የአኪሊዮስ ተረከዝ
የትሮጃንን ጦርነት ከተካፈሉ ሁሉ አኪሊዮስ ዋናው ጀግና እንደነበር ሆሜር በድርሰቱ በኢሊያድ ያስነብባል። ግሪኮች የዚህን ምክንያት እንዲህ ሲሉ በአፈታሪካቸው ይናገራሉ፦
አኪሊዮስ ሕጻን እያለ ወደፊት በጦርነት እንደሚሞት ትንቢት ይነገር ነበር። እናቱም ልጇ እንዳይሞትባት ስለፈራች መፍትሄ ታፈላልግ ነበር። ምትሃታዊው ከሆነው ስቴክስ ወንዝ ውስጥ የተነከረ ሰው ከማንኛውም አደጋ ይድናል ሲባል ስለስማች ወደዚሁ ወንዝ ወስዳ ሕጻኑን በተረከዙ ይዛ ነከረችው።
እንደተባለውም በሰውነቱ ላይ ምንም አደጋ ስለማይደርስበት፣ ወጣቱ አኪሊዮስ እጅግ የተዋጣለት ተዋጊ ሆነ። በተሳተፈባቸው ማናቸውም ጦርነቶች ምንም ጭረት እንኳ ሳይደርስበት በአሸናፊነት እየተወጣ ስሙ ገነነ። የጠላት ወገን በብዙ ፍርሃት በሚርድባቸው በነዚያ ወራት፣ አንድ ጊዜ እንዳጋጣሚ ፓሪስ የተባለ የጠላት ወታደር የአኪሊዮስን ተረከዝ አነጣጥሮ መርዝ በተቀባ ቀስት መታው። እናቱ በምትሃተኛው ወንዝ ውስጥ ስትነክረው በተረከዙ ይዛው ስለነበር የወንዙ ውሃ ተረከዙን አልነካውም ነበር፣ ስለሆነም አክሊዮስ በፍጥነት ሞተ።
የዚህ አፈታሪክ ትርጉም፣ ማናቸውም ገዝፈው እሚታዩ ግለሰቦችም ሆነ ሥርዓቶች፣ ሁሉም እሚያጠፋቸው ድክመት አላቸው። አፈታርኩም እንዳየነዉ የአኪሊዮስ ተረከዝ በምትሃተኛዉ ወንዝ ስላልተነከረ ህወቱን ያጠፋበት ድክመት ሆንዋል።