ሸንኖንግ (ቻይንኛ፦ 神農) በቻይና ልማዳዊ ታሪክ በኩል ከፉሢ ዘመን ቀጥሎ የነገሠው ንጉሥ ነበረ። በጥንታዊ ዘመን ግብርና እንዳስተማረ የሚል እምነት በአንዳንድ የቻይና መጽሐፍ ሊገኝ ይችላል። እንስሳን ለምግብ መግደል የማያስፈልግ ተግባር ይሆን ዘንድ፣ ሕዝቡን እህልን ለመዝራትና የማረሻ ጥቅም አስተማራቸው ይላል። የ«ሸንኖንግ» ትርጉም «ቅዱስ ገበሬ» ያህል ሲሆን፣ የቤተሠቡ ስም «ጅያንግ» እና የተሰጠው ስም «ሽዕንየን» መሆኑ ተጽፏል።

ሸንኖንግ ዕፅዋትን ሲቀምስ

ኋይናንዝዕ በተባለው መጽሐፍ መሠረት ከሸንኖንግ ዘመን አስቀድሞ ሕዝቡ ከረሃብና ከበሽታ ተቸገሩ። ሸንኖንግ ግን ለራሱ ምርመራ አድርጎ፣ ብዙ መቶ አትክልትን ቀምሶ በመሞክሩ፣ የእጽዋት ጥቅም በደንብ አስተማራቸው። በአንዱ ቀን 70 መርዞች በላ ይባላል። ሸንኖንግ በንጻው ጂንግ (የቅዱስ ገበሬ የእጽዋት ጽሁፍ) የተባለውን ጥንታዊ መጽሐፍ እንደጻፈ ደግሞ ይባላል። ይህ 365 መድኃኒቶችን ይዘርዝራል። በተለመደው አቆጣጠር በ2745 ዓክልበ. 70 መርዞችን የሚከላክለውን የሻይ ቅጠል በድንገት ወደ ፍል ውኃው ሲወድቅ መጀመርያው ያገኘው እሱ ነበር። እንዲሁም አክዩፐንክትየር (በመርፌ ለጤና መውጋት) እንደ ፈጠረ ይታመናል። በዘመኑ የቀጥር ገበያ እንዳስቆመ፣ ለ38 ዓመት እንደ ነገሠ ተጽፏል። ከሱ ዘመን በኋላ «የሸንኖንግ ነገድ» ወይም «የነበልባል ነገሥታት» እስከ ኋንግዲ (ቢጫው ንጉሥ) ዘመን ድረስ እንደ ገዙ ይጻፋል።