ሻሩም-ኢተርሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ ማሪሱመር ላዕላይነቱን በያዘበት ጊዜ የማሪ ንጉሥ ነበር።

በዚህ ዘመን ላዕላይነት ማለት የሱመር ዋና ከተማ ኒፑርን የገዛው ወገን ነበር። በዝርዝሩ ሰነድ ዘንድ፥ ከአዳብ ንጉሥ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ ዘመን በኋላ አዳብ ተሸነፈና የሱመር ንጉሥነት ከአዳብ ወደ ማሪ ተዛወረ። እንዲህ ከማለት ቀጥሎ 6 የማሪ ነገሥታት ስሞች ይዘርዝራል። አንቡ፣ አንባ፣ ባዚ «የቆዳ ሠሪ»፣ ዚዚ «የሱፍ ሠሪ»፣ ሊመር «ቄስ» እና ሻሩም-ኢተር ናቸው። እነዚህ ስሞች ከሌላ ምንጭ በተለይ በማሪ ፍርስራሽ ከተገኙት ጽላቶች ገና አይታወቁም። ደግሞ እነዚህ ሁሉ የማሪ ገዦች ወይም ከንቲቦች ቢሆኑም፣ ሁላቸው በመላ ሱመር ላዕላይነቱን እንደ ያዙ አይመስልም። ስለዚህ ከእነዚህ 6 ስሞች ምናልባት መጨረሻው ብቻ እሱም ሻሩሚተር የመላ ሱመር ላዕላይነት የያዘ ነበር የሚል ሀሣብ ቀርቧል።[1] የሻሩም-ኢተር ትርጉም ፍች ከአካድኛው ሻሩም «ንጉሥ» እና ኢተር «የላቀ» ነው። በዝርዝሩ በልዩ ልዩ ቅጂዎች ዘንድ ወይም 7 ወይም 9 ዓመታት ገዛ።

ከሻሩም-ኢተር ቀጥሎ «ማሪ ተሸነፈና የሱመር ንጉሥነት ከማሪ ወደ አክሻክ ተዛወረ» በብዙ ቅጂዎች ይላል። ሌሎች ቅጂዎች እንዳሉ ግን፣ ቀጥታ ወደ ኪሽ ንግሥት ኩግባው ነበር የተዛወረው። ከአክሻክ ነገሥታት ስሞች፣ አንዱ ብቻ ከሌላ ጽላት ይታወቃል እሱም ፑዙር-ኒራሕ ነው። በዚያው ጽላት ፑዙር-ኒራሕ የኩግባው ቀዳሚ ይባላል። ስለዚህ ላዕላይነቱ ከሻሩሚተር በኋላ ወደ አክሻክ ተዛወረ ማለት ትክክለኛ ይመስላል፣ ከአክሻክ ገዚዎችም ፑዙር-ኒራሕ ብቻ ላዕላይነቱን (ኒፑርን) የያዘው ይሆናል።

ከማሪ እና ከኤብላ ከተገኙት ጽላቶች እንደሚታወቅ በዚሁ ዘመን የማሪ ንጉሥ ስም በማሪኛ «ሒዳዓር» ይጻፋል። በማሪ ለ፴፭ አመታት እንደ ገዛ ይታወቃል። በኤብላ ንጉሥ ኢሻር-ዳሙ 32ኛው ዘመነ መንግሥት (2077 ዓክልበ.) የኤብላ ዋና ሚኒስትር ኢቢ-ዚኪር ይህን ሒዳዓር አሸነፈው። በአንዱ ጽላት የሚስቱ ስም «ፓባ» ይሰጣል።[2]

ቀዳሚው
አዳብ ንጉሥ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ
ሱመር (ኒፑር) ገዥ
2107-2100 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
አክሻክ ንጉሥ ፑዙር-ኒራሕ
ቀዳሚው
ኢኩን-ኢሻር
ማሪ ንጉሥ
2112-2077 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ኢሽቂ-ማሪ
  1. ^ Mari at Historyfiles
  2. ^ ዳግላስ ፍረይን፣ ጥንታዊ መዝገቦች (እንግሊዝኛ)