ማስሩቕ (መስሩቕ፣ መስሩቅ፡ 595 አ.ም ገደማ) በየመን የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሥ፣ በየመን የኢትዮጵያ ንጉሥ ኣብረሃ የመጨረሻው ልጁ ሆኖ ከታላቅ ወንድሙ ከአክሱም ቀጥሎ በየመንና አካባቢው ግዛቶች በዙፋን የተቀመጠ። እናቱ ንግስት ሪይሃና ትባላለች። ከወንድሙ ከያክሱም ጋር የአንድ አባትና እናት ልጆች ናቸው። ሪይሃና ከየመን ልዑላን ቤተሰብ የምትወለድ ስትሆን ሥሙ ዙል-ያዛን (ዱ-ያዛን) ከተባለ፣ ከሂምሪያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አንዱ ክፍል ከሚወለድ የመጀመሪያ ባልዋ ላይ በግድ ጠልፎ ነው ንጉሥ ኣብረሃ ያገባት። የወንድማማቾቹ በእናታቸው የመናዊ መሆን ከሕዝቡ ተቀባይነት ለማግኘት ብዙም አልረዳቸውም። ከወንድሙ ከያክሱም ንግስና ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያውያን ወራሪ ኃይልና ዝና እያሽቆለቆለ ሄዶ በምትኩ ሥርዓት አልበኝነት፣ ተቃውሞና ጥላቻ በየመን እያየለ ሄዶ በንጉስ ማስሩቅ ጊዜ ወደ ፍጹም የከፋ ረብሻና አለመረጋጋት ተቀይሮ ነበር። እንዲሁም ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ ሲባል ከባድ ጭቆና በሕዝቡ ላይ ይታይና ይደርስ ጀመር። የመኖች ከውጪ ሌላ ረዳትና ኃይል እስኪያገኙ ድረስ ግን የኢትዮጵያዉን ንጉስ ማስሩቅ ከሥልጣኑ የሚያነቃንቀው ደረጃ የደረሰ ኃይልና እንቅስቃሴ አልተገኘም።


የዘጠነኛው ክ/ዘመን ጸሃፊ ታብሪን እንደዘገበው ከሆነ ለንጉስ ማስሩቅ ውድቀት፣ ብሎም ለኢትዮጵያ የባሕር ማዶ ግዛት ማክተም አንዱና ዋንኛ ምክንያት የሆነው የገዛ ግማሽ ወንድሙ ሠይፍ ማዕዲ ካሪብ ኢብን ዱ-ያዛን ነው። ሠይፍ ማዕዲ በአብረሃም ቤት ያደገና ከቀሪው ልጆቹ እኩል እንደ ገዛ ልጁ አብረሃም ያሳደገው ልጁ ሲሆን ሠይፍ ማዕዲም ቢሆን አባቱ አብረሃም እንደሆነ ነበር የሚያውቀው። ከዕለታት አንድ ቀን በርሱና በወንድሙ ማስሩቅ መካከል በተነሳ ጭቅጭቅ ውስጥ የዱ-ያዛን ልጅ መሆኑን ይረዳል። ሠይፍ ማዕዲም ከጥንቱ የየመናዊው ንጉሣዊ ቤተሰብ የሚወለድ መሆኑንና ዙፋኑ ለርሱ የሚገባ መሆኑን አውጆ እርዳታ ለማግኘት የመንን ለቅቆ ኮበለለ።

ለሠይፍ ማዕዲ የእርዳታ ጥሪ መልስ የሰጠው የታላቋ ፋርስ ንጉሥ ቀዳማዊ ኾስሩ ኑሺርዋን፣ 800 ከሚደርሱ በሕግ ሥር ካሉ ወታደሮች ጋር ዕድሜው 80 ዓመት የደረሰውን ባለ አንድ ዓይና የጦር አበጋዝ ዋህራዝ በመርከብ ወደ የመን ላከ። በፐርሺያ ጦር ቁጥር ማነስ የተነሳ የአበሻው ንጉስ ማስሩቅ ጠላቶቹን እጅግ አናንቆ ነበር የተመለከታቸው። በዚህም የተነሳ የፐርሺያ ጦር የየመን ወደብን ከረገጠ ጀምሮ ከአንድ ወር ጊዜ በላይ ሳይዋጋቸው የመወስኛ ዕድል ሰጣቸው። እንዲያውም ለዋህራዝ ጦር የምግብና ሌላም ስንቅ ያሉበት ድረስ ለስላቅ ይልክላቸው ነበር። ይህ ያልተጠበቀ ዕድል ለፐርሺያ ጦር ጥሩ የእረፍትና የጦር ዝግጅት እንዲያደርግ ረዳው። ሠይፍም ከየመን የሂምያር መሳፍንት ቤተሰቦች ጋር እየተላላከ ደጋፊና ወገን ለመሰብሰብ አስቻለው። በመጀመሪያው ዙር ጦርነት፣ ንጉስ ማስሩቅና ዋህራዝ ሁለቱም ልጆቻቸውን በአዝማችነት ልከው የሁለቱም ልጆች በጦርነቱ ተገደሉ። በዚህ ጦርነት ላይ የፐርሺያዎች የቀስት ፍላጻ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። የኢትዮጵያ ጦር ከጦርና ጋሻ በስተቀር ቀስትን በወቅቱ ስላልታጠቀ፡ እራሱን ላልተመጣጠነ ጉዳት አጋለጠ። አበጋዙ ዋህራዝ በመቀጠል ይዘውት የመጡትን መርከቦች በማቃጠል፡ የሠራዊቱን የመሸሽ ዕድል አጨልሞ ፈጽሞ እንዲዋጋ አሰልፎ አዘጋጀው። ለወሳኙ ጦርነት፣ ንጉሥ ማስሩቅ እራሱ በዝሆን ላይ ተቀምጦ፣ ግምባሩ ላይ ሩቢ አድርጎ ወደ 100 ሺህ የሚገመት ሠራዊቱን እየመራ ለጦርነት ተሰለፈ። አንድ አይናው ዋህራዝ ቀስቱን ደግኖ የማስሩቅ ሩቢ ላይ በማነጣጠር የለቀቃት ፍላጻ በአፍታ ማስሩቅን ግምባሩን ነድላ ገደለችው። በዚህ የተሸበረው የኢትዮጵያ ጦር ተበታተኖ ለሽንፈት እንዲዳረግ ምክንያት ሆነ።

በዚህ ጦርነት የተገባደደው የአክሱማዊያን የየመን ግዛት ሥልጣን፣ በፐርሺያዎች የበላይ አስተዳደርነት ተተክቶ ሙስሊሞች ወደ የመን እስከሚመጡ ድረስ ፀና።