ዳርዳኑስግሪክና በሮሜ አፈ ታሪክ የዳርዳኒያ መንግሥት (በኋላ ትሮአስ) መሥራች ነበር።

የሮሜ ባለቅኔ ዌርጊሊዩስና ሌሎች እንደ ተረኩት፣ ዳርዳኑስና ወንድሙ ያሲዩስ (ያሱስ፣ ያሲዮን) ከ«ሄስፔሪያ» (ጣልያን) ነበሩ፣ ከአትላስ በኋላ ነገሡ፣ የንጉሥ «ኮሪቱስ»ና የእሌክትራ ልጆች ነበሩ። ዲዮኒስዮስ ዘሀሊካርናሦስ ግን ከአርካዲያ እና የዜውስና የኤሌክትራ ልጆች ያደርጋቸዋል። በግሪኮችና ሮማውያን አፈ ታሪክ ዘንድ፣ በአገራቸው ከታላቅ ጐርፍ በኋላ እስከ ሳሞትራቄ ድረስ በቆዳ ጀልባ ውስጥ ሰፈፉ። በዚያ በአረመኔ ሥርዓቶች ተሳተፉ፣ ያሲዩስ ከዴሜቴር ጋራ ካመነዘረ በኋላ ግን ዜውስ ገደለው ይባላል። ከዚህ በኋላ ዳርዳኑስ ወደ ደብረ ኢዳትንሹ እስያ ሔደ፤ በዚያ ንጉሡ ቴውኬር ሰላምታ ሰጥቶት ሴት ልጁን ባቴያን በትዳር ሰጠው። ዳርዳኑስ ርስትንም ከቴውኬር ተቀብሎ ከተማውን ዳርዳኒያና ከዚያም በላይ ጢምብራ የተባለውን ከተማ ሠራ፤ ጎረቤቶች ምድሮች ደግሞ ያዘ። በዳርዳኒያ መንግሥት ላይ ለ64 ወይም ለ65 ዓመታት ነግሦ ልጁ ኤሪክቶኒዮስ ተከተለው።

አኒዩስ ባሳተመው ዜና መዋዕል እንዳለው፣ ዳርዳኑስና ያሲዩስ የካምቦብላስኮን («ኮሪቱስ») እና የኤሌክትራ ልጆች ሲሆኑ ያሲዩስ ከአትላስ ኪቲም በኋላ በጣልያን (እንዲሁም በፈረንሳይ) ነገሠ፤ ዳርዳኑስ ግን ለጣልያን ዙፋን ብሔራዊ ጦርነት አደረገ። «አቦሪጌኔስ» ከነአለቃቸው ሮማነሦስ ከዳርዳኖስ ወገን ጋር ሲሆኑ፣ የእስፓንያና የሲኪሊያ ገዥ ሲኪሌውስ ግን የያሲዩስ ጓደኛ ነበር። በመጨረሻ በ1758 ዓክልበ. ግ. ዳርዳኖስ ወንድሙን ያሲዩስን ገድሎ ከጣልያን ወደ ሳሞትራቄ ደሴት ሸሸ፤ ከዚያም በ1736 ዓክልበ. አካባቢ ዳርዳኑስ ምድርን ከማዮንያ (ልድያ) ንጉስ አቲስ ተቀብሎ ትሮያን መሠረተ፣ ፷፬ ዓመታት በዳርዳኒያ መንግሥት ላይ ነገሠ። በምላሽ ዳርዳኑስ የሱን ይግባኝ መብት በጣልያን ለአቲስ ልጅ ለቲሬኑስ ተወው። ቲሬኑስ ወደ ጣልያን ሄዶ አስተዋይና የተወደደ ንጉሥ ሆነ፤ በዚህም ወቅት ፲፪ ነገዶች ከጣልያን ወደ ልድያ ፈለሱ። ሌሎችም ከልድያ ወደ ጣልያን ፈለሱ።

ቀዳሚው
የለም (አዲስ)
ዳርዳኒያ ንጉሥ ተከታይ
ኤሪክጦኒዮስ