ስልክ ወይም ቴሌፎን (የግሪክ ቃል ከሆኑት τῆλε - ቴሌ፣ [ሩቅ ማለት ሲሆን] እና φωνή - ፎኔ፣ [ድምፅ ማለት ሲሆን] የመጣ ቃል ነው።) የመግባቢያ መሳሪያ ሲሆን ድምፅን (በዋናነት የሰዎችን) የመቀበል እና የማስተላለፍ ተግባር ያከናውናል። ይህ መሳሪያ በረዥም ርቀት ያሉ ሁለት ሰዎችን በድምፅ እንዲገናኙ ያስችላል።

የ1970ዎቹ ባለ መንኪያ ቁጥሮች ስልክ

ስልክ እንዴት ይሰራል

ለማስተካከል
 

ድምፅ ሞገድ ስለሆነ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ የሚል አቅም አለው። በተረፈ፣ የተለያዩ ድምጾች የተለያየ የሞገድ ይዘት ይኖራቸዋል፣ ስለሆነም የተለያዩ ቃላት እነሱን ሊለይ በሚችል መልኩ የራሳቸው የሆነ ሞገድ አላቸው። ስልክ የሚሰራው ይህን የድምጽ ጠባይ በመጠቀም ነው።

ከጎን እንደሚታየው፣ ሰውየው ቃላትን ሲናገር ከጥላሸት (ካርቦን) ዱቄቱ ፊት ለፊት ያለው ሽፋን ይርገበገባል፣ አንድ አንድ ቃላት ሽፋኑ በሃይል እንዲርገበገብ ሲያደርጉ ሌሎች በቀስታ ይሆናል። ይህ መርገብገብ በተራው የጥላሸቱ ዱቄት አንዴ በሃይል እንዲታመቅ ሌላ ጊዜ በላላ ሁኔታ እንዲሆን ያረጋል፣ የጥላሸቱ መታመቅና ፈታ ማላእት በተራው ከባትሪው መንጭቶ በውስጡ የሚያልፈው የኤሌክትሪክ ጅረት አንዴ ደመቅ አንዴ ቀዝቀዝ እንዲል ያደርጋል። የኤሌክትሪኩ ጅረት ሌላኛው ሰውየ ማዳመጫ ሲደርስ ማዳመጫው (ስፒከሩ) ከመጅመሪያው ሰውየ ንግግር አንጻር አንዴ ደመቅ አንዴ ደከም ብሎ እንዲርገበገብ ያደርጋል። በሌላ አነጋገር የመጀመሪያው ሰውየ የተናገረው ንግግር በዚህ መልኩ በሽቦው ውስጥ ይሻገራል። አሌክሳንደር ግርሃም ቤል የፈለሰፈው ስልክ ይህን አይነት ይዞታ ነበረው።