1 ኢድሪስ (አረብኛ፦ إدريس الأو ሙሉ ስም፦ ሳዪድ ሙሐማድ ኢድሪስ ቢን ሙሐማድ አል-ማህዲ አስ-ሰኑሢ) ከ1944 እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ የሊቢያ ንጉሥ ነበሩ። እንዲሁም ከ1908 ዓ.ም. ጀምሮ የሰኑሢ እስልምና ወገን አለቃ ነበሩ።

የሊቢያ ንጉሥ ኢድሪስ

1912 ዓ.ም. ሊቢያ የጣልያን ግዛት በሆነበት ጊዜ፣ ኢድሪስ የቀሬናይካ ክፍላገር ኤሚር የሚል ማዕረግ አገኙ። በተጨማሪ በ1914 ዓ.ም. የትሪፖሊታኒያ ክፍላገር ኤሚር ሆኑ። ዳሩ ግን በዚያ አመት ከጣልያኖች ጋር በመጣላት ወደ ግብጽ ሔዱ። በ2ኛው ዓለማዊ ጦርነት ጣልያኖች ከተሸነፉ በኋላ ኢድሪስ ወደ አገራቸው ተመለሱ። በ1944 ዓ.ም. አዲሱ የሊቢያ መንግሥት በተመሠረተ ጊዜ «የሊቢያ ንጉሥ» የሚል ማዕረግ ተሰጡ።

ንጉስ ኢድሪስ በ1957 ዓ.ም.

በ1961 ዓ.ም. ጤንነታቸው ደክሞ ዘውዳቸውን ለወራሻቸው የወንድማቸው ልጅ ልዑል ሃሳን አስ-ሰኑሢ ለመተው አሰቡ። ለሕክምና በቱርክ አገር ሲቆዩ ሃሳን አስ-ሰኑሢ ዘውድ ከተጫኑ ከ1 ቀን በፊት የሠራዊት አለቃ ሙአማር አል-ጋዳፊ ተነሣና መንፈቅለ መንግሥት አካሔደ። ኢድሪስ እንደገና በስደት ወደ ግብጽ ተመለሱና በዚያ በ1975 አ.ም. አረፉ።

የሊቢያ መንግሥት (1944-1961) ሰንደቅ ዓላማ።

ከ1944 እስከ 1961 ድረስ እሳቸው የሊቢያ መንግሥት ብቸኛ ንጉሥ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በጋዳፊ መንግሥት ላይ የተነሡት ተቃዋሚ ወገኖች ብዙዎቹ የሰኑሢ ወገን ደጋፊቆች ሆነው በኢድሪስ ዘመን የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ የሚይዙ ሲሆኑ ታይተዋል። የሰኑሢ አልጋ ወራሽ አሁን ልዑል ሙሐማድ አስ-ሰኑሢ ሲሆኑ በስደት በእንግሊዝ ኖረዋል። ባለፈው የካቲት 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ጋዳፊ ቢሸነፍ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ዘውድ ስለ መጫናቸው በአል-ጃዚራ ዜና ሲጠየቁ፣ ይህ በሊቢያ ሕዝብ የሚበየን ጉዳይ ይሆናል ብለው መለሱ።