ዳ ዩ (ቻይንኛ፦ 大禹 «ታላቁ ዩ») በቻይና አፈ ታሪክ የጥንታዊ ቻይና ንጉሥና የሥያ ሥርወ መንግሥት መስራች ነበር።

ዳ ዩ

በአንዳንድ ምንጭ ዘንድ የዩ አባት ጉን ነበረ። የቀርከሃ ዜና መዋዕል በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ በኋሥያ ንጉሥ ሹን ዘመን (በ2059 ዓክልበ. ግድም) ዩ አዲስ የሥራዎች ሚኒስትር ሆኖ የወንዞቹን ጎርፍ ገደበ። በ2058 ዓክልበ. ዩ የጻውወይ ሥራዊት አሸነፈ። በ2047 ዓክልበ. አገሩ በ፲፪ ክፍላገራት ተከፋፈለች። አሁን «ዳ ዩ» ከሹን ጋር እንደ ጋርዮሽ ንጉሥ ተቆጠረ። በ2028 ዓክልበ. ዩ በይፋ የሹን አልጋ ወራሽ ሆነ፤ አገሩም ከ፲፪ ወደ ፱ ክፍላገሮች አከፋፈል ተመለሰ። በ2026 ዓክልበ. ዩ የዮውምያው ብሄር አሸነፈ፣ የኋሥያ ተገዦች ሆኑ። በ2010 ዓክልበ. ሹን አረፈና ዳ ዩ የሥያ ሥርወ መንግሥት መስራች ሆነ።

የዳ ዩ ፱ ክፍላገራት (አንድ አስተያየት)

ከዚህ በኋላ ዩ ለ፰ ዓመታት ለብቻው ገዛ። ነገር ግን በጠቅላላ ከሹን ጋራ ዘመኑ ፵፭ ዓመታት ይቆጠራል። በመጨረሻው ዓመት (2002 ዓክልበ. ግድም) መኳንንቱን ወደ ስብሰባ ጠርቶ ከመኳንንቱ አንድ ፋንግፌንግ የሚባለው ወደ ስብስባው ስለ ዘገየ፣ ዳ ዩ ይሙት በቃ ፈረደበት። በኋለና ዘመን ብዙ ትውፊቶች ስለዚህ ፋንግፈንግ ተነሡ። በዚያውም ዓመት ዩ አረፈና ከሦስት ዓመት ልቅሶ በኋላ ልጁ በ1999 ዓክልበ. ተከተለው።

ዘጠኙ ክፍላገራትና አምስቱ ካሬዎች

ሹ ጪንግ ወይም «ብሉይ ሰነዶች» መሠረት፣ ከዘጠኙ ክፍላገራት በላይ ዩ «መላውን ዓለም» በካሬ ዞኖች አከፋፈለ። ከዋና ከተማ ቤተ መንግሥት ዙሪያ እስከ 500 ድረስ (እስከ 200 ኪሎሜትር ድረስ) መጀመርያው ወይም «ንጉሣዊ ዞን» ሆነ፣ የሚኖሩበት እህልን ይገብራሉ። ከዚያ ዙሪያ እስከ ሌላ 500 ሊ ድረስ «የመኳንንት ዞን» ሆነ። ከዚያም ዙሪያ ሦስተኛው ካሬ ዞን «የጸጥታ ሃይል ዞን» ሲሆን የሚኖሩበት ሠልፍ ይለመዱ ነበር። ከዚያም ዙሪያ አራተኛው ካሬ ዞን «የክልካይ ዞን» ተባለ፤ መጀመርያ 200 መቶ ሊ የ ሕዝቦች፣ አፍአ 300 ሊ ቀላል ግዞት የተፈረደባቸው ሰዎች የሚገኙበት ይሆን ነበር። አምስተኛው ካሬ ዞን ወይም «አውሬ ዞን» ያልተሠለጠኑ ሕዝቦችና ከባድ ግዞት የተፈረደባቸው ሰዎች የኖሩበት ነበር። ከዚህ አምስተኛው ካሬ ውጭ የተረፈው አገር ሁሉ ከቤተ መንግሥት ከ1000 ኪ/ሜ በላይ ርቀት ሆኖ በፍጹም አረመኔዎች የታሠቡት ሕዝቦች መኖርያ ነበር። ይህ ዕቅድ በታሪክ መቸም ተግባራዊ ባይሆንም፣ እስከ 1800 ዓም ያህል ድረስ ለቻይና መሪዎች የአስተሳሰብ ምሳሌ ሆኖ ቀረ።

ቀዳሚው
ሹን
የሥያ (ቻይና) ንጉሥ ተከታይ