ዳኛዋቲ
ዳኛዋቲ (በርምኛ፦: ဓညဝတီ ፣ ፓሊኛ፦ /ዸኘቨቲ/) በጥንታዊ አራካን (አሁን ረክሃይን ክፍላገር ሚየንማ) እና በአፈ ታሪክ የነበረ የከተማ፣ የ፫ ሥርወ መንግሥታትና የሀገር ስም ነበረ።
ለነዚሁ ፫ ቅድመ ታሪካዊ ሥርወ መንግሥታት አንዳችም ቅርስ እስካሁን ባለመገኘቱ፣ ከትውፊትና አፈ ታሪክ ብቻ ይታወቃሉ።
በአራካን ታሪክ፣ እስከ 1420 ዓም እስከ ምራውክ-ኡ መንግሥት ምንም እርግጠኛ አቆጣጠር ወይም መዝገብ የለም።
የእንግላንድ ጸሐፊ አርሰር ፈይር በ1825 ዓም በጻፈው የበርማ ታሪክ አቆጣጠር፣ የልማዳዊ ነገሥታት ዝርዝር ለነዚህ ፫ ዳኛዋቲ ሥርወ መንግሥታት ከ2674 ዓክልበ. ጀምሮ እስከሚከተለው እስከ ዌሻሊ መንግሥት እስከ 780 ዓም ድረስ ቆየ። በእርሱ አከፋፈል ዜና መዋዕሉ እንዲህ ያመልክታል፦
- መጀመርያው ዳኛዋቲ መንግሥት፣ 2674-833 ዓክልበ.። ከመሥራቹ ማራ ዩ (2674-2612 ዓክልበ. የገዛ ተብሎ) ይጀመራል።
- ሁለተኛው ዳኛዋቲ መንግሥት፣ 833 ዓክልበ.-138 ዓም
- ሦስተኛው ዳኛዋቲ መንግሥት፣ 138-780 ዓም።
በአራካን አፈ ታሪክ፣ በዚህ ፫ኛው መንግሥት መጀመርያ ጎታማ ቡዳ እራሱ አገሩን እንደ ጎበኘ ይባላል። በእንግሊዝ ጸሐፊው ፈይር ሐሣብ ግን ከጎታማ ዘመን በኋላ የቡዲስም እምነት ወደ አገሩ የገባበት ወቅት ይሆናል እንጂ በማለት በ፪ኛው ክፍለ ዘመን አደረገው።
ዘመናዊ የአራካን (ረክሐይን) ጥናት መምህሮች የአርሰር ፈይር አቆጣጠሮች በፍጹም እንደ ተሳቱ ጽፈዋል። በነርሱ አቆጣጠር፦
- መጀመርያው ዳኛዋቲ - 3325-1515 ዓክልበ.
- ሁለተኛው ዳኛዋቲ - 1515-588 ዓክልበ.
- ሦስተኛው ዳኛዋቲ 588 ዓክልበ - 320 ዓም.
በዚህ አስተሳሰብ ጎታማ ቡዳ በውነት በ፫ኛው ዳኛዋቲ መጀመርያ አገሩን ጎበኘ። ፫ኛ ዳኛዋቲ ከ588 ዓክልበ. እስከ ዌሻሊ መንግሥት እስከ 320 ዓም እንደ ቆየ አንዳንድ ማስረጃዎች አቅርበዋል።[1]
በአፈታሪኩ መሠረት፣ የ፩ኛ ሥርወ መንግስት መስራች ማራ ዩ ከሕንድ አገር አርያኖች ዙሪያ ከቫራነሲ ከተማ መንግሥት ፈለሰ። ሆኖም አርያኖቹ ይህን ከተማ ቫራነሲን የሠፈሩት በዛሬው ታሪክ ሊቃውንት ግመት ከ1500 ዓክልበ. (ርግ ቬዳ) በፊት አይሆንም። ስለዚህ፣ ማራ ዩ ወይም በ2674 ዓክልበ. ወይም በ3325 ዓክልበ. ያደረገው ነገሥታት ዝርዝር መጋነን ሳይሆን አይቀርም።