ይሖዋ በዕብራይስጥ ቋንቋ יהוה በመባል በአራት ፊደላት (ሲነበቡ ዮድ ሔ ዋው ሔ) የተጠቀሰው የፈጣሪ ስም በአማርኛ የተለመደ አጠራር ነው።


የጥንት አይሁዳውያን በነበራቸው ወግ መሰረት ይህንን ስም በአደባባይ መጥራት እንደ ትልቅ ኃጢአት ስለሚቆጠር ከዚህ ወግ በፊት የነበሩት አይሁዳውያን (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈው የምናገኛቸው ግለሰቦችም ጭምር) ይህን ስም እንዴት አድርገው የጠሩት እንደነበር ማወቅ አልተቻለም።


በ1879 የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በዘጸዓት 6፡3 ላይ "እግዚአ-ይሆዋ" (Lord Jehovah) በማለት ይህንን ስም አስቀምጧል። አብዛኞቹ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአንዳንድ ቦታዎቻቸው ላይ "ያህዌ" ወይም "ያህዌህ" የሚለውን አጠራር የተጠቀሙ ሲሆን በአጠቃላይ "እግዚአብሔር" በሚለው ቃል መጠቀምን መርጠዋል።

መለኮታዊው ስም - አስፈላጊነቱና ትርጉሙEdit

በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ መዝሙር 83፡18 የተተረጎመው እንዴት ነው? ታዋቂው የኪንግ ጀምስ እንግሊዝኛ ትርጉም ይህን ጥቅስ "ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ (Jehovah) የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንህ ይወቁ።" ሲል ተርጉሞታል። በርከት ያሉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ የሚለውን ስም "እግዚአብሔር"፣ "ጌታ" ወይም "ዘላለማዊ" እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል።

ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ስም ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ እዚህ ጥቅስ ላይ በአይነቱ ልዩ የሆነ የግል ስም ሠፍሮ ይገኛል። ይህ ስም በዕብራይስጥ ፊደላት יהרה (የሐወሐ) ተብሎ ተጽፏል። በአማርኛ የተለመደው የዚህ ስም አጠራር "ይሖዋ" ነው። ይህ ስም የሚገኘው በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ ነውን? አይደለም። መጀመሪያ በተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 7000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል!

የአምላክ ስም ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበውን የናሙና ጸሎት እንመልከት። ጸሎቱ የሚጀምረው "በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ የቀደስ" በሚሉት ቃላት ነው።(ማቴዎስ 6፡9) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ "አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው" ሲል ወደ ፈጣሪ ጸልዮአል። "አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ" የሚል መልስም ከሰማይ መጥቷል። (ዮሐንስ 12፡28) የአምላክ ስም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ታዲያ አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ በማውጣት በማዕረግ ስሞች የተኩት ለምንድነው?

ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ይመስላል። አንደኛው ምክንያት ብዙዎች 'ስሙ መጀመሪያ ይጠራበት የነበረው መንገድ ዛሬ ስለማይታወቅ ልንጠቀምበት አይገባም' የሚል አቋም ያላቸው መሆኑ ነው። የጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጻፈው ያለ አናባቢ ነበር፣ (ልክ የጥንቱ የግእዝ ቋንቋ አጻጻፍ ያለ አናባቢ ይጻፍ እንደነበረው)። ስለሆነም ዛሬ የሐወሐ የሚሉት ፊደላት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንዴት ይነበቡ እንደነበር በእርግተኝነት የሚያውቅ የለም። ይሁን እንጂ ይህ የአምላክን ስም እንዳንጠቀም ሊያግደን ይገባልን? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ኢየሱስ የሚለው ስም ይጠራ የነበረው የሹዋ ወይም የሆሹዋ ተብሎ ሊሆን ይችላል፤ በአሁኑ ጊዜ ይህን በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም። ሆኖም ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች በቋንቋቸው የተለመደውን አጠራር በመጠቀም ኢየሱስ የሚለውን ስም በተለያየ መንገድ ይጠሩታል። ለምሳሌ ጂሰስ በእንግሊዝኛ፣ የሱስ ወይም ኢየሱስ በአማርኛ፣ ያሱ ወይም ያሹ በብዙ የአፍሪካ ቋንቋዎች፣ የሆሹዋ በዕብራይስጥ፣ ኢሳ በአረብኛ፣ የሱሳ በተለያዩ የኢትዮጵያ ደቡብ አካባቢ ቋንቋዎች የኢየሱስ ስም በተለያየ መንገድ ይጠራል። ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን አጠራር ስለማያውቁ ብቻ በዚህ ስም ከመጠቀም ወደኋላ አላሉም። በተመሳሳይም ወደ ውጭ አገር ብትሄድ የራስህ ስም በሌላ ቋንቋ ለየት ባለ መንገድ እንደሚጠራ ትረዳ ይሆናል። ስለዚህም ብዙ ሰዎች የአምላክ ስም ጥንት ይጠራበት የነበረውን መንገድ በእርግጠኝነት አለማወቃችን በስሙ እንዳንጠቀም ምክንያት ሊሆነን አይችልም የሚል አመለካከት አላቸው።

የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሁለተኛው ነገር ለረጅም ዘመን ከኖረ የአይሁዳውያን ወግ ጋር የተያያዘ ነው። ብዙዎች አይሁዳውያን የአምላክ ስም ፈጽሞ መጠራት የለበትም የሚል እምነት አላቸው። ይህ እምነት የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በተሳሳተ መንገድ ከመተርጎም የመነጨ እንደሆነ ካለው ሁኔታ መረዳት ይቻላል፦ "የእግዚአብሔር (የይሖዋ) አምላክህን ስም ያለአግባብ አታንሳ (ወይም በከንቱ አትጥራ)፤ እግዚአብሔር (ይሖዋ) ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሳውን በደል አልባ አያደርገውምና።" - ዘጸዓት 20፡7

ይህ ህግ የአምላክን ስም ያለ አግባብ (በከንቱ) መጠቀምን ወይም መጥራትን ያወግዛል። ይሁን እንጂ ስሙን አክብሮት በተሞላበት መንገድ እንዳንጠቀም በፍጹም አይከለክልም። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሁፎችን (ብሉይ ኪዳንን) የጻፉት ጸሐፊዎች በሙሉ አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ይመሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ናቸው። ሆኖም የአምላክን ስም በተደጋጋሚ ጊዜያት ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል በብዙ አምላኪዎች ፊት በታላቅ ድምጽ ይዘመሩ በነበሩ ብዙ መዝሙራት ውስጥ የአምላክን ስም ጠቅሰዋል። እንዲያውም ይሖዋ አምላክ አምላኪዎቹ ስሙን እንዲጠሩ ያዘዛቸው ሲሆን ታማኝ አገልጋዮቹም ይህንን ትዕዛዝ አክብረዋል። (ኢዩዔል 2፡32፣ የሐዋርያት ስራ2፡21) ስለዚህ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንዳደረገው የአምላክን ስም አክብሮት በተሞላበት መንገድ መጠቀም ይችላሉ።