ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በ፲፰፻፺፯ ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ውስጥ የተወለዱ ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ሰው ከመኾናቸው ባሻገር፤ በፈረንሳይ አገር የግብርና ትምሕርት ያጠናቀቁ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በ ስልጣንም መጀመሪያ የ ልዑል አልጋወራሽ መርድ አዝማች አስፋ ወሰን ፀሐፊ፤ የእርሻ ሚኒስቴር ምክትልና ዋና ሚንስትር፤ የገንዘብ ሚኒስትር፤ የሕዝብ አገልግሎት ሚኒስትር እንዲሁም የዘውድ አማካሪ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።
በታሪክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውና አጠቃላዩን የኢትዮጵያን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚዘክረውን «ዝክረ ነገር» የተሰኘውን መጽሐፍ በ ፲፱፻፵፪ ዓ.ም. ለህትመት አብቅተዋል። እኚህ ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው፤ በታሪክና ባህል፤ በትምህርተ ጥበባት እና በመንፈሳዊ ግንባራት አሥራ አምስት መጻሕፍትን አበርክተዋል። እነዚህም መጻሕፍት
አንደኛ ክፍል፦ ታሪክና ባህል
- ዝክረ ነገር (ሁለት ጊዜ ታትሟል)
- ያባቶች ቅርስ (ሦስት ጊዜ ታትሟል)
- እንቅልፍ ለምኔ (ሦስት ጊዜ ታትሟል)
- አማርኛ ቅኔ ነጠላ (አምስት ጊዜ ታትሟል)
- ስለ ኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት አስተዳደርና ግብር
- አማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው (ሦስት ጊዜ ታትሟል)
- ያገር ባህል (ቡልጋ)
- ባለን እንወቅበት
- የቀድሞው ዘመን ጨዋ ኢትዮጵያዊ ጠባይና ባህል
- ቼ በለው
ሁለተኛ ክፍል፦ ትምሕርተ ጥበባት
- ጥበበ ገራህት (የ እርሻ መሬት ዝግጅት)
- ብዕለ ገራህት (ከ እርሻ የሚገኝ ብልጽግና)
ሦስተኛ ክፍል፦ አንክሮ ለእግዚአብሔር፤ ተዘክሮ ለነፍስ (መንፈሳዊ)
- ዕጹብ ድንቅ
- ስም ከቃብር በላይ
- ሰዋስወ ሰማይ
ጥቅስ
ለማስተካከልብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ቋንቋችን ባህላችንን፤ ልማዳችንን እና መንፈሳችንን የሚይስተጋባ አንዱ ትውልድ የሚከተለውን ትውልድ የማስተማርና ይኼን ቅርሳችንን የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል። «ወላጆች ለልጆቻቸው በየጊዜው አንዳንድ ግጥም እየሰጡ ሠምና ወርቁን እንዲለዩ፤ በውስጡ ተሸፍኖ የሚገኘውን ድርብ ምስጢር መርምረው ተጨንቀውና ተጠበው እንዲያወጡና እንዲያስፋፉትም ቢያደርጓቸው የሚገኘው ፍሬ አስደሳች ይሆናል። ወጣቶቹ የሚሰለቹ ቢሆን እንኳ ኮሶ እየመረረ ካልተዋጠ ፈውስን አይሰጥምና እየተከታተሉ ማሠራቱ ዋጋ አለው፤ ይጠቅማልም።»[1]
እንዲሁም፦ «እኛ ኢትዮጵያውያን አገራችን ጥንታዊት መሆኗን ሥልጣኔም በመሻት ዐዋቆችና አስተዋዮች አባቶቻችን በብዙ የደከሙ መሆናቸውን በመገንዘብ ላገራችን ወጣቶችም ሆነ ወይም ለውጭ አገር ሰዎች እውነተኛውንና ምስክርም ሊሆን የሚገባውን ሁሉ እየሰበሰብን ማዘጋጀት፤ ለመጭውም ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ አለብን።»[2]