የመዲና ሕገ መንግሥት በነቢዩ ሙሐማድ በመዲና በ614 ዓም የፈጠረው ሕገ መንግሥት ሲሆን እስከ 653 ዓም የራሺዱን ኻሊፋት መሠረት ሰነድ ነበር።

በአንዳንድ ምንጭ ዘንድ ይህ ሰነድ የዓለም መጀመርያው ሕገ መንግሥት ቢባልም ይህ ስኅተት ነው፤ የሕገ መንግሥት ታሪክ ይዩ።

የመዲና ሕገ መንግሥት (614 አ.ም.)

ለማስተካከል
  • ፩. ይህ የነቢዩ መሐመድ ጽሁፍ በቁራይሽያጥሪብ (መዲና) እስላሞችና ከእነርሱ ጋር በሚከተሉት፣ በሚተባበሩት፣ በሚታገሉት መካከል የሚነካው ነው።
  • ፪. ከሰው ልጆች ተለይተው አንድ ብሔርና ኅብረተሠብ ይሆናሉ።
  • ፫. የቁራይሽ ብሔርተኞች እንደ በፊቱ የደም ዋጋ ይከፍሉ፤ ለምርከኞቻቸው ቤዛ ግን ለእስላም አማኞች እንደሚገባ በምሕረትና በትክክል ይከፍሉ።
  • ፬-፲፩. (እንዲሁም የበኒ አውፍ፣ የበኒ ሳኢዳ፣ የበኒ አል-ሃሪጥ፣ የበኒ ጁሻም፣ የበኒ አል-ናጃር፣ የበኒ አመር ኢብን አውፍ፣ የበኒ አል-ናቢት፣ የበኒ አል-አውስ ብሔርተኞች እንደ #፫)
  • ፲፪. በአማኞች መካከል የደም ዋጋ ወይም ቤዛ የሚከፍል ድሃ ካለ ሊረዱት የጋራ ኃላፊነታቸው ነው።
  • ፲፫. ማንም አማኝ ከሌላው አማኝ ደንበኛ ጋር ያለርሱ ፈቃድ አይባበረም።
  • ፲፬. በአማኞች መካከል አንድ አመጸኛ ወይም በድለኛ ወይም ጥላቻ የሚያስፋፋ ማንም ሰው ካለ፣ የገዛ ልጁ ቢሆንም የሰው ሁሉ እጅ ይሆንበታል።
  • ፲፭. ማንም አማኝ ሌላውን አማኝ ስለ አረመኔ (ማለት እስላም ስላልሆነው ሰው ምክንያት) ከቶ አይገድልም፣ ወይም አማኙ አረመኔውን በሌላው አማኝ ላይ አይረዳውም።
  • ፲፮. የአላህ ጥበቃ አንድ የጋራ ነው። ከሁሉ ታናሽ ለሆነው ጥበቃ እንደሚደረግ ለሁላችሁ ይሁን። አማኞቹ እርስ በርስ ይረዳዱ እንጂ ሌሎችን አይረዱ።
  • ፲፯. እኛን የሚከተሉት አይሁዶች ደግሞ እርዳታና እኩልነት ያገኙ፣ እነርሱ አይበደሉም ጠላቶቻቸውንም አንረዳም።
  • ፲፰. የአማኞች ሰላም አንድ የጋራ ነው አይለየም። አማኞቹ በአላህ መንገድ ሲታግሉ፣ የአንዱ ወገን የግል ሰላም አይደረግም ማለት ነው። የሠላም ሁኔታ ለሁሉ እኩል መሆን አለበት እንጂ።
  • ፲፱. በዘመቻ ጊዜ አንዱ ፈረሰኛ ሌላውን ደባሉን ከኋላው ተከትሎ ይውሰደው።
  • ፳. አማኞቹ በአላህ መንገድ ሲታግሉ፣ የሌላው አማኝ ደም ከተፈሰሰ ቂሙን መበቀል ይኖርበታል።
  • ፳፩. አማኞች የተሻለውን መሪነት ከአላህ ተቀብለዋል። አረመኔ ለቁራይሹ እቃ ጥበቃ መስጠት አይፈቀድም፣ በጉዳዮቹም ምንም አይግባ።
  • ፳፪. ማንም ሰው አማኙን ያለ ምክንያት ከገደለው፣ ዘመዱ በደሙ ዋጋ ካልተጠገበ በቀር ገዳዩ በምላሽ ይገደል። አማኞቹ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ይጸኑበት፣ እርምጃ ይወስዱበት።
  • ፳፫. በዚሁ ጽሑፍ በአላህም በፍርድ ቀንም የሚያምን ሰው በድለኛውን ለመርዳት ወይም ለመጠብቅ ከቶ አይፈቀደም። እንዲህ ካደረገ ግን የአላህ እርጉማንና መዓቱ በሙታን ትንሳኤ ይሆንበታል፣ ያንጊዜ ምንም ንስሐ ወይም ቤዛ አይቀበልለትም።
