርያም፡ይወለዳሉ።

የተወለዱት፥ሐምሌ ፳፡ቀን፥፲፰፻፷፱፡ዓ.ም.፥ምንጃር፡ቀርሾ፡ዐጥር፡በተባለው፡ስፍራ፡ነው።አባታቸው፡አቶ፡እሸቴ፥የራስ መኰንን፡ ጭፍራ፡ስለ፡ነበሩና፥መሰንቆም፡ስለሚጫወቱ፥ራስ፡መኰንንን፡ተከትለው፡ወደ፡ሐረር፡ሲኼዱ፥ነጋድራስንም፡በሕፃንነታቸው፡ይዘዋቸው፡ስለ፡ኼዱ፥ያደጉትና፡ዐማርኛ፡ትምህርታቸውን፡ያጠናቀቁት፡በሐረር፡ነው።

አባታቸው፡አቶ፡እሸቴ፥ሐረር፡እንዳሉ፡በመሞታቸው፥ነጋድራስ፥በወጣትነት፡ዕድሜ፥ዳግማዊ ዐፄ፡ ምኒልክን፡ተከትለው፡ወደ፡አዲስ አበባ፡መጡ።

፲፱፻፡ዓ.ም.፥ሙሴ፡ሆልስ፡የተባለ፡ጀርመናዊ፡በኢትዮጵያ፡ለብዙ፡ጊዜ፡ከቈየ፡በኋላ፥ወደ፡አገሩ፡ሲመለስ፥ዐፄ፡ምኒልክን፡በተሰናበተበት፡ጊዜ፥ጀርመን፡አገር፡ወስዶ፡የሚያስተምራቸው፡ሦስት፡ወጣቶች፡እንዲሰጡት፡ስለ፡ጠየቃቸውና፥ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴም፡በጥሩ፡ሠዓሊነታ ቸው፡በቤተ፡መንግሥቱ፡ስለ፡ታወቁ፦«ያ፡ተሰማ፡እሸቴ፥እጁ፡ብልኅ፡ነውና፥መኪና፡መንዳት ና፡መጠገን፡እንዲማር፡እሱ፡ይኺድ»፡ብለው፡ዐፄ፡ምኒልክ፡ስለ፡ወሰኑ፥ወደ፡ጀርመን፡አገር፡ለመኼድና፥ለኹለት፡ዓመት፡ያኽል፡የኦቶሞቢልን፡አሠራር፡ለመማር፡ቻሉ።

ነጋድራስ፥መሰንቆ፡መምታትና፡ዜማ፡ካባታቸው፡ተምረው፡ስለ፡ነበር፥ወደ፡ጀርመን፡አገር ፡ኼደው፡በቈዩበት፡ጊዜ፥ የተላኩበትን የሹፌርነትና የመካኒክነት ትምህርት አጠናቀው አጥጋቢ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የመጀመሪያውን የአማርኛ ዜማ ሸክላ እዚያው በጀርመን ሀገር ሆነው ለማስቀረፅ በቅተዋል። በጀርመን ቆይታቸው ወቅት "ሂዝ፡ማስተርስ፡ቮይስ"፡ከሚባለው፡ኩባንያ፡ጋራ፡በመዋዋል፥መዲናና ዘለሰኛ ዜማዎች በ፲፯ አይነት ስልት እየተጫወቱ ተቀርፀዋል። ኩባንያውም ለዜማው ባለቤት የድካም ዋጋ እንዲሆን በወቅቱ ፲፯ ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል። [1] ይህም፥ዐዲስ፡አበባ፡ሲመለሱ፥በሀብታሞች፡ደረጃ፡ለመቈጠር፡ዕድል፡ሳይሰጣቸው፡ አልቀረም።

ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴን፡እጅግ፡ታዋቂ፡ካደረጓቸው፡ነገሮች፡አንዱ፥የነዚህ፡ዲስኮች፡ ኢትዮጵያ፡መምጣትና፥ሌላም፡ያማርኛ፡ዲስክ፡ስላልነበረ፥ለኻያ፡ዓመት፡ያኽል፥ዐቅም፡ባለው፡ቤተሰብ፡ዅሉ፡በግራሞፎን፡ይሰማ፡የነበረው፡የሳቸው፡ዘፈን፡ብቻ፡በመኾኑ፡ነው።ሌሎች፡ያማርኛ፡ዲስኮች፡የተቀረጹት፡ጠላት፡ኢትዮጵያ፡ሊገባ፡ኹለት፡ዓመት፡ያኽል፡ሲቀር ፥በነፈረደ ጐላ፥በነንጋቷ ከልካይና፡በነተሻለ መንግሥቱ፡ተጫዋችነት፡ወደ፡፲፱፻፳፭-፲፱፻፳፮፡ገደማ፡ነው።

ዐዲስ፡አበባም፡እንደ፡ተመለሱ፥የቤተ፡መንግሥት፡መኪናዎች፡ኀላፊ፡ኾነው፥የዘመኑን፡ታዋቂ፡ኢትዮጵያውያን፡ሾፌሮች፡አሠልጥነዋል።ስለ፡ዐፄ፡ምኒልክ፡በተጻፈ፡አንድ፡የታሪክ ፡መጽሐፍ፡ላይ፥ነጋድራስ፡መኪና፡ላፄ፡ምኒልክ፡ሲያሳዩ፡የተነሡት፡ፎቶግራፍ፡አለ።ጸሓፊው፡ግን፥በስሕተት፥"ፈረንጅ፡ሲያስጐበኝ"፡ብሎ፡ጠቅሶታል።


  1. ^ "ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 6". Archived from the original on 2011-09-29. በ2010-12-18 የተወሰደ.

ይድነቃቸው ተሰማ «የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ዐጪር የሕይወት ታሪክ» ("ሠምና፡ወርቁ፡ተሰማ፡እሸቴ"፥ጥቅምት፡፲፱፻፹፭፡ዓ.፡ም.፥ገጽ፡1-9።)