ለፊልሙ፣ ሳራን ይዩ።

ሣራመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የአብርሃም ሚስትና የይስሐቅ እናት ነበረች። በዑር ከላውዴዎን ተወልዳ ስሟ በመጀመርያ ሦራ (ወይም በዕብራይስጡ ሣራይ፥ «ልዕልቴ») ሲሆን በኋላ እግዚአብሔር ወደ «ሣራ» (ዕብራይስጥ ሣራህ፥ «ልዕልት») ቀየረው።

ሣራና አብርሃም፣ 1900 ዓ.ም. ግድም እንደ ተሣለ

ኦሪት ዘፍጥረት 20፡12 ዘንድ፥ አብርሃም ለጌራራ (ፍልስጥኤም) ንጉሥ ለአቢሜሌክ እንዳለው፣ ሣራ የአባቱ (ታራ) ልጅ ሆና በእውነት እህቱ ነበረች። በኩፋሌ 10፡47 ደግሞ አብራም የአባቱን ልጅ ሦራን እንዳገባት ይገልጻል። (ይህ አይነት ትዳር በእግዚአብሔር ሕገጋት የተከለከለው በሕገ ሙሴ ገና ወደፊት ነበር።)

ዘፍጥረት 17:17፥ ኩፋሌ 12:32 እንደሚለን የአብርሃም ዕድሜ መቶ ሲሆን የሣራ ዕድሜ 90 ዓመት ስለ ተባለ ከአብርሃም በኋላ 10 ዓመታት እንደ ተወለደች ይመስላል። ዘፍጥረት 23:1 እስከ 127 ዓመት በሕይወት ኖረች ይለናል። በኩፋሌው ዜና መዋዕል መሠረት ግን ሣራ በ2024 ዓመተ ዓለም ዐረፈች (14:22)፣ ይህ ከአብርሃም ልደት 148 አመታት በኋላ ሊቆጠር ስለሚችል (10:30) እነዚህ ቁጥሮች ሁሉ አይስማሙም። የሣራ ዕድሜ በዘፍጥረት 23:1 እስከ 138 ዓመት ድረስ ከሆነ ግን ሁላቸው ይስማሙ ነበር። በዕብራይስጥ ኦሪት ዘፍጥረት የተሠጡት ዕድሜዎች እንዲህ አይነት ልዩነት ስለሚበዛ፣ ይህ የአይሁድ ረቢዎች ቅጂዎች ግድፋት አልነበረም ለማለት አንችልም።

ሣራ በፈርዖን ቤተ መንግሥት፣ 1900 ዓ.ም. ግድም እንደ ተሣለ

ሦራ ከአብራም ጋራ ከዑር ወደ ካራን፣ ከካራንም ወደ ከነዓን ተጓዘች። አብርሃም የቤተሠቡ ባለቤት ሲሆን በከብትና በሎሌዎች ረገድ በጣም ሀብታም ሆነ። ረሃብ ወደ ከነዓን አገር በደረሰ ጊዜ ግን ወደ ግብጽ ሄዱ። የሣራህ ውበት ታዋቂ ነበረ፣ በዚያን ጊዜ የግብጽ ሰዎች ለራሳቸው እንዲይዟት ባሏንም አብርሃምን እንዲገድሉት የሚል ጭንቀት ለአብርሃም ነበረ። ስለዚህ እህቱ ብቻ እንደ ሆነች ለማለት አዘዛት። እንዲህ ሆነ፣ የግንጽም ፈርዖን ሣራን ወደ ቤተ መንግሥቱ ጨመራትና ለአብርሃም የብዙ ከብቶች ዋጋ ሰጠው። ሳይነካት ግን እግዚአብሔር ቤተ መንግሥቱን በመቅሠፍት መታ። ስለዚህ ፈርዖን በደሉን ስላወቀ አብርሃምን ሦራንና ከብቶቻቸውንም ከዚያ ሰደዳቸው። በኩፋሌ ዘንድ እነሱ በግብጽ ለ7 ዓመታት ቆዩ፣ ግብፃዊት ባሪያዋን ሀጋርን በዚህ ዘመን እንዳገኙ ይሆናል።

ሣራ በ1545 ዓ.ም. እንደ ተሣለች

ሣራ እስካሁን ድረስ መካን ሆና ልጅ እንዲገኝ ባሪያዋን ሀጋርን ለአብራም እንደ ሁለተኛ ሚስት ሰጠቻት (ዘፍጥረት 16:3)። ሀጋር የአብርሃም ሚስት ምንም ብትሆን ግን ለሣራ በባርነት ቆየች፣ ስለዚህ ርጉዝ ከሆነች በኋላ በሀጋርና በእመቤቷ በሣራ መካከል መቀኝነት መጣ። ሀጋር ለአብራም እስማይልን ወለደች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሥላሴ አብርሃምን በከነዓን ሲጎበኙ ሣራ እራሷ ልጅ እንድትወልድ አሉ። ሣራም በዕድሜዋ ልጅ እንድትወልድ ሰምታ በልብዋ ሳቀች። እግዚአብሔር ለኔ ምንም የማይቻለኝ ሥራ የለም አላቸው። ልክ እንዳላቸውም ሣራ ለአብርሃም ልጁን ይስሐቅ ወለደ። ከዚህ በኋላ ከእመቤቷ ጋር ስለ ነበረው መቀያየም አጋርና እስማይል ሸሽተው የእስማይል ልጆች በፋራን ምድረ በዳ ሠፈሩ።

ሣራ ገና እርጉዝ በነበረችበት ወቅት በጌራራ ሲቆዩ፣ አብርሃም እንደገና እህቴ ብቻ ናት ብሎ አስመሰለ። እንደ ዘመኑ ልማድ የአገሩ ንጉሥ አቢሜሌክ ለራሱ እንድትሆን ወሰዳት። እንደገና ንጉሡ ሳይነካት እግዚአብሔር ማለደ፣ በሕልሙ ውስጥ ዛተው። የእግዜር ፈቃድ ከአቢሜሌክ ይልቅ አሸነፈና ያንጊዜ ሣራ በነጻ ወጣች፣ አቢሚሌክ ደግሞ ለአብርሃም ብዙ ከብትና ብር ጨመረ (ዘፍጥረት ምዕራፍ 20) ።

ሣራ ቢያንስ 127 ዓመታት ሆና ባረፈችበት ዘመን አብርሃም ለመቃብር አንድ ዋሻ በኬብሮንኬጥያዊው ሰው ኤፍሮን ገዛ።

ሣራ የታማኝነት አራያ ሆና በአዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ ትከበራለች -- ሮማውያን 4፡19፣ 9፡9፤ ዕብራውያን 11፡11፣ ወደ ገላትያ ሰዎች 4፡22-26፤ 1 ጴጥሮስ 3፡6።

ቁርአን ደግሞ ሣራ በስሟ ባትጠቀስም በዘፍጥረት ከተገኘው ታሪክ ብዙ አይለይም።

በኋላ የአይሁድ ረቢዎች (ከፈሪሳውያን ወገን የወጡ) እንደ ልማዳቸው ስለ ሣራ የጻፉት ተጨማሪ መረጃዎችና ትችቶች ብዙ አሉ።