ጋውማታ
ጋውማታ ወይም ሐሣዌ ሥመርዲስ ወይም ስፈንዳዳቴስ (530 ዓክልበ. ሞተ) በጥንታዊ ፋርስ መንግሥት እኔ የንጉሡ የታላቁ ቂሮስ ልጅ ነኝ በማለት ያባበለ አስመሳይ ነበር።
በቂሮስ በኲር በካምቦሲስ ዘመነ መንግሥት ካምቦሢስ ታናሽ ወንድሙን ባርዲያን አስገድሎ ነበር። በኋላ ግን ኮምቦሲስ በግብጽ ሳለ አንድ ማጎስ (የዞራስተር እምነት ቄስ) እና የሜዶን ሰው ጋውማታ እንደ ተገደለው ባርዲያ እራሱን ባማስመስል በአመጽ ተነሣ። ካምቦሲስ በድንገት ሞተና ጋውማታ ለአጭር ጊዜ ፋርስን ገዛ። ሐሣዊ መሆኑ በታወቀ ጊዜ፣ ፯ መኳንንት ከነርሱም ፩ ዳርዮስ ጋውማታን በደፈጣ ገደሉት፣ ከነርሱም ዳርዮስ ለዙፋኑ ተመረጠ።
ይህ ዳርዮስ እራሱ በገደል ድንጋይ ላይ ባስቀረጸው በበኂስቱን ፅሁፍ ይተረካል፣ እንዲሁም ፪ የግሪክኛ ጸሐፍት ሄሮዶቶስ (480 ዓክልበ)ና ክቴሲያስ (400 ዓክልበ.) ይተርኩታል። በታሪኩ ዝርዝሮች ትንሽ ይለያያሉ።
የበኂስቱን ጽሁፍ እንደሚለው ካምቤሲስ የሞተው በገዛ እጁ ነበር። ከዚህም በኋላ በዳርዮስ ዘመነ መንግሥት አንድ ሌላ አመጸኛ ደግሞ «ቫህያዝዳታ» እኔ ባርዲያ ነኝ በማለት አስመስሎ ዳርዮስ እሱንም አስገደለው።
በሄሮዶቶስ ውስጥ የቂሮስ ልጅና አስመሳዩ ሁለቱም «ስመርዲስ» ተብለዋል። በክቴሲያስ ዘንድ፣ የቂሮስ ልጅ ስም «ታኞክሳርኬስ» ነው፣ አስመሳዩም «ስፈንዳዳቴስ» ይባላል። በነዚህ ግሪኮች ዘንድ ካምቦሲስ በገዛ ሠይፉ የሞተው ከድንገት ነበር። በሌሎች ጥቃቅን ዝርዝሮች ይለያያሉ።