ክርስቶስ ሠምራ
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ከሷ በፊትም ሆነ በኋላ ካሉት ቅዱሳን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ያልጠየቁትን ዐይነት ምልጃ የለመነች ቅድስት ናት ማለትም ሰይጣን ይቅር እንዲባል የጠየቀች ልዩ ቅድስት ናት።
ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ | |
---|---|
ከታላላቅ ቅዱሳን አነስት አንዷ | |
የነበረችበት ጊዜ | በ፲፭ኛው ክፍለዘመን |
ያረፈችበት ቀን | ነሐሴ ፳፬ |
ንግሥ | ነሐሴ ፳፬ |
መዐረግ | ኢትዮጵያዊት ቅድስት |
የአባት ስም | ደርሳኒ |
የእናት ስም | ዕሌኒ |
የትውልድ ቦታ | ሸዋ ቡልጋ ልዩ ስሙ ቅዱስ ገዬ(ጥጥ ምድር) |
ዩምትከበረው |
በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን[1] |
በየወሩ የሚነበብ ገድሏን እዚህ ላይ በመጫን ይጠቀሙ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነንና ፀንተን ንጉሠ ሰማይ ወምድር እየሱስ ክርስቶስ በአማላጅነቷ ይቅርታን የምታሰጥ ለመሆኗ ቃል ኪዳን የገባላትን የክርስቶስ ሠምራን ገድል እንጽፋለን።
የእናታችን የክርስቶስ ሠምራ የትውልድ ሀገሯ ሸዋ ቡልጋ ስሙ ቅዱስ ጌየ የተባለ ቦታ ልዩ ስሙ ጥጥ ምድር አከባቢ ነው። የአባቷ ስም ደረሳኒ የእናቷ ስም ዕሌኒ ይባላል፡፡ እኒህም ቅዱሳን ሰዎች ደጋጎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ በሃይማኖት የጸኑ በበጎም ምግባር የከበሩ ነበሩ፡፡ ይህችንም ከእግዚአብሔር የተመረጠችና የተመሰገነች ልጅ ከወለዱ በኋላ በክብርና በስርዓት አሳድገው የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ትእዛዝ እያስጠኑ ብሉይ ከሐዲስ አስተማሯት፡፡
ዘመኑም ዓፄ ገብረ መስቀል ላሊበላ ከ1181 እስከ 1221ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩ ሲሆን በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆኑቱን የአለት ውቅር የሆኑትን የላሊበላ አብያተ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻወች በመገንባት ይታወቃሉ ። ላሊበላ በትክክለኛ አጻጻፍ ላይለ-በላይ ሲሆን ቃሉ በጥንቱ አገውኛ «ንቦች ሳይቀር ንጉስነቱን እውቅና ሰጡ» ማለት ነው።
ከዚያም የመኳንንት የመሳፍንት ልጅ ናትና ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ሠምረ ጊዮርጊስ ለሚባል ሰው አጋቧት፤ እሷም ዐስር ወንዶች ሁለት ሴቶች ልጆች ወለደች እኒያንም ልጆቿን በክብር በስርዓት አሳድጋ አስተማረቻቸው፡፡ በዘመኑ ዐጼ ገብረ መስቀል የሚባል ደግ ንጉሥ ነበረና ደግነቷን ዐይቶ ዝናዋን ሰምቶ አትርሽኝ ብሎ ፪፻፸፪ አገልጋይ ላከላት እርሷም ይህማ ከንቱ ውዳሴ ሊሆንብኝ አይደለምን መጽሐፍ ቢሆን ይነበብበት ይጸለይበት ገንዘብ ቢሆን ይመጸወት ነበር ብላ ወደ እግዚአብሔር አመለከተች፡፡
በዚችም ሰዓት ፊቱ እንደ ጸሐይ እያበራ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ የተወደድሽ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እንዴት ነሽ? እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠሸን ምግብ አንቺ ተመገቢ ብሎ ቅዱሳት በሚሆኑ እጆቹ ሰጣት እሷም ተቀብላ ፈጣሪዋን አመስግና ተመግባለች፡፡ ከተመገበችም በኋላ መንፈስ ቅዱስ በሰውነቷ መላባት አደረባት ከዚህ የተነሳ ብዙ ዘመን እህል ሳትበላ ውሀ ሳትጠጣ ቆየች፡፡ ከዚህም በኋላ ያ መልአከ እግዚአብሔር ከእንግድህ የእግዚአብሔር በረከት ረድኤት ካንቺ ጋር ይሁን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ስሪ ዐጸድ ትከይ ብሎ ሰላምታ ሰጥቷት ዐረገ፡፡
ያ ደገኛ ንጉሥ የሰጣትን አገልጋዮች አስጠርታ ቤተ ክርስቲያን ሥሩ ዐጸድ ትከሉ አለቻቸው እነሱም ዐጸድ ተከሉ ቤተ ክርስቲያን ሠሩ፤ ሥራውም ከተፈጸመ በኋላ ታቦተ ሚካኤልን አስገባች ለሷም በሰው ልጅ ያልታነጸ በመቁረጹ ያልተቀረጸ ኅብሩ የማይታወቅ መንበር አምጥቶ አንቺ አስቀድሽበት ብሎ ሰጣት እሷም ተቀብላ ፈጣሪዋን እያመሰገነች ስትኖር ከዕለታት አንድ ቀን ያ ደግ ንጉሥ ከሰጣት አገልጋዮች አንዲቷ መንፈስ ርኩስ የተዋሐዳት አገልጋይ ነበረችና ከክፋቷ እንድትመለስ ብትመክራት ክፉ አትናገሪ ብትላት አልመለስም ብላ አስቀየመቻት ብታዝንባት ሞተች፡፡
እሷም ይህማ በኔ ምክንያት ስትሞት ነፍሰ ገዳይ መሆኔ አይደለምን ፈጣሪዬ የቸርነትህን ስራ ሥራልኝ ብላ ብታዝን ብታለቅስ ያች ሙታ የነበረች አገልጋይ ተነሣችላት ቤተሰቦቿም መጥተው አገልጋሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሣች አሏት፡፡ እናታችን ክርስቶስ ሠምራም ሄዳ ያችን አገልጋይ ከሞትሽ በኋላ ማን አስነሳሽ? ብትላት አምላከ ክርስቶስ ሠምራ /የአንቺ አምላክ/ አስነሣኝ አለቻት፡፡ ከዚህም በኋላ እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በዓለመ ስጋ ሳለሁ ሙት ያስነሣልኝ ከሰው ተለይቼ ከሀገር ወጥቼ ብለምነው እንዴት በሰማኝ ብላ ልብሰ ምንኩስናዋን ቆቧን /አስኬማዋን/ አዘጋጀች፡፡ ቤተሰቦቿም ይህ ሁሉ የምናኔ ልብስ የማነው? አሏት፣ እሷም ኃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ነው አለቻቸው እነሱም መልካም ነው ብለው ተቀምጠው ሳለ ከዕለታት አንድ ቀን ልብሰ ምንኩስናዋን አስይዛ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሔደች ቤተሰቦቿም ከቤተ ክርስቲያን ልትቆይ መስሏቸው ወደ ዕለት ተግባራቸው ተሰማሩ ያች ሙታ የተነሳች አገልጋይ ሕጻኑን አዝላ ተከተለቻት መንገዷንም ፈጥና ስትሔድ በመንገዷ ላይ ብዙ ነዳያኖች አገኘች የያዘችውን ገንዘብ የለበሰችውን ልብስ ሁሉ ለነዚያ ድሆች ሰጥታ ልብሰ ምንኩስናዋን ለብሳ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብታ ሰውነቷ እስኪደክም ትሰግድና ትጸልይ ጀመረች፡፡ ከዚህ በኋላ የገዳሙ መነኮሳት ከሩቅ መምጣቷን ዐውቀው መንፈሳዊ ሰላምታ ከሰጧት በኋላ ወደ በአታቸው አስገቧት። ያን አብራ ይዛው የተሰደደችው ሕጻን ረኀብ ስለተሰማው ከገዳሙ ውጭ ሆኖ ያለቅስ ነበር ከእናቱ ከመለየቱም በላይ ጊዜው ጨልሞ ነበር። በዚያን ጊዜ አንዲት መበለት ሕጻኑን ለማንሣት ስትቃጣ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወደ ገነት አገባው ተመልሶ ወደ እርሷ መጥቶ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እንዴት ነሽ ልጅሽ ከደጅ ወድቆ የቀረ አይምሰልሽ ከገነት ተቀምጦ ከሕጻናት ጋር ዳግማዊ ቂርቆስ ተብሎ የሕጻናት አለቃ ሆኖ ተቀምጦልሻል አላት፡፡ ይህን ተናግሮ በኮከብ ተመስሎ ወደ ቤጌምድር ወሰዳት እሷም ከባሕር ገብታ እንደተተከለ ምሰሶ ሁና ሰውነቷ ተበሳስቶ ዓሣ መመላለሻ እስኪያደርጋት ድረስ ዓሥራ ሁለት ዓመት በባሕሩ ውስጥ ቆመች፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታ ወደ እርሷ መጥቶ ቃል ኪዳን ሰጣት የቃል ኪዳኑም መጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን ሙሉ ስንዴ ምርት አሳያት ባሳያትም ጊዜ አቤቱ ጌታዬ ምን አደርገዋለሁ አለችው ጌታም መለሰላት ተመልከች ልትበይው አይምሰልሽ አንዲት የስንዴ ፍሬ ከምድር ወድቃ ብዙ ፍሬ ሁና እንደምትነሳ አንቺም መንግስተ ሰማያት ብዙ ነፍሳትን ይዘሽ ለመግባትሽ ምሳሌ ነው አላት፡፡ እናታችን ክርስቶስ ሠምራም መለሰችለት በምን ሥራየ ነው ይህን ቃልኪዳን የሰጠኸኝ አለችው፡፡ ከዚህ ዓለም ንብረትሽን ንቀሽ ልጆችሽን እናት አባትሽን ጥለሽ ስለ ወጣሽ ነው ቃል ኪዳን የሰጠሁሽ አላት ይህንንም ብሏት ከሷ ተሰወረ፡፡ እናታችን ክርስቶስ ሠምራም ብቻዋን እንደልማዷ እስከ ሦስት ቀን ድረስ በባህር ውስጥ ቆማ ስለ ዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እያዘነች እያለቀሰች ቀረች፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ቅዱስ ሚካኤልን፣ ቅዱስ ገብርኤልን፣ቅዱስ ሩፋኤልን፣ እናቱ ማርያምን አስከትሎ ወደ ክርስቶስ ሠምራ መጣ እንዲህም አላት ቀድሞ ቅዱስ ሚካኤልን ባልደረባ ሰጥቸሽ ነበር ዛሬም እኒህ ተጨምረው ረዳት ይሁኑሽ ብሎ ሰጣት፡፡
እናቴ ማርያምም ጠላትን ድል ትነሽው ዘንድ እናት ትሁንሽ እኔን እንዳቀፈችኝ ትቀፍሽ፣ እንዳዘለችኝ ትዘልሽ ብሎ አዘዘላት፣ እመቤታችንም ልጄ ወዳጄ ሆይ ክርስቶስ ሠምራ በአንተና በቅዱስ ሚካኤል ላይ ፍቅሯ የጸና ነው ፤ ብላ ስትናገር ክርስቶስ ሠምራ በፊቷ ከምድር ላይ ወደቀች እግዝእትነ ማርያምም እንዴት ነሽ የልጄ ወዳጅ የነፍስ ሁሉ አማላጅ ብላ በእጇ አነሣቻት ባፏ ሳመቻት በደረቷ አቀፈቻት በጫንቃዋ አዘለቻት ከዚህም በኋላ እንዲህ አለቻት ልጄ ወዳጄ ያዘዘልሽን ፈጸምኩልሽ ከእንግድህ ወድህ እግዚአብሔር አይለይሽ ብላት ዐረገች፡፡ በዚያን ጊዜ ዓለሙ ሁሉ ድርቅ ችግር ረሀብ ሆኖ ሦስት ዓመት ሕዝቡ በየመንገዱ ወድቆ አሞራ ሲጫወትበት አይታ አዘነች አቤቱ ጌታየ ይህን ዓለም ለምን ፈጠርኸው እንዲህ ከንቱ አላፊ ጠፊ ከሆነ ቢቀር ይሻል ነበር /ክቡር ዳዊት ሰው ዕጸ ከንቱ ይመስላል/እንዳለ፡፡ ዕፀ ከንቱ ዕለቱን በቅላ ዕለቱን አብባ ዕለቱን አፍርታ ደርቃ ወድቃ ታድራለች የሰውም ኑሮ ይህን ይመስላል ብላ አለቀሰች፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ አዳም ከነልጆቹ ከሚሠራው ኃጢአት እኔ በዕለተ ዐርብ ከተቀበልኩት ፲፫ቱ ሕማማተ መስቀል ይህንን በልብሽ ብትመዝኝው ወደ ማንኛው ያደላ ይመስልሻል ቢላት መልስ ለመስጠት ተሳናት፡፡ ከዚህም በኋላ ክርስቶስ ሠምራ አቤቱ ፈጣሪየ እኔን ባሪያህን ከክፉ ነገር ሁሉ ሠውረኸኛልና ዲያብሎስን ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ አለችው ይኸውም ወድጀው አይደለም ስለ አዳምና ስለ ልጆቹ በጠቅላላውም ስለ ሰብአ ዓለም ሥጋቸው ሥጋየ ስለሆነ እንዳያስታቸው ክፉ ስራ እንዳያሰራቸው ብየ ነው ማርልኝ ማለቴ አለችው፡፡ ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊቱን ፈገግ አድርጎ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዕፁብ ድንቅ ልመና ለመንሽኝ ሌሎች በኋላሽም የነበሩ በፊትሽም የሚመጡ ያልለመኑትን ልመና ለመንሽኝ ብሎ ቅዱስ ሚካኤልን ጠርቶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ብላ ለመነችኝ እሺ ካላት ታምጣው ይዘኻት ሂድ አለው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም እሺ ብሎ እጅ ነስቶ ሰይፈ ቁጣውን መዞ ነይ እንሂድ አላት እርሷም ከቅዱስ ሚካኤል ፊት ፊት እየሄደች ከሲኦል አፋፍ በደረሱ ጊዜ ዲያቢሎስ በተኮነኑ ነፍሳት ላይ ተቀምጦ አየችው ቅዱስ ሚካኤልም በይ ጥሪው እሺ ብሎ ምሕረት ከወደደ አላት እሷም በጠራችው ጊዜ ሳጥናኤል ብሎ የጠራኝ ማን ነው? በዚህ በሠራዊት ማህል ነግሼ ከተቀመጥኩበት አለ፡፡ እናታችን ክርስቶስ ሠምራም እኔ ነኝ አለችው ወደ እኔ ለምን መጣሽ አላት እሷም ከፈጣሪህ ጋር አስታርቅህ ብየ አለችው እሱም አንቺን ከቤትሽ ከንብረትሽ ሳለሽ አስትሻለሁ ብየ ብመጣ ያጣሁሽ ሰው እኔን ልታስታርቂኝ መጣሽ? ግን ይህን ያደረገ ያ የቀድሞው ጠላቴ ሚካኤል ነው ሲጻረረኝ የሚኖር ከክብሬም ያወረደኝ እሱ ነው እንጂ አንቺ ምን ጉልበት አለሽ ብሎ አፈፍ ብሎ በግራ እጁ ቀኝ እጇን ይዞ ወደ ሲኦል ወርውሮ ጣላት ያን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በሰይፍ ቢመታው ሲኦል ተከፈተች ብርሃን ለበሰች ዲያብሎስም ከነሠራዊቱ ጮኸ ድልቅልቅ ሆነ ሲኦልም ከተከፈተች በኋላ ሰው በሰው ላይ ሆኖ ተጨናንቀው እንደ ውሻ ሲናከሱ አየች፡፡ ብዙ ነፍሳት እንደ ንብ መጥተው ሰፈሩባት እኒያን ነፍሳት ብትቆጥራቸው ፲ሺ /ዐሥር ሺህ/ ነፍሳት ሆኑ ቅዱስ ሚካኤልም እሷም እኒያን ነፍሳት ይዘው ወደ ፈጣሪያቸው በደረሱ ጊዜ እኒያ ነፍሳት የናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እንቦሳ ዘለሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሲኦል ብቻዋን ቀረች ዕርቃኗን ሆነች ዲያብሎስም ቅዱስ ሚካኤል አሸነፈኝ ብርቱ ጸብም ተጣላኝ ምርኮየንም ነጠቀኝ ብሎ ጮኸ አለቀሰ፡፡
እናታችንም ክርስቶስ ሠምራና ቅዱስ ሚካኤል የነፍሳት ምርኮአቸውን ይዘው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በቀረቡ ጊዜ ከፈጣሪያቸው ዘንድ ሰገዱ፡፡ ጌታም ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አደረግሽው ጥቂት ምርኮም አገኘሽን አላት እሷም መለሰችለት /መንክር ግብሩ ለእግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ/ እንዳለ ክቡር ዳዊት አቤቱ ጌታየ በአንተ ቸርነት በምሕረትህ ብዛት ደካማውን ብርቱ ብርቱውን ደካማ የምታደርገው አምላክ በኔ በባሪያህ ላይ አድረህ የቸርነትህን ሥራ ሠራህ አዎን አገኘሁ አለችው፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤልን እኒህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ወዳጄ ወደ ክርስቶስ ሠምራ ማደሪያ ውሰዳቸው ከሷ ጋር ደስ እያላቸው ይኖሩ ዘንድ አለው፡፡ እሷም መለሰችለት አቤቱ የኔ ጌታ ወዴት ነው አለችው እሱም ከእናቴ ከወለደችኝ ከማርያም በስተ ቀኝ ነው መቀመጫሽ አላት፡፡ ከእንግህም ስምሽ በትረ ማርያም ይሁን አላት፡፡ ዳግመኛም ይህንም ካላት በኋላ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ በየቀኑ ሦስት ሦስት እልፍ ነፍሳተ ኃጥአንን ከሲኦል እንድታወጪ ሥልጣን /ዓሥራት/ ሰጥቸሻለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት፡፡ አቤቱ ጌታየ ምሕረትህ የበዛ ፍርድህ የቀና ነው እያለች አመሠገነች፡፡ከዚህ በኋላ ነይ እግዚአብሔር ወደ አዘዘን እንሂድ አላት ተከትላው ስትሔድ የማር፣ የወይን፣ የዘይት አፍላጋት የሚያጠጡት አትክልቶች አየች ይህች ቦታ ለማን ትሆናለች ብላ ቅዱስ ሚካኤልን ጠየቀችው እርሱም መልሶ ምን ታስቢ ነበር አላት እርሷም ይህች ቦታ ለማን ተሆናለች እያልኩ አስባለሁ አለችው፡፡ እርሱም ለአንቺ ቢሆን ትወጃለሽን? አላት ፡፡ ምነው ዝቅ ታደርገኛለህ? ጌታየ ከእናቴ ከማርያም ጋር ነው መቀመጫሽ ብሎኝ የለምንምን? አለችው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ልብሽን ለምን ታኮሪዋለሽ አላት፡፡ ይህንንም ካላት በኋላ እስኪ ወደ ላይ ተመልከች አላት፡፡ ክርስቶስ ሠምራም ወደ ሰማይ ቀና አለችና እኔስ እንደ እንባ እንደኮረብታ ሆኖ ታየኝ እንጂ ሌላ ያየሁት ነገር የለም አለችው የሥላሴ ቸርነት እስኪገለጽ ጥቂት ቆይ አላት አንገቷን ዘንበል አድርጋ ቆይታ ቀና ብትል እመቤታችን እንደ ፀሐይ ሆና ከዋክብተ ብርሃን በፊት በኋላዋ ከበዋት አየች እሷም እንደ ንሥር ብር ብላ ሂዳ አንገቷን አቅፋ ጉልበቷን ሳመቻት:: እመቤታችንም ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እንዴት ነሽ? አንቺን የወለደች ማኅጸን የተባረከች ናት አንቺንም አጥብተው ያሳደጉ ጡቶች የተባረኩ ናቸው አንቺንም ያዩ ዐይኖች የተባረኩ የተቀደሱ ናቸው አንቺንም የሚያመሰግኑ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ያንቺን ገድል የሚሰሙ የሚያሰሙ የተባረኩ ናቸው ልጀ ወዳጄ ያዘዘልሽ ከኔ በስተቀኝ ነው ብላ በቀኟ አስቀመጠቻት፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ተመለሰች ጌታዋ ፈጣሪዋም አንቺን ያመሰገኑ ስምሽን የሚወዱ የሚጠሩ ዝክርሽን ያዘከሩ በዓልሽን ያከበሩ እስከ ፲፪ ትውልድ እምርልሻለሁ አላት፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ጠርቶ ወስደህ ከሥጋዋ አዋህዳት አለው ቅዱስ ሚካኤልም ወስዶ ከሥጋዋ ሊያዋሕዳት ሲል ሥጋዋ ሸቶ ገምቶ ብታየው ስለፈጣሪህ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ከዚህ ከሸተተና ከገማ ሥጋ አታግባኝ አለችው ቅዱስ ሚካኤልም የጌታዬን ፈቃድ ሳልፈጽም ለመቅረት እንደምን ይቻለኛል ብሎ ሰይፍ ከሰገባው ተመዞ እንደሚከተት እሷንም እንዲሁ ከሥጋዋ አዋሐዳት ያን ጊዜ ገምቶ ሸቶ የነበረውን ሥጋ አንድነት አድርጎ ቢያዋሕዳት ነፍሷን ስጋዋን አንድ ሆኖ ሕያዊት ነፍስ ለምልማ እንደነበረች ጸናች፡፡ እንደልማዷ ከባህሩ ገብታ ፲፪ ዓመት ከተቀመጠች በኋላ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፈረች ፲፩ ጦር አሠርታ ከውስጥ ዕፀ ከርካዕ ተከለችና ጌታን በዕለተ ዓርብ የግርግሪት እንደ አሠሩት እርሷም መበለት ጠርታ እሠሪኝ አለቻት መበለቲቱም እንዳዘዘቻት የግራዋን ወደ ቀኝ የቀኟን ወደ ግራ አመሳቅላ የፊጥኝ አሠረቻት ጌታችን እንደታሠረበት ባለው ስቁረት ችንካር ከታሠረች በኋላ እነዚያን ጦሮቹን አምጭ አለቻት እሺ ብላ አመጣችላት ሦስቱን በፊቷ ሦስቱን በኋላዋ ሦስቱን በቀኟ ሦስቱን በግራዋ ተከለችና ሥግደት ጀመረች፡፡ ከዚህም በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ፀንታለችና በብረቱ ላይ በምትሰግድበት ጊዜ ወደ ፊቷ ስትል ደረቷን ወደኋላዋ ስትል ጀርባዋን ወደ ቀኝ ስትል ቀኝ ጎኗን ወደግራ ስትል ግራ ጎኗን እየወጋት ፲፩ ዓመት ከጉድጓድ ውስጥ ኖረች፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ እንዲህ አላት ሰማይን ያለምሰሶ ምድርን ያለመሠረት እንደ አፀናኋት እኔንም ፈርተው የሚያከብሩኝን አልቅሰው አዝነው ተክዘው የሚጠሩኝን አከብራቸዋለሁ አላት ከዚህ በኋላ ጌታ ከኔ በታች ሁነሽ ትከብሪያለሽ መቀመጫሽም ከኔ በታች ነው የማዕረግ ስምሽ እንደ እናቴ እንደ ማርያም ሰአሊተ ምሕረት አቁራሪተ መዓት ነው አላት ይህንንም ካላት በኋላ ከጻድቃን ከሰማዕታት ከደናግል ከቅዱሳን ከእንጦንስ ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ክብርሽ ትክክል ይሁን አላት፡፡ ይህንንም ሰምተው መላእክት ዕፁብ ድንቅ ብለው አመሰገኑ ዲያብሎስም መላእክት ሲያመሰግኑ ሰምቶ ለወዳጅህ እንዲህ ያለ ዕፅፍ ድርብ ደስታ ትሰጣለህ ብሎ ጋዳ ጋዳ ብሎ አመሰገነ ጋዳ ጋዳ ማለት የሥላሴ ቸርነት ዕፁብ ድንቅ ነው ማለት ነው ከዚያም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕረፍትሽ ደርሷልና ከጉድጓድ ወጥተሸ ከባሕር ቆመሽ ለምኝኝ ብሎ ከእሷ ተሠወረ ቅዱስ ሚካኤልም የእግዚአብሔር አገልጋይ የቅድስት ድንግል ማርያምና የብርሃናውያን መላእክት ወዳጅ ሆይ የምትሰሪውን ሁሉ እግዚአብሔር ወዶልሻውልና እግዚአብሔር እንዳዘዘሽ ልብሽ የሚያስበውን ሁሉ ከባሕር ውስጥ ቆመሽ ለምኝው አላት፡፡
እሷም ቆስሎና ተበሳስቶ የነበረው ሥጋዋ እንደገና በእግዚአብሔር ኃይል የፀና ሆኖ ብርን ለብሳ እንደ ፀሐይ አብርታ ከጉድጓድ ወጣች፡፡ ከባሕሩ በገባች ጊዜ ጌታ ኤልያስን ሙሴን መትምቁ ዮሐንስን ሂዳችሁ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን አጥምቋት ብሎ አዘዛቸው ኤልያስና ሙሴ በቀኝ እጃቸው የብርሃን መስቀል ይዘው መጥምቁ ዮሐንስ የብርሃን አክሊልና በውስጡ ላህበ መለኮት ያልተለየው አፉ በእግዚአብሔር እደ ጥበብ የታተመ ሥራው በትእምርተ መስቀል አምሣል የሆነ የብርሃን ጽዋ እጁ ይዞ ወደርሷ መጡ፡፡
ከዚህ በኋላ ኤሊያስ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ የምህረት ቃል ኪዳን በልብሽ የሞላብሽ እንዴት ነሽ አላት ሰላምታህን እቀበል ዘንድ አንተ ማንነህ አለችው እኔ ኤሊያስ ነኝ አላት ይህን ባላት ጊዜ ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡
ሁለተኛም በእግዚአብሔር ኃይል ሰይጣንን ድል የነሳሽው ክርስቶስ ሰምራ ሆይ እንዴት ነሽ አላት እግዚአብሔር ይመስገን አንተ ማን ነህ አለችው እኔ ሊቀ ነብያት ሙሴ ነኝ አላት እሷም አንተን ያሳየኝ አምላክ ይክበር ይመስገን አለችው፡፡
ሦሥተኛ ዮሐንስ ሥምረተ አብ ሥምረተ ወልድ ሥምረተ መንፈስ ቅዱስ በልብሽ የተሞላብሽ እንዴት ነሽ አላት እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ አንተ ማን ነህ አለችው እኔ መጥምቁ ዮሐንስ ነኝ አላት ይህን ባላት ጊዜ ፈጣሪዋን አጥብቃ አመሰገነች፡፡
ከዚህ በኋላ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ እያሉ ኤሊያስ በቀኝ ሙሴ በግራ መጥምቁ ዮሐንስ በፊት በኋላዋ እየዞሩ እኛ ሰይጣንን እንደካድነው አንቺም ካጅው አሏትና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ወደ ባህር ገብተሸ ተጠመቂ እግዚአብሔር እንዳዘዘን ልናጠምቅሽ መጥተናልና አሏት፡፡ ይህን ባሏት ጊዜ ወደ ባህሩ ገባች ያን ጊዜ በዩሃንስ እጅ በነበረው የብርሃን ጽዋ በገዛ እጁ ተከፈተ ስለዚህም የእግዚአሔር ባለሟሎች ኤሊያስና ሙሴ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስም አደነቁ እሷም ይህን መለኮታዊ ጥምቀት በአምሳለ ትዕምርተ መስቀል በፈሰሰ ጊዜ ሰውነቷ በብርሃን ተሞላ የተጠመቀችበት ባህርም እስከ ሦሥት ቀን ድረስ እየበራ ቆየ፡፡ በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር የጥበቡን ሥፋት የቸርነቱን ብዛት እንዲሁም በቅዱሳን ነብያት አድሮ ያደረገላትን ቸርነት ዐይታ አደነቀች አመሰገነችም፡፡ ከዚህ በኋላ ዮሐንስ እንዲህ አላት ይህ ክብር ይህ ጸጋ ይህ ሹመት ይህ ግርማ ሞገስ የተጠመቅሽው በዕለተ ዐርብ ከጌታ ቀኝ ጎን የወጣ ማየ ገቦ ሌሎች ቅዱሳኖች አልተጠመቁበትም አላት እሷም መለሰችለት ምነው እንኳን ቅዱሳን ክርስቲያን ሁሉ የሚጠመቁበት በማየ ገቦ አይደለምን እኔስ በተወለድኩ በ፹ ቀኔ ተጠምቄ የለምን አለችው ይህስ እውነትሽን ነው ብለው አጥምቀዋት ተሠወሩ እሷም በበዓቷ ቀረች፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታዋን በዕውቀት ባለ እውቀት በስህተት በድፍረት የሚያስቀይምህን ሁሉ ማርልኝ አለችው ጌታም ወዳጄ ክርስቶስ ሰምራ ሆይ አማልጅን አትርሽን ያሉሽን ሁሉ እምርልሻለሁ ነገር ግን አባይ ጠንቋይን አልምርም ቀድሞ ለእናቱ ለማርያም በድግልናዋ በቅድስናዋ አባይ ጠንቋይ እንዳልምር ምያለሁ ብሎ ተሠወረ፡፡ ማዕቀበ እግዚእ የሚባል ሰው በዚያ አገር በማዕዶተ ጣና ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን መልአከ ጽልመት መጥቶ ይህችን ዕፀ ሕይወት ሰውነትሕን በጥተህ ብታገባ ድህነት እርጅና ሞት ማጣት አያገኝህም ነበር አለው፡፡ እንግዳውስ ይህ ሁሉ ካላገኘኝ በሁለመናየ በጥፍሬም ሳይቀር ቅበርልኝ አለው መልአከ ጽልመትም በል እግዚአብሔርን ካድልኝ አለው እሺ ብሎ ካደለት ሰይጣን ለወዳጁ ቅርብ ነውና በሰውነቱ በጥቶ ቀብሮለት ሄደ እሱም በሰይጣን ታምኖ ሲኖር እኒያ አያገኙህም ያለው ሁሉ ድህነት እርጅና ሞት ተሰብስበው መጡበት ይህ ሁሉ አያገኙህም ብሎኝ አልነበረምን አወይ የሰይጣን ነገር ብሎ አለቀሰ እስኪ ብታማልደኝ ወደ ክርስቶስ ሠምራ ልሂድ ብሎ አሰበ ጸጋ እግዚአብሔር ያልተለያት መንፈስ ቅዱስ ያደረባት ናትና ገና ሳይመጣ በጸጋ አውቃ አዘነችለት ከዚህ በኋላ ጌታችን ፈጣሪያችን መጥቶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እንዴት ነሽ ምን ያስለቅስሻል ምንስ ያሳዝንሻል አላት ማእቀበ እግዚእ የሚባል ሰይጣን ያሳተው አንተን የካደ አማልጅኝ ሊለኝ ስለመጣ ነውና እድትምርልኝ ብዬ አለችው እሱም እሱንስ አልምረውም አላት ስለምን ትኮንነዋለህ ብትለው እኔን ክዶ ዲያብሎስን አምኖ ዕፀ ሕይወትን በሰውነቱ በጥቶ አግብቷልና አልምረውም አላት ዕፂቱን አጥፍተህ እሱን ብትምረው ይቻልህ የለምን በዚያውስ ላይ አንተ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነውና ላንተ ምን የሚሳንህ ነገር አለ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡
እሱም ስለአንቺ ፍቅር ምሬልሻለሁ ብሏት ከሷ ተሠወረ፡፡ ከዚህ በኋላ ማዕቀበ እግዚእ ወደ እርሷ መጥቶ እመቤቴ አማልጅኝ አትርሽኝ ከፈጣሪዬ አስታርቂኝ አላት ጌታህስ ይቅር ብሎሃል አለችው ጌታዬ ይቅር ካለኝ በሰውነቴ የተቀበረውን ዕፀ ሞት ፍቀሽ ጣይልኝ አላት ያን ጊዜ ሰውነቱን በምላጭ ብትፍቀው ደሙ እንደ ቦይ ውሃ ፈሰሰ እርሱም ይህን ያደረገልኝ ከክህደት ወደ እምነት የመለሰኝ አምላክ ይክበር ይመስገን እያለ ሲያመሰግን ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ይህችም ነፍስ ከሰማዕታት ነፍሳት ማኅበር አንድ ሆነች እናታችን ክርስቶስ ሠምራም የዚህችን ነፍስ መግቢያዋን አሳየኝ እያለች ስትጸልይ ጌታ ነይ ላሰይሽ ብሎ ወሰዳት ያቺም ነፍስ ከፀሐይ ፯ እጅ አብርታ ማኅበረ ሰማዕት ሁና አገኘቻት ያን ጊዜ ጌታዋን አጥብቃ አመሰገነች ለንስሐ በቅተው የሚመጡትን ሁሉ ብርሃናቸው ከፀሐይ ፯ እጅ እንዲያበራ ዕውነት እልሻለሁ አላት፡፡
ወዲያውም መንግስተ ሰማያትን ውረሽ ግርማዬን ልበሽ በአላት ጊዜ ሰማይና ምድር ተናወፁ እሷም ለእግሯ መቆሚያ አጣች ጌታም አይዞሽ ጽኝ አላት ሰማይና ምድረም ጸኑ እናታችን ክርስቶስ ሠምራም ጌታዋን አመሠገነች፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ከሥጋዋ አዋሐዳት በነሐሴ ፳፬ ቀን ክብርሽም በዓልሽም ይሁንልሽ፣ አላት፡፡ ከዚህ በኋላ ጻድቃን ሰማዕታት መላእክት እናቱ እግዝእትነ ማርያምን ፣ መጥምቁ ዮሐንስን፣ ፲፪ቱን ነቢያት አብርሃምን ይስሐቅን ፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን፣ ሰሎሞንን፣ እንጦንስን፣ መቃርስን፣ ርዕሰ መነኮሳትን አስከትሎ ዐስር የብርሃን አክሊል አስይዞ በዕለተ ዓርብ ወደ እርሷ መጥቶ ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራን እጅ ንሷት አላቸው፡፡ እነሱም ጌታ እንዳዘዛቸዉ እሺ ብለዉ እንደቅጠል ረግፈዉ እጅ ነሷት እሷም የጌታየ ባለሟሎች ቅዱሳን ክቡራን እንዴት ናችሁ ብላ እጅ ነሳቻቸዉ፡፡ ከዚህ በኋላ ጌታ ገድልሽን የፃፈ ያፃፈ የሰማ ያሰማ በዓልሽን ያከበረ ዝክርሽን ያዘከረ ስምሽን የጠራ እስከ ዐስራ ሁለት ትዉልድ ድረስ ምሬልሻለሁ አላት፡፡ እሷም እንደ ገድል ማን ተኰንኖ እንደ ወንጌል ማን ጸድቆ የሚሉ ሰዎች አሉና ትምርራቸዋለህ? ትኰንናቸዋለህ? አለችው፡፡
እሱም እንደ ወንጌል ማን ጸድቆ እንደ ገድል ማን ተኰንኖ ብለዉ የሚጠራጠሩ ክፍላቸዉ ከአርዮስ ከሰባልዮስ ጋር ነዉ አላት:: ከዚህ በኋላ ጌታን አብዝታ አመሰገነችዉ ጌታም ከቤትሽ ከናትሽ ከአባትሽ ከልጆችሽ ፳፪ ዓመት ከጉድጓድ ከባህር እያለቀስሽ ኑረሻልና እንግዲህ ማረፊያሽ ደርሷል ነይ ዕረፊ አላት ሥጋሽም ከምድር ወድቆ የሚቀር አይደለም በኋላ በዕለተ ምፅአት አነሳዋለሁ እንዲህም ሲላት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች መላዕክትም ዕልልታ ደስታ አደረጉ ነቢያት ሐዋርያት ሰማዕታት ፃድቃንም ሁሉ በዕጃቸዉ እያጨበጨቡ በእግራቸዉ እያሸበሸቡ በአፋቸዉ እልል እያሉ ተቀበሏት፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ለወዳጄ ለክርስቶስ ሠምራ ዕድሜዋን ጨምረህ ፳፪ ዓመት የተጋደለችዉን ፳፭ ዓመት ብለህ ፃፍላት ዓለዉ ቅዱስ ሚካኤልም እሺ ብሎ ዕድሜዋንና ገድሏን ጽፎ ከበድነ ሥጋዋ አጠገብ አስቀምጦት ተገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ አባ ይስሐቅ የሚባል ጻድቅ መነኩሴ ከእናታችን ከክርስቶስ ሠምራ ዘንድ እየሔደ በረከት ይቀበል ነበርና ከዕለታት አንድ ቀን እንደልማዱ ተነስቶ ቢሄድ በድነ ሥጋዋን እንደ ምሰሶ ቆሞ አገኘዉ እጅ ቢነሣዉ ዝም አለዉ እናቴ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ምን አገኘሽ ባርኪኝ እንጂ ብሎ በድነ ስጋዋን ቢዳስሰዉ ቃል አልመለሰችለትም ነፍሷም ከሥጋዋ ተለይቶ አገኘዉ እየጮኸ አንድ ጊዜ በድንጋይ አንድ ጊዜ ከመሬት ሲወድቅ መነኮሳቶች ወንዶችም ሴቶችም ጩኸት ሰምተዉ አባታችን ምን ሆነህ ነዉ አሉት እባረካለሁ ብዬ ብመጣ ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ አገኘሁት አላቸዉ፡፡ በዚያን ጊዜ እነዚያ መነኮሳቶች አንድነት አለቀሱ አባታችን አባ ይስሐቅም በአንገቷ ላይ ያለዉን መፅሐፍ አዉጥቶ ቢያየዉ ከተወለደችበት ቀን ጀምሮ እስከ አረፈችበት ቀን ድረስ በሥላሴ ትእዛዝ በቅዱስ ሚካኤል ፀሐፊነት የተፃፈ መፅሐፍ ተገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ ቅዱስ አባ ይስሐቅን ጠርቶ ከጉድጓግ በድነ ሥጋዋን በሣጥን አድርገህ እግዚአብሔር የሰጣትን ክብርና ፀጋ እኒህንም ዓሥሩን አክሊላት አድርገህ ከቤተ መቅደስ አግብተህ አኑረዉ አለዉ እሱም እንዳዘዘዉ አደረገ፡፡ በፍጻሜ ዘመኗ በቁመቷ ልክ በዓት ሰርታ ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ ዐሥራ ሁለት ጦር ተክላ ወዲያ ወዲህ ሳትል፤ ቆማ ፲፪ አመት ኖራለች። ስትሰግድም ሥጋዋ በጦር ተወግቶና ተፈቅቶ አልቋል። ጌታም ይህን ሁሉ መከራዋን እንደመሥዋዕት ቆጥሮላት በቃል ኪዳኗ የተማጸነውን ስሟን የተራውን እስከ አሥር ትውልድ እንዲምርላት ተስፋዋን ነግሯት ክብርት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሜ መላእክት አሳርጓታል። የዕረፍቷ መታሰቢያ ነሐሴ ፳፬ ይከበራል። በረከቷ አማላጅነቷ፤ ቃል ኪዳኗ አይለየን አሜን። “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” ወደ ዕብ.፲፪፡፩¬-፪ (12:-1-2) ==> ቅድስቲቱ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል በፆም በፀሎት በተጋድሎ ከቆየች በኋላ ወደ ጣና ገዳማት በመጓዝ ከሌሎች ቅዱሳን የሚለያትን ጥያቄ ለፈጣረሪዋ አቅርባ እንደነበር ከገድሏ እንረዳለን። ቅድስት እንታችን ነፍሷን ያለ ርህራሄ የሚያስጨንቀውን ዲያብሎስን ለማስታረቅ ተነሳች። ምክንያቱም በአስፈሪው የሲዖል እሳት የሚንገበገቡት የሰው ልጆች ስቃይ አሳስቧታልና “ሳጥናኤል ይማር አለም ይዳን” ብላ ተማጸነች። ==> ጌታም ይህ ሁሉ መከራዋን እንደመሥዋዕት ቆጥሮላት በቃል ኪዳኗ የተማጸነውን፣ ስሟን የጠራውን፣ በስምሽን ዝክርን ያዘከረ፣ ገድልሽን የጻፈ ያጻፈ፣ የሰማ ያሰማ በዓልሽን ያከበረ እስከ አሥር ትውልድ (12) እንዲምርላት ተስፋዋን ነግሯት ክብርት ነፍሷን ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላዕክት አሳርጓታል። የዕረፍቷ መታሰቢያ ነሐሴ ሃያ አራት 24 ከተክልዬ በዓል ጋር ይታሰባል (ይከበራል) ። ==> በተጨማሪም ከባሕር ላይ ቆማ ስትፀልይ ፲ (10) አክሊል ወርዶላታል። ገዳሟ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ሲጓዙ ሸኖን አለፍ ብለን ሰንቦ ከምትባል ከተማ ስንደርስ ወደ ቀኝ ታጥፈን ጠጠራማጥርጊያ የአርበኞች ጎዳና ይዘን ስንጓዝ ቡልጋ ሀረገ ማርያም፣ ኮዩ፣ ስኮር፣ ንፋስ አምባ የሚባሉ የገጠር ከተሞችን አልፈን ሾላ ገበያ ዋና እንደርሳለን። ከመኪናችን እንደወረድን ጥቂት መንደሮችን አልፈን በረጅም ርቀት አሻግረን ስንመለከት ጉብ ባለች መጠነኛ ቦታ ላይ ችምችም ያለ አጸድ ሲመለከቱ እና እይተጠጉ ሲሄዱ ከ 800 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ በኢትዮጵያዊት ጻድቅ የእምነት ሴት አርበኛ ጻድቅ ክርስቶስ ሠምራ በእጇ የተተከለ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ቅርስ የተጋድሎ ባዕቷንና አሁን ታቦተ ህጉ ያለበትን ትንሽ መቆኞ ይገኛል። የገዳሟም ስም ጌዬ ገዳም ሲሆን ዕድሜ ጠገብ ባለታሪክም ነው። ==> “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። <== ” መዝ.፴፫፥፲፯¬-፳፩ 33፥17¬-21
ሱራፌል ጌታቸው surea520@gmail.com ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም እና ደብረ ትጉኃን ቅዱስ ገብርኤል ፍኖተ ህይወት ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