ነብኸፐትሬ መንቱሆተፕ ግብጽን ከጤቤስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። በ39ኛው ዓመት በግብጽ ስሜንና ደቡብ ውሕደት አገሩ እንደገና አንድ ሆኖ የ11ኛው ሥርወ መንግሥትየግብጽ መካከለኛ መንግሥት መጀመርያ ፈርዖን ይቆጠራል።

ነብኸፐትሬ መንቱሆተፕ፣ የሁለቱ ዘውዶች ተጭነው በዙፋን ተቀምጦ

በዘመኑ መጀመርያ መንቱሆተፕ ዋና ከተማውን በጤቤስ በግብጽ ደቡብ ክፍል መሠረተ። ከዚያ በፊት «1 መንቱሆተፕ» የሚባል መሪ በጤቤስ እንደ ተገኘ አሁን ይታስባል። ለ1 መንቱሆተፕ ሕልውና ብዙ መረጃ ወይም ቅርስ ባይገኝም ለዚሁ ነው ዘመናዊ ሊቃውንት ይህን ፈርዖን «2» መንቱሆተፕ የሚሉት። ብዙዎች ደግሞ የመንቱሆተፕ ዘመን ከ3 አንተፎች (አንተፍ 1, 2, 3) በኋላ እንደ ደረሰ ያደርጉታል። በዕድሜው ጥንትነት የተነሣ ልክ መቼ እንደ ገዛ መነሻውም ከየት እንደ ሆነ ብዙ ተቃራኒ አስተሳስቦች አሉ። የንጉሡም ስም በየጊዜ ስለተቀየረ አጠያያቂ ጉዳዮች አሉ። የቶሪኖ ፈርዖኖች ዝርዝር የሚባል ሰነድ የ51 ዓመት ዘመን ይሠጠዋል፤ ለጨለማ ዘመን ግን ይህ ምንጭ በጣም ታማኝ አይሆንም።

መንቱሆተፕ በዘመኑ መጀመርያ «ሔሩ ሳንቂብታዊ» የሚለው የሔሩ ስያሜ ወሰደ። በ14ኛው ዓመት በስሜን ግብጽ በሄራክሌውፖሊስ ከገዛው ፈርዖን ከመሪካሬ ጋራ ጦርነት ተነሣ። በዚያ ጊዜ ፈርዖኑ «ነብኸፐትሬ» የሚለውን ስም ጨመረ፤ የሔሩ ስያሜውም «ሔሩ ነጨሪኸጀት» ሆነ። በዚህ ጦርነት ውስጥ የአሥዩት ገዦች ለመሪካሬ እንደ ዘመቱ ይታወቃል። እንዲሁም በ1920ዎቹ በሥነ ቅርስ በጤቤስ አካባቢ የ60 ወታደሮች አስካሬኖች በውግያ ተገድለው የመንቱሆተፕ ስም በከፈናቸው ላይ ታትሞ ተገኝተዋል።

ከስሜኑ ጋር እየተዋገ በ29ኛውና በ31ኛው ዓመቱ ወደ ደቡብ ደግሞ በኩሽ መንግሥት ላይ ዘመተ። በመጨረሻ ሠራዊቶቹ አሥዩትን አሸነፉ። መሪካሬ ያንጊዜ ሞተና ከትንሽ በኋላ መንቱሆተፕ ሄራክሌዎፖሊስን ይዞ የሁለቱን መንግሥታት ንጉሥ ሆነ። ይህ በ39ኛው ዓመቱ ሆኖ የሔሩ ስያሜውን እንደገና ቀይሮ «ሐሩ ሸማታዊ» ሆነ።

መቃብሩ በጠቤስ ዙሪያ እስካሁን ይገኛል። ፈርዖኑ እራሱ የአረመኔ አምላክ ኦሲሪስ ትስብእት እንደ ተቆጠረ ይታወቃል። ይህም እምነት ለብዙ ዘመናት በ12ኛው ሥርወ መንግሥት ዘመንም ይቀጠል ነበር። ከሚስቶቹም ለሥነ ቅርስ የታወቁት ነፈሩ፣ ተም፣ ካዊት፣ ሳደህ፣ አሻዪት፣ ኸንኸነት እና ከምሲት ናቸው።

ቀዳሚው
መሪካሬ
ግብፅ ፈርዖን ተከታይ
1 አንተፍ