ባሕር ዳር ግንቦት ሃያ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ
የባሕር-ዳር ግንቦት ሃያ ዓለም አቀፍ ጥያራ ጣቢያ ከባህር ዳር ከተማ በስተ ምዕራብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት፣ በ፩ሺ፰መቶ፳፩ ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ የአየር ጣቢያ ነው።
ባሕር-ዳር ግንቦት ሃያ ዓለም አቀፍ ጥያራ ጣቢያ | |
የባህር ዳር ግንቦት ሃያ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ | |
ከፍታ | 1821 ሜትር |
ጥያራ ጣቢያው አንድ አስፋልት የለበሰ የሦስት ሺ ሜትር ርዝመት በአርባ አምስት ሜትር ስፋት ያለው የኮንክሪት ማኮብኮቢያ ያለው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እንደ ቦይንግ 757 የመሳሰሉ ሦስት የጭነትና አራት ቦምባርዲዬር የመንገደኛ ጥያራዎችን ለማቆም የሚያስችል ሥፍራ አለው። ጥያራ ጣቢያው ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉት እንደ ጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ የደህንነት ተቋማትና ኳራንቲን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ያሟላ ነው።
የባሕር-ዳር ግንቦት ሃያ ዓለም አቀፍ ጥያራ ጣቢያ በሳምንት በአማካይ ሃያ አንድ በረራዎችን በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአካባቢው እያደገ ለመጣው የአበባ፣ ፍራፍሬና አትክልት ምርቶች ማቆያ የሚሆንና 150 ቶን የማከማቸት አቅም ያለው የቀዝቃዛ መጋዘንም ከ50 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ገንብቶ አጠናቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሕር-ዳርን እና መቀሌን ከካርቱም ጋር ለማገናኘት የተጀመረው አዲሱ ዓለም አቀፍ በረራ የሁለቱን አገራት የንግድ፣ የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ ለማሸጋገር የላቀ ሚና እንደሚኖረው ሲገመት፤ የበረራ መስመሩ በሳምንት ለሦሰት ቀናት የሚከናወን ሲሆን ሰሜን ሱዳንን ከሰሜን የአገራችን ክፍል በቀጥታ የሚያገናኝ ነው።