ኦስሮኤኔ
(ከኦስሮኤና የተዛወረ)
ኦስሮኤኔ (ግሪክኛ፦ Ὀσροηνή ፣ አረማይክ «የኡርኻይ መንግሥት») ከ140 ዓክልበ. ጀምሮ እስከ 234 ዓም በስሜን መስጴጦምያ የተገኘ ነፃ አገር ግዛት ነበር። ከዚያ በኋላ እስከ 600 ዓም የሮሜ መንግሥት (የቢዛንታይን መንግሥት) አውራጃ ሆነ። ዋና ከተማው ኤደሣ (አሁን ሳንሊዩርፋ፣ ቱርክ አገር) ነበረ። በ600 ዓም የፋርስ መንግሥት ያዘው።
የሰሌውቅያ መንግሥት እየወደቀ የኦስሮኤኔ መንግሥት በ140 ዓክልበ. ግድም የመሠረተው ሥርወ መንግስት ነባታያውያን ከተባለው አረባዊ ነገድ ነበር።
በአንዳንድ ታሪክ ዘንድ፣ ንጉሡ 5ኛው አብጋር በ24 ዓም ለኢየሱስ ክርስቶስ በደብዳቤ ይነጋገሩ ነበር። ኢየሱስም «በእጅ ያልተሠራ መልክ» እንደ ላከላቸው ተብሏል (የጄኖቫ ቅዱስ መልክ ይዩ)። ይህ 5ኛው አብጋር ክርስትናን ተቀብሎ ኦስሮኤኔ ያንጊዜ መጀመርያው ክርስቲያን አገር እንደ ሆነ በአፈ ታሪክ ተብሏል። በሌሎች ምንጮች ዘንድ ግን 9ኛው አብጋር በ192 ዓም ክርስትናን የመንግሥት ሃይማኖት መጀመርያ ያደረጉ ነበሩ።
በ108 ዓም የሮሜ መንግሥት አገሩን በጦር ያዘና እስከ 113 ዓም ድረስ «ደንበኛ ግዛት» አደረጉት። በ206 ዓም እንደገና ወደ ሮሜ መንግሥት ተጨመረ፣ የኦስሮኤኔ ነገሥታትም ከዚያ እስከ 234 ዓም ድረስ በስም ብቻ ቀሩ።