ክሪስታቮ ደጋማ (ከ፲፭፻፰ አካባቢ እስከ ነሐሴ ፳፮ ቀን ፲፭፻፴፬ ዓ.ም.) በኢትዮጵያፖርቹጋሎችን ጦር መሪ የነበረ (1541-43) ሲሆን የግራኝ አህመድን ሰራዊት ቁጥሩ በጣም ባነሰ ሰራዊት አራት ጊዜ አሸንፎች በአምስተኛው ጊዜ ተማርኮ ሃይማኖቴን አልቀይርም ሲል የተገደለ አዋጊ ነበር። ሪቻርድ በርተን የተባለ የታሪክ ተመራማሪ ክሪስታቮን በጀግኖች ዘመን የተወለደ ቀደምት ጀግና ነበር ሲል አድንቆታል።[1] በሌላ በኩል ክሪስትቮ የታዋቂው አለም አቀፍ ተጓዥ ቫስኮ ደጋማ ልጅ ነበር።

ክሪስታቮ ደጋማ የግራኝ አህመድ ጦርን ሲገጥም

እስቲቮ የፖርቹጋሎችን ሃይል በቀይ ባህር በማስተባበር ኦቶማን ቱርኮችን እንደወጋ

ለማስተካከል

ክሪስታቮ ወደ ህንድ አገር በ1532 ከታላቅ ወንድሙ ስቲቮ ደጋማ ጋር በመሆን ከሄዱ በኋላ በ1535 ተመልሰዋል። ከዚያም በ1538 ወደ ዲዩ ከሌላ ተጓዥ ጋር ሄዷል። በነዚህ ጉዞወች ባሳየው ፈጣን አይምሮ የብዙወችን ህይወት አድኗል። ስለዚህ ስላሳየው ከፍተኛ ጥበብ የህንድ ገዥ የነበረው ታላቅ ወንድሙ ስቲቮ ደጋማ በ1541 በቀይ ባህር ውስጥ ቱርኮችን ለመዋጋት ካሰለፋቸው የፖርቹጋል መርክቦች የአንዱ አዛዥ አደረገው። ነገር ግን በዚህ ጦርነት ምንም ድል ስላላገኙ እ.ኤ.አ ግንቦት 22፣ 1541 መርከቦቻችቸው ምጽዋ ላይ መልህቃቸውን ጣሉ።

የኢትዮጵያው ዘመቻ

ለማስተካከል

የቀይ ባህሩን ጦርነት አለመሳካት ለመበቀልና የኢትዮጵያውን ንጉስ አጼገላውዲወስን ለመረዳት በክሪስታቮ የሚመራ 400 ጠመንጃ ያነገቱ የፖርቱጋል ሰራዊት የያዘ ጦር ወደ ውስጠኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሄድ ስቲቮ አዘዘ። ከነዚህ ሰባወቹ የእጅ ጥበብ አዋቂወችና መሃንዲሶች ሲሆኑ 130 የሚሆኑ አሽከሮችን ያቀፈና ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ አርቅብስ የተባለ የጥንት ጠመንጃ፣ አንድ ሽህ ረጅም የጦር ዘንግ እና ብዛት ያላቸው የጥንት መድፎችን ያካተተ ነበር። .[2] በዚህ ጊዜ አህመድ ግራኝ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከከፈት 14 አመት ሆኖት ነበር፣ 3/4ኛ የሚሆነውንም ክፍል ተቆጣጥሯል።

ጉዞ ወደ ደብራዋ

ለማስተካከል

በክሪስታቮ የሚመራው ጦር በምጽዋአርቂቆ ካረፈ በኋላ ያሁኑ ኤርትራ ጥንታዊ ዋና ከተማ ወደነበረው ደብራዋ ጉዞ ጀመረ ። ከ11 ቀን ጉዞ ኋላ የፖቹጋሉ ሰራዊት ደበራዋ ላይ ሓምሌ 20 ደረሰ። በሃከሉ ግን በግራኝ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትና በዚህ ምክንያት ከህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍና የእንባ ዋይታ እንደነበር ካስታንሶ ሳይመዘግብ አላለፈም። [3]

