ታይሥዌ
ታይሥዌ (ቻይንኛ፦ 太學 «ከፍተኛ ትምህርት») ወይም «የቻይና ቤተመንግሥት ዩኒቨርሲቲ» በቻይና በ6 ዓክልበ. በንጉሥ ፒንግ ሃን የተመሠረተ የጥንት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነበረ።
ከዚህም በፊት የቤተ-መንግሥታዊ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በቻይና ይታወቅ እንደ ነበር ይመስላል። በአፈ ታሪክ ትውፊታዊው ንጉሥ ሹን በ2050 ዓክልበ. ገደማ ሻንግ ሥያንግ የተባለውን ተቋም እንደ መሠረተ ተዘግቧል። እንዲሁም በሥያ ሥርወ መንግሥት (2000-1600 ዓክልበ. ግድም) ከፍተኛው ተቋም «ዶንግ ሹ» እንደ ተባለ ተጽፏል። በሻንግ ሥርወ መንግሥት (1600-1054 ዓክልበ.) ደግሞ ከፍተኛው ተቋም «ዮው ሥዌ» ይባል ነበር። በሚከተለውም ዦው ሥርወ መንግሥት (1054-229 ዓክልበ.) በዋና ከተማቸው ውስጥ አምስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነበሩዋቸው፣ ከነዚህም አንዱ «ታይሥዌ» ወይም «ፒ ዮንግ» ተባለ።
የሃን ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ፒንግ በዋና ከተማው በቻንግአን በ6 ዓክልበ. ከመሠረተው በኋላ፣ የቻይና ቤተ መንግሥት ከነዩኒቨርሲቲው በ17 ዓም ከዚያ ወደ ልዎያንግ ተዛወረ፣ እስከ 182 ዓም ድረስ እዚያ ቆየ። ከዚያም ዋና ከተማው፣ ቤተ መንግስትና ተቋሙ ብዙ ጊዜ ከቻንግ-አንና ከልዎያንግ መካከል ይፈራረቁ ነበር።
ተቋሙ ያስተማረው በተለይ የኮንግ-ፉጸ ትምህርትና የቻይና ሥነ ጽሑፍ ነበር፤ ከአገሩ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከፍተኛው ነበርና ይህም በተለይ ለመንግሥት ሠራተኞች ነበር።
ከጥንት ጀምሮ ተማሮች ያጠኑት «የኮንግ-ፉጸ ስድስቱ ሙያዎች» እንዲህ ነበሩ። 1) የኮንግፉጸ ሥርአተ ቅዳሴ፣ 2) የቻይና ባህላዊ ሙዚቃ፣ 3) ቀስትን ማስፈንጠር፣ 4) ሰረገላ መንዳት፣ 5) የቁም ጽሕፈት፣ 6) ሥነ ቁጥር ነበሩ።
በ2ኛው ክፍለ ዘመን 30,000 ሰዎች በተቋሙ ውስጥ ነበሩበት።
በ573 ዓም፣ የታይሥዌ ስያሜ «ጐዝርጅየን» («የአገር ልጅ ተቋም») ሆነ፤ በዚያውም ስም እስከ 1897 ዓም ድረስ በቻይና ልዩ ልዩ ዋና ከተሞች ቆመ። ከዚያ በኋላ የቤጂንግ ጐዝርጅየን (1395 ዓም ተሠርቶ) ወደ ዘመናዊው «ቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ተቀየረ፣ እስካሁንም ይገኛል። እንዲሁም በናንጂንግ የነበረው «ናንጂንግ አካዳሚ» ቀድሞ እንደ «ናንጂንግ ታይሥዌ» በ250 ዓም ተመሠርቶ፣ በ1894 ዓም ዘመናዊ ሆነ፣ አሁንም ናንጂንግ ዩኒቨርሲቲ ይባላል።