የአስተሳሰብ ሕግጋት


የአስተሳሰብ ሕግጋት ማለት ማናቸውም ስሜት የሚሰጡ ሐሳቦች ሊከተሏቸው የሚገቡ ሕግጋት ማለት ነው። ይህ ፈላስፎች በዘመናት ላይ ያገኙት አንድ የሥልጣኔ ምርት ነው። እነዚህ ሕግጋት እጅግ መሠረታዊ እና ሁሉም የዕውቀት ዘርፍ ሊከተሏቸው የሚገባ ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሮ ሳይቀር ሊተገበሩ የሚገቡ ናቸው። የሕግጋቱ ብዛት ሦስት ሲሆን እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፦

ሕግ ፩)የተቃርኖ ሕግ፦ ሁለት ተቃራኒ ዓረፍተ ነገሮች፣ በአንድ ጊዜ እውነት ሊሆኑ አይችሉም። ወይንም በሌላ አነጋገር አንድ ዓረፍተ ነገር በአንድ ጊዜ እውነት እና ውሸት ሊሆን ከቶ አይችልም።
ሕግ ፪)መሃከል አግላይ ሕግ፦ አንድ ዓረፍተ ነገር ቢሰጥ፣ ወይ እራሱ እውነት ነው፣ ወይም ደግሞ ተቃራኒው እውነት ነው። ከዚህ ውጭ የሆነ፣ በሁለቱ ዓረፍተነገሮች መካከል ገብቶ እውነት የሆነ ሦስተኛ አረፍተ ነገር ፈጽሞ የለም። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ዓረፍተ ነገር ወይም እውነት ነው ወይም ውሸት ነው እንጅ ሌላ ሦስተኛ ነገር ሊሆን አይችልም።
ሕግ ፫)የማንነት ሕግ፦ ሁሉም ነገር ከራሱ ጋር አንድ አይነት ነው። በሌላ አነገጋገር አንድ አረፍተ ነገር እውነት ከሆነ፣ እውነት ነው። ይሄ ሕግ በጣም ግልጽ ቢመስልም አንድ አንድ ጊዜ ጥርጣሬ ላይ ሊዎድቅ ይችላል። ለምሳሌ የመታገስ ቁመት ሜትር ከሃያ ነው። የሚለው ዓረፍተ ነገር የዛሬ አስር አመት እውነት ቢሆን፣ ዛሬ ቁመቱ ሲጨምር ውሸት ይሆናል። ይሁንና፣ ህጉ ለሚቀየሩ ነገሮች ሳይሆን ባሉበት ለረጉ ነገሮች ብቻ ነው የተደነገገው።

እዚህ ላይ ተቃራኒ ሲባል ዘመናዊና የጠራ ትርጉም አለው፣ አለበለዚያ እላይ የተጠቀሱት ህግጋት አይሰሩም። ለምሳሌ፦ ሁሉም ሰው ኬኒያዊ ነው ለሚለው ዓረፍተ ነገር ተቃራኒ ቢፈለግ፣ ሁሉም ሰው ኬኒያዊ አይደለም እሚል ይሆናል። ይሁንና ሁሉም ሰው ኬኒያዊ አይደለም ማለት ምን ማለት ነው? ማንም ሰው ኬኒያዊ አይደለም ማለት ነውን ወይንስ አንድ አንድ ሰዎች ኬኒያዊ አይደሉም ነው? የመጀመሪያው ዓይነት ተቃርኖ ተጻራሪነት ይባላል። ይሁንና በዘመናዊ ሥነ አመክንዮ ተቃራኒ ሲባል ሁለተኛው ዓይነት ተቃርኖን ወይም በሌላ አነጋገር መጣረስ እሚለውን ዓይነት መንገድ ይይዛል። በሌላ አባባል እዚህ ጽሑፍ ላይ ተቃራኒ ሲባል መጣረስን እንጅ ተጻራሪነትን አይወክልም።

ነጭ እና ጥቁር በተለምዶ ተቃራኒ ተደርገው ይወሰዳሉ። ስለሆነም በ ሕግ ፪ መሰረት፣ ሁሉም ነገር ወይም ነጭ ነው፣ ወይም ደግሞ ጥቁር ነው። ይሁንና ይሄ አስተሳሰብ ስህተት ነው። ሁሉም ነገር ነጭ ነው ሚለው አረፍተ ነገር ተቃራኒ ሁሉም ነገር ነጭ አይደለም እሚል ነው። ስለሆነም ሕግ ፪ እሚሰራው ለዚህ አረፍተ ነገር ነው።