የደም መፍሰስ አለማቆም
ሰውነት በተፈጥሮ የሚገጥሙ ጉዳትና አደጋዎችን የሚቋቋምበት እና የሚፈታበት የራሱ የሆነ ስርአት አለው። ደም በደህናው ጊዜ በደም ዝውውር ስርአት ውስጥ እና በደም ቧንቧዎች ውስጥ እየተዘዋወረ ይኖራል። ነገር ግን የደም ቆዳ እና ደም መልስ /አርተሪ እና ቬይኖች/ በሚጐዱበት ጊዜ ደም ማርሰስ ይጀምራል። ይህ ፍሰት ወደ ውጭ አለዚያ ውስጥ ወዳሉት ህብረ ህዋሳት /ቲሹዎች/ ሊሆን ይችላል።
ይህን የደም መፍሰስ በማቆም ወደ ጤነኛ ስርአት የሚመልስበት ሄሞስታሲስ የሚባል ስርአት በሰውነታችን ተጠናክሮ ይገኛል። በዚህ ሂደትም የደም መፍሰስ በሚገጥም ወቅት የተጐዱት የደም ቧንቧዎች ራሳቸውን በማጥበብ ፍሰቱን ለመግታት ሲሞክሩ ፕላትሌትስ የተሰኙት የደም ክፍሎች ደግሞ እርስ በእርሳቸው በመጣበቅ የተጠላለፈ ክር መሳይ ድር ይፈጥሩና ቀዳዳውን ለመድፈን ይጥራሉ። ደም የማርጋት ሂደቱም በዚሁ ይጀመራል። ይህ የማርጋት ሂደት እንደተጀመረ ከ20 የሚያንሱ ቅመሞችና ንጥረ ነገሮች በቅድመ ተከተል ይነቃቁና ደሙን ለማቆም ሂደቱ ይቀጥላል። በስተመጨረሻም ፋይብሪን የተባሉ ክሮች ተፈጥረው የተጐዳው አካባቢ ጋር በመጠቅጠቅ ጉዳቱ እንዲድን ያደርጋል። የደም መፍሰሱ እንደቆመና ጉዳቱ እንደዳነ ክሮቹ ይሟሙና አጠቃላይ የደም ስርአቱ ወደ ቀድሞው ጤናማ ሁኔታው ይመለሳል፡፡
ይህን ጤናማ የደም መፍሰስን የማቆምና የማርጋት ሂደት የሚያቀላጥፉ በርካታ ንጥረ ነገሮች ያገኛሉ። ከማዕድናት ደግሞ ካልሲየም ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ችግር ደም ሲፈሰን ቶሎ እንዳይቆም፣ ይህን ተከትሎም ለሚመጡ በርካታ የጤና ችግሮች ይዳርገናል። ሁኔታው በቁጥጥር ስር ካልዋለ እስከሞት ለሚደርስ አደጋ መጋለጥ እጣ ሊሆን ይችላል።
ደማችን መፍሰሱን ለምን አያቆምም?
ለማስተካከልየደም መፍሰስ ለመቆም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ የሚያደርጉ የማርጊያ ቅመሞች አለመኖር ወይም መጠናቸው ማነስ ሊሆን ይችላል። ለዚህ የቅመሞቹ ማነስ ወይም አለመኖር ሁለት ዋነኛ መነሻዎች ይጠቀሳሉ። በዘር ከወላጆች ችግሩን ይዞ መውለድ የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ደም የማርጋት ስርአቱን የሚያደናቅፍ ከውልደት በኋላ የመጡ የጤና ችግሮች ናቸው። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በቀይ የደም ህዋሳት እና ቧንቧዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ የጉበት ህመሞች፣ የኩላሊት ችግር፣ የቫይታሚን ኬ እጥረት፣ የመቅኒ ችግር እንዲሁም እንደ አስፕሪን ያሉ መድኃኒቶችን አዘውትሮ መጠቀም ቀድመው ይነሳሉ።
የደም መፍሰስ ያለመቆም ችግር ያለባቸው ሰዎች ችግር ከልጅነት ሊጀምራቸው አሊያም ካደጉ በኋላ በአጋላጭ ምክንያቶች ሊታይባቸው ይችላል። የደም አለመርጋት ችግር እንዳለ ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል በትንሹም በትልቁም መድማት፣ የአፍንጫ በተደጋጋሚ መድማት፣ የተለያዩ የቀዶ ጥገናዎች ከተደረጉ በኋላ የደም ፍሰት ቶሎ ያለመቆም፣ የድድ መድማት በብዙዎች ላይ ይታያሉ። እነዚህም ምልክቶች ተደጋግመው ከታዩ ሐኪም ጋር ቀርቦ ሁኔታው ከደም ያለመርጋት ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ በባለሙያዎች ይመከራል።
ሄሞፊሊያ የወንዶችን ደም አፍሳሹ ችግር
ለማስተካከልበተለይ ወንዶችን የሚያጠቃው በዘር የሚወረሰው የደም ያለመርጋት ችግር /በሳይንሳዊ አጠራሩ ሄሞፊሊያ/ የበርካታ ወንዶች ችግር ነው። ይህ ችግር በዘረ-መል ወንድ ልጅ ከእናቱ ሊወርሰው በሚችል ጤናማ ያልሆኑ ዘረ-መሎች እና የማርጊያ ቅመሞች ማነስ ይከሰታል። ይህ አይነት ሰው አፍንጫው ቢደማ ቶሎ አይቆምም፣ በትንሽ በትልቁ ይደማል። ይህ ሁኔታ በሴቶች የመከሰት ዕድሉ አነስተኛ ነው። የዚህን ዘረ-መል አይነት ሴቶች ቢሸከሙትም ህመም የመሆን አጋጣሚ ግን የለውም። እጅግ በጣም ጥቂት ሴቶች ሰዎች ላይ አልፎ አልፎ ምልክቶች ሊታዩ ቢችሉም ለክፉ የሚሰጣቸው አይደለም።
ሄሞፊሊያ የተሰኘው ይህ በዘር የሚተላለፍና ወንዶችን በተለይ የሚያጠቃ የደም አለመርጋት ችግር ፋክተር 8 በተሰኘ የደም ማርጊያ ቅመም ማነስ ምክንያት ይከሰታል። ችግሩ በምርመራ ከታወቀም ይህንኑ ያጠረ ቅመም በመስጠት ሊታከም ይችላል። ደም አለመርጋት መገጫ ከሁኑት ሁለት ዋነኛ ህመሞች ሁለተኛው ደግሞ ቮን ዊልብራንድ የተባለው ህመም ነው፡፡ ይህ ችንር ቮን ዊልበራንድ ፋክተር የተሰኘው ቅመም የሚያንስ በመሆኑ የደም መርጋቱን ለመፍጠር የሚረዱ የሚጠላለፉ ክሮችን መስራት በማስቸገሩ ይታወቃል። የዚህ ቅመም ማነስ ሰዎች በሚደሙ ወቅት ደሙ ቶሎ እንዳይቆም ያደርጋል። ችግሩ በሴቶች ሲከሰት የወር አበባቸው ላይ ችግሩ ይፈጥራል። የወር አበባቸውም ቶሎ አይቆምም።
የደም መፍሰስ ጠንቆች
ለማስተካከልየደም መፍሰስ ችግሩ በደም ማጣት ብቻ አይወሰንም። መቆም ያልቻለው ደም ፍሰት በአጭር እና ረጅም ጊዜ የተለያዩ የጤና ችግሮችንም ያስከትላል። ደም ያለመቆሙን ተከትሎ የሚከሰት ሞት እንደሚኖርም ባለሙያዎች ያስታውሳሉ። ከደም ያለመርጋት ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ ችግሮች ጥቂቶቹም የመገጣጠሚያዎች ጠባሳ እና የመገጣጠሚያ በሽታዎች፣ በዐይን ውስጥ ከሚከሰት የደም መፍሰስ የሚነሳ የዐይን ብርሃን ማጣት፣ የደም ማነስ፣ የነርቭ ችግሮች ናቸው።
የጥንቃቄ እርምጃዎችና የሕክምና መፍትሄዎች
እነዚህ የደም ለመርጋት መቸገር እና የደም በብዛት መፍሰስ ችግር ለማወቅ ቀደም ብለው የተጠቀሱ ምልክቶችን አስተውሎ ምርመራ ማድረግ ይሞከራል። የችግሩ አይነት እና ዝርዝር ሁኔታዎች በጥያቄዎችና የደም ምርመራዎች ከተለየ በኋላ እንደየግለሰቡ ሁኔታ ተመጣጣኝ የሆነ መፍትሄ በባለሞያዎቹ ይሰጣል። ከእነዚህ መፍትሄዎች መካከል ደም ለማርጋት አስፈላጊ የሆኑት ቅመሞች ማነስ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ቅመሞቹን ወደ ደም እንዲደርስ ማድረግ አንዱ መፍትሄ ነው። ከበድ ያለ የደም መፍሰስ ጉዳት ካለም ቅመሞቹን መጠን ከመተካትና ማሳደግ በተጨማሪ ደም መተካትም አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በህክምና ከሚሰጡ መድኃኒቶች በተጨማሪ የየራሳችን ለጤናማ የደም ግብአቶች ልንወስዳቸው የሚገቡ ማዕድናትን የያዙ ምግቦች መመገብም መልካም ነው። በተለይም እንደ ካልሲየም እና ፖታሲየም አይነት ማዕድናትን የሚይዙ አረንጓዴ አትክልቶች እና የወተት ተዋፅኦዎች ጠቃሚ ግብአቶች ናቸው። ዋናው ነገር ችግሩን በጊዜ ተረድቶ የባለሞያ እርዳታ በመፈለጉ ላይ ይሆናል። ደም ቶሎ አይቆምልዎትም እንግዲያው ችላ አይበሉት። ኋላ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል! ሠላም።