  • ፳፬. ስለ ማንኛውን ነገር ስትለያዩ ጉዳዩ ለአላህና ለሙሐመድ ይቀርብ።
  • ፳፭. አይሁዶች በአማኞቹ ጎን እየታገሉ ለጦርነቱ ድርሻቸውን ይከፍላሉ።
  • ፳፮. የበኒ አውፍ አይሁዶች ከአማኞቹ ጋር አንድ ኅብረተሠብ ናቸው። የአይሁድና ሃይማኖት ለአይሁዶቹ ይፈቀዳል። ደንበኞቻቸውም እንዲህ ናቸው፤ በድለኛው ወይም ኃጢአተኛው ግን እራሱንም ቤተሠቡንም ይበድላል።
  • ፳፯-፴፬. እንዲሁም የበኒ አልናጃር፣ የበኒ ሳኢዳ፣ የበኒ አልሃሪጥ፣ የበኒ ጁሻም፣ የበኒ አውስ፣ የበኒ ጣላባ፣ ለጃፍና (የበኒ ጣላባ ክፍል)፣ ለበኒ አል-ሹታይባ አይሁዶች እንደ #፳፮ ይላል።
  • ፴፭. ታማኝነት ከከሐዲነት ይጠብቃል። የጣላባም ደንበኞች እንደነሱ ይሁኑ። የአይሁዶችም ጓደኞች እንደነሱ ይሁኑ።
  • ፴፮. ማንም ያለ ሙሐመድ ፈቃድ ወደ ጦርነት አይሄዱም። ከተበደሉ ግን ቂሙን ከማብቀል አይከለከሉም። ቂም በማብቀል ካልሆነ በቀር ሰውን የገደለው ሁሉ ራሱን ቤተሠቡንም ገድሏል።
  • ፴፯. አይሁዶች ለውጪያቸው ይሸከማሉ፣ እስላሞችም ለውጪያቸው ይሸከማሉ። በዚህ ጽሁፍ ከተዋዋሉት ወገኖች አንዱ ቢጠቃ፣ ሌላው ለመርዳት ይመጣል። እርስ በርስ ይመካከሩ፤ ታማኝነት ከከሐዲነት ይጠብቃልና።
  • ፴፰. ማንም ሰው ስለ ጓደኛው በደል ኃላፊ አይሆንም። የተበደለውም ሁሉ ሊረዳ ይገባል።
  • ፴፱. አይሁዶች በአማኞች ጎን እየታገሉ ለጦርነቱ ድርሻቸውን ይከፍላሉ። (= #፳፭ በማዳግም)
  • ፵. ያጥሪብ (መዲና) ለዚሁ ሰነድ ተከፋዮች የተቀደሠ ይሆናል።
  • ፵፩. በደል ወይም ወንጀል ካልሠራ በቀር፣ የቤት እንግዳ (መጻተኛ) እንደ ባለቤቱ ክቡር ነው።
  • ፵፪. ሴት በቤትሠብዋ ፈቃድ ካልሆነ በቀር የቤት እንግዳ አትሆንም።
  • ፵፫. ማናቸውም አስቸጋሪ የሆነ ጠብ ወይም ክርክር ቢነሣ፣ ወደ አላህና ወደ ሐዋርያው ወደ ሙሐማድ መቅረብ አለበት። በዚህ ሰነድ ለቅንነትና ለደግነት የሆነውን ይቀበላል።
  • ፵፬. ቁራይሽና የሚረዱአቸውም ጥበቃ አይሰጡም።
  • ፵፭. በያጥሪብ ላይ ጥቃት ከደረሰ እርስ በርስ ይረዳዳሉ።
  • ፵፮. የሰላም ውል ለመሥራትና ለመጠብቅ ቢጠየቁ፣ ይህን ማድረግ አለባቸው፤ እስላሞችም እንዲህ ቢጠየቁም የአላህ ጦርነት ካልሆነ በቀር ማድረግ አለባቸው። እያንዳንዱ ድርሻውን ከጎኑ በኩል ይቀበላል።
  • ፵፯. የአል-አውስ አይሁዶችና ደንበኞቻቸው እንደ ሌሎቹ በዚሁ ሰነድ ያሉትን መብቶች አላቸው፤ ውሉን እስከሚያከብሩ ድረስ። ታማኝነት ከከሐዲነት ይጠብቃልና ያገኘውን ለራሱ ያገኛል። አላህ ይህን ሰነድ ተቀብሏል።
  • ፵፰. ይህ ጽሑፍ ክፋተኛውን ወይም ከሓዲውን አይጠብቅም። በደል ወይም ክፋት ካላደረገ በቀር፣ ማንም ሰው ወደ ዘመቻ ቢሄድም ወይም እቤቱ ውስጥ ቢቆይም ጸጥ ይሆናል። አላህ ደጉን ታማኙንም ይጠብቃልና ሙሐመድ የአላህ ነቢይ ነው።