ከንግስት ሰብለ ወንጌል ጋር ስለመገናኘታቸው

ለማስተካከል

ደብራዋ ከደረሱ በኋላ ክረምት ስለገባ ከዚያ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ተረዱ[4] ነገር ግን ክሪስታቮ ወታደሮቹ እንዲሁ ቁጭ ብለው በስንፍና ክረምቱን እንዲያሳልፉ ስላልፈገ ከመድፎቹ መንሽራተቻ እንጨት ሰንጥቀው በመጋዝ መግዘው እንዲሰሩ አደረገ። ቀጥሎም ግራኝ አህመድን ተቀብለው የነበሩ ጎርቤት ሰፈሮችን እየዘመቱ እንዲያጠቁና እንዲመዘብሩ አደረገ። ደብራዋ ከነበረው ባህረ ነጋሽ ንግስቲቱ ሰብለ ወንጌል እሱ ካለበት ብዙ ሳትርቅ ደብረ ዳሞ ደብር ላይ ከሴት ልጆቹዋ እና ሰራተኞቻ ጋር እንደሰፈረችና አህመድ ግራኝ በብዙ ሙከራ ሊቆጣጠረው ሞክሮ ደብሩ እምቢ እንዳለው ተረዳ።[5] ክሪስታቮ ከ100 ወታደሮቹ ጋር እመሆን ወደ ደብሩ በመሄድ ንግስቲቱ የሱን ሰራዊት እንድትቀላቀል ጋበዛት። ግብዣውን በመቀበል ከ30 ወንዶች እና 50 ሴቶች ጋር በመሆን ወርዳ በትልቅ ስነስርዓት ከፖርቹጋሎቹ ጋር ተቀላቀለች። [6]

የመጀመሪያው ጦርነት

ለማስተካከል

ክረምቱ እንዳባራ ዘመቻው ወደ ደቡብ ጀመረ። ባመጡት የጦር መሳሪያ ብዛት እርምጃቸው በጣም ዘገምተኛ ስለነበር፣ ግማሹ መሳሪያቸ በደብረ ዳሞ እንዲቀመጥ ክሪስታቮ አደረገ። በዚህ መንገድ በ1541፣ የገና ዕለት የክሪስታቮ ሰራዊት ቅድስት ሮማኖስ ቤ/ክርስቲያንን አልፎ [7]ጥምቀትን በዓል ከነሰራዊቱ በአጋሜ አውራጃ አከበረ።[8] ደጋማ ለመጀመሪያ ጊዜ የ እስላሞቹን ጦር በ ታህሳስ 2፣ 1542 አምባ ሰናይትሓራማት ላይ የባጫንቴ ጦርነት በሚባለው ገጠማቸው። [9] በዚህ ጦርነት ላይ የፖርቹጋሎቹን ቁጥር ማነስና የጠላት ጦር በአምባ ላይ ሆኖ ተመቻችቶ መቀመጥን በማገናዘብ ንግስት ሰብለ ወንጌል አምባውን በመከለል እንዲያልፉትና የልጇ የገላውዲወስ ጦርን ከሸዋ እስኪመጣ እንዲጠብቁ ምክር ሰጣ ነበር። ነገር ግን ክሪስታቮ፣ አምባውን በጀግንነት ካልተቆጣጠሩት በመንገድ ላይ የተቀላቀላቸው የኢትዮጵያ ሰራዊት እምነት በማጣት ሊከዳቸው እንደሚችልና የአካባቢው ህዝብም የምግብና መሰል እርዳታወች ሊያቋርጥ እንደሚችል በማስረዳት እድሉን መሞከር እንዳለበት ከገለጸላት በኋላ ወደ አምባው አመራ። ጠላት አምባው ላይ ሆኖ በድንጋይና በቀስት ቢዋጋም እነክሪስታቮ በመድፍ በመታጀብ የጦር ዘንጋቸውን እንደመሳሪያ በመጠቀም ተራራውን ድል አድርገው ወጥተው ያዙት። በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት እየመራ የተጋፈጠው እራሱ ክሪስታቮ ነበር፣ ይሁንና እግሩ ላይ በጥይት ከመቁሰል ውጭ ጉዳት አልደረሰበተም። በጦርነቱ 8 ብቻ ወታደሮች ነበር የሞቱበት[10]


ሁለተኛውና ሶስተኛው ጦርነት

ለማስተካከል

ንግስት ሰብለ ወንጌል እንደፈራችው የደብረ ሰናይቱ ጦርነት ዜና ለአህመድ ግራኝ ደረሰውና ወደ ሰሜን ዘመቻ ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ሁለቱ ሰራዊት ጃርቴ ወይም ዋጅራት ተራራ አጠገብ ተገናኙ። [11] ተፋጠው ባሉበት ሁኔታ ግራኝ ለፖርቹጋሎች የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንዲወጡ ወይም የራሱን ሰራዊት እንዲዋሃዱ አለዚያም ጦር ገጥመው እንዲጠፉ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ላከ። መልዕክቱ ከተሰማ በኋላ በኢማሙ ትዕዛዝ መሰረት መልዕክተኛው ለክሪስታቮ የመነኩሴ ቆብ በስድብ መልክ ሰጠው። ለዚህ መልዕክተኛ ሽልማት ሜዳልዮን ሰጥቶ ቢመልሰውም፣ ክሪስታቮ ቀጠል አድርጎ የራሱን መልዕክተኛ ወደ ኢማሙ በመላክ ኢትዮጵያ የመጣው በ"ባህሩ አንበሳ" ትዕዛዝ (የፖርቱጋል መንግስት) ሲሆን በሚቀጥለው ቀን አህመድ ግራኝ የክርስታቮን ማንነት እንዲያውቅ እንድሚያረገው ነገረው። ይኸው መልዕክተኛ ለአህመድ ግራኝ የጸጉር መንቀያ እና ትልልቅ መስታውቶች በስጦታ መልክ ሰጠው (ሴት ነህ ብሎ ለመስደብ) [12]

ከዚህ በኋላ ሚያዚያ 4 ላይ ጦር ገጠሙና የክሪስታቮ ሃይሎች ድል አደረጉ። በዚህ ጦርነት አንደኛው ወታደር ሲሞት ከግራኝ በኩል ደግም ግራኝ እራሱ ፈረሱን ሰንጥቆ ባለፈ ጥይት ቆሰለ። ፈረሱ ሞቶ ሲወድቅ ግራኝም አብሮ ስለወደቀ የኢማሙ ሰራዊት ንጉሳቸውን በቃሬዛ ተሸክመው በመሸሽ ከጦርነቱ ሜዳ ራቅ ብለው ሰፈሩ። ከ12 ቀን በሁዋላ እንደገና ጦርነት ገጠሙና አሁንም ከበፊቱ በበለጠ የግራኝ ጦር ተሸነፈ። በነዚህ ሁለት ጦርነቶች ውስጥ ክሪስታቮ እንዳዋጊ ትዕዛዝ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በድፍረት ፊት ለፊት እየተታኮሰ ጀግንነቱን አስመሰከረ። የሁለተኛው ዙር ጦርነት ድል ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም እነክሪስታቮ ይጠብቁት የነበሯቸው ፈርሶች በጊዜ ባለመድረሳቸው ግራኝ ሙሉ በሙሉ ሳይሸነፍ ወደ ደቡብ ለመሸሽ ቻለ። [13]

የግራኝን ሽንፈት የሰሙት የአካባቢው ህዝብ ለግራኝ ስንቅ ማቀበል አቆሙ፣ ይልቁኑም አመጽ ማስነሳት ጀመሩ። ከህዝቡ ግብር ለማስከፈል የሚላኩ ወታደሮች ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ መመናመን ጀመረ። ግራኝ በዚህ ጊዜ ዋጃራት [14] ወይም እንደ አንዳንድ ታሪክ ጽፊወች ዞብል ተራራ ሰራዊቱን አሰፈረ ።[15] ክሪስታቮም ግራኝን በመከተል እስከ አሻንጌ ሃይቅ ድረስ ዘምቶ በመሃሉ ክረምት ስለገባ በእቴጌ ሰብለ ወንጌል ምክር ወፍላ ላይ ሰፈረ።

አራተኛው ጦርነት

ለማስተካከል

በመሃሉ አንድ የአይሁድ እምነት ተከታይ አምባሰል ተራራ ላይ የግራኝ ጠንካራ ምሽግ እንዳለና ለጊዜው በጥሩ ሁኔታ መክላከያ እንደሌለው ነገረው። [16] ይህን ምሽግ በ3 ምክንያት ለመያዝ ፈለገ፡ 1) ምሽጉ ላይ ብዙ ፈረሶች ነበሩ እናም ፈረሶች ስለሚፈልግ 2) የኢትዮጵያው ንጉስ ገላውዴወስ ሸዋ ውስጥ ጦር ይዞ እየታገለ የነበረ ቢሆንም ሃይሉ ብዙ ስላልነበረና 3) በክሪስታቮና በገላውዲወስ ሃይሎች መካከል ያለ እንቅፋት ይሄው አምባሰል ላይ ያለው የግራኝ ምሽግ ስለሆነ ለመቆጣጠር ፈለገ። (በጊዜው ገላውዲወስ ከ30 እስከ 900 የሚደርሱ ጠመንጃ ያዥ ተከታዮች እንደነበሩት የተለያዩ ጻህፍት ይዘግባሉ) [17] ክሪስታቮ በፍጥነት ከ100 ወታደሮች ጋር በመሆን በተራራው ላይ በመዝመት ተቆጣጠረው። ከዚህ ድል መልስ ወፍላ ላይ ካለው ምሽግ ሲደርስ ግራኝ በሚቀጥለው ቀን እንደሚወረው ተራዳ። ኢማሙ በክረምቱ ወራት የዛቢድ (ደቡብ አረቢያ)ን ንጉስ በመማጸንና ገንዘብ በመላክ ብዙ ነፍጠኞች ፣ ክሪስታቮ ከነበረው በላይ አገኘ።[18]

አምስተኛው ጦርነት

ለማስተካከል

ፖርቹጋሎቹ በብዙ ጀግንነት ቢፋለሙም፣ ነሐሴ 28፣ የወፍላ ጦርነት ተብሎ በሚታቀው ከባድ ሽንፈት ገጠማቸው። በዚህ ወቅት 170 ብቻ ፖቹጋሎች በሂወት ተረፉ። ክሪስታቮም በጥይት እጁ ቆስሎ ከዋናው ጦር ተለይቶ በሸሸበት ቦታ በአካባቢው በነበረች አሮጊት ጠቋሚነት እሱና 14 ተከታዮቹ ከተደበቁበት ቁጥቋጦ ስር ተማረኩ። .[19]

የክርስታቮ ሞት

ለማስተካከል
 
የክሪስታቮ አሟሟት፣ የቤተክርስቲያኖች በግራኝ መቃጠል በኋላ የግራኝ በፖርቱጋልና በገላውዲዎስ መሸነፍ በቀኝ ጌታ ጀምበሬ ሃይሉ፣ ፲፱፻ ዓ.ም.

ከተማረከ በኋላ ክሪስታቮ ወደ አህመድ ግራኝ የጦር ካምፕ ተወሰዶ ለኢማሙ ቀረበ። ኢማሙም የተላከለተን የጸጉር መንቀያ በማውጣት የክሪስታቮን ጢም አንድ ባንድ በመንቀል ሃይማኖቱን እንዲቀይር አሰቃየው። [20] ክሪስታቮ በሃይማኖቱ ስለጸና በመጨረሻ ግራኝ አህመድ እራሱ በጎራዴ አንገቱን ቀልቶ ቅሪቱን አጠገቡ ወደነበረው ምንጭ ወረወረው። ካስታኖ የተባለው በጊዜው የነበር የፖርቱጋል ጸሃፊ ያ ምንጭ ወደ ጠበልነት እንደተቀየረ ይናገራል። [21]

ከሞቱ በኋላ

ለማስተካከል

ግራኝ በወፍላ ጦርነት ያገኘውን ከፍተኛ ድል ግምት ውስጥ በማስገባት የፖርቹጋሎቹ ሃይል ያለጥርጥር አልቆለታል በማለት ከነበሩት የቱርክና አረብ ወታደሮች 200 አስቀርቶ የተቀሩትን በተናቸው። ከዚያ ጣና ሃይቅ አካባቢ ደራስጌ እሚባል ቦታ ላይ ካሰራው ማረፊያ ቦታ ሄዶ ሰፈረ። በዚህ መካከል ግን ንግስት ሰብለ ወንጌልን የሚከተሉ 120 ጦረኞች ከወፍላው ጦርነት ከተረፉት የኢትዮጵያና ፖርቹጋል ሰራዊት ጋር ተቀላቀሉ። ከ10 ቀን በኁዋላም ልጇ አጼ ገላውዲስ ከወታደሮቹ ጋር ክሪስታቮ ነጻ ባወጣው አምባሰል አድርጎ ተገናኛቸው። በዚህ ወቅት ክሪስታቮ ከመሞቱ በፊት ደብረ ዳሞ ላይ ያከማቸውን መሳሪያ አስመጡና የኢትዮጵያዊውንና የፖርቱጋሉን ሃይል አስታጠቁ።

የወይና ደጋው ጦርነት

ለማስተካከል

በንዲህ ሁኔታ የተባበረው ሰራዊት ወደ ጣና በመትመም የግራኝን ጦር ወይና ደጋ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ ተጋፈጡት። በዚህ ጦርነት የፖርቹጋሎች ወታደሮች ሌላውን ክፍል ለኢትዮጵያውያን ትተው ባለፈው ጦርነት ላይ ብዙ ጉዳት ያደረሱባቸውን የቱርክ ወታደሮች ላይ በማነጣጠር ብዙ ጉዳት አደረሱ። በመካከሉም አንዱ ፖርቱጋላዊ ግራኝን አነጣጥሮ በመግደል የክሪስታቮን ሞት ሊበቀል ቻለ። [22]

 
የክሪስታቮ ደጋማ ፊርማ

ማጣቀሻወች

ለማስተካከል
  1. ^ Richard Burton, First Footsteps in East Africa (New York: Praeger, 1966), p. 181
  2. ^ According to Gaspar Corrêa, as translated by Whiteway, p. 274.
  3. ^ Castanhoso does not explicitly name this town, but Whiteway (p. xlvi) makes a convincing case that Debarwa is meant.
  4. ^ Whiteway, p. 9.
  5. ^ Whiteway, pp. xlvii f.
  6. ^ Whiteway, pp. 10-20.
  7. ^ Whiteway's identification (pp. l ff) of a "small house in which were some three hundred men, more or less, all desiccated, sewn up in very dry skins, the skins very much decayed but the bodies entire" (pp. 26f).
  8. ^ Whiteway, p. 28.
  9. ^ Whiteway, pp. lii f.
  10. ^ Whiteway, pp. 31f.
  11. ^ Whiteway, p. liv
  12. ^ Whiteway, pp. 26f
  13. ^ Whiteway, p. 51.
  14. ^ Whiteway, pp. lix f.
  15. ^ J. Spencer Trimingham, Islam in Ethiopia (Oxford: Geoffrey Cumberlege for the University Press, 1952), p. 89.
  16. ^ Whiteway, pp. 56 f.
  17. ^ The number of musketeers varies amongst the primary sources: Castanhoso states that there were nine hundred musketeers (Whiteway, p.55); the Emperor Gelawdewos in two different letters states that there were six hundred (translated in Whiteway, pp. 117, 120).
  18. ^ Whiteway, pp. 65 f.
  19. ^ Jerónimo Lobo, The Itinerário of Jerónimo Lobo, translated by Donald M. Lockhart (London: Hakluyt Society, 1984), pp. 207f; Castanhoso's account is translated in Whiteway, pp. 66-70.
  20. ^ Castanhoso in Whiteway, p. 68; Lobo, p. 208
  21. ^ Whiteway refers to this letter at p. lxiv n.1
  22. ^ Castanhoso fails to mention the story of John of Castillo, who charged into the Muslim troops so he could fire upon Ahmad Gragn at point-blank range, after which the Imam's followers killed him; however, every other near-contemporary account of the battle (e.g., Bermudez, Lobo) describes this as how the Imam died, so at the very least it was an early legend repeated in Ethiopian and Roman Catholic circles